የኩባ ፖሊስ የረሃብ አድማ አድራጊዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በኩባ አንድ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ መታሰሩን በመቃወም የረሃብ አድማ ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎችን ፖሊስ መክበቡ ተሰማ።
የረሃብ አድማውን የሚመራው ቡድን ቢሮን በመዲናዋ ሃቫና ፖሊስ ከከበበ በኋላ በአድማው የተሳተፉ የተባሉ አባላትን በቁጥጥር ስር አውሏል።
ሳን ኢሲድሮ የተባለው እንቅስቃሴ ቡድን አራማጆችም እንደተናገሩት የተወሰኑት አባላሎቻቸው በፖሊስ እንደተደበደቡና መከበባቸውም ይፋ እንዳይሆን የማኅበራዊ ሚዲያቸውም እንደተዘጋ ገልፀዋል።
ራፐር ዴኒስ ሶሊስ ከፖሊስ ጋር በገባው እሰጣገባ ምክንያት ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።
የኩባ ባለስልጣናት ከበባው የተደረገው ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የተሰጠውን የጤና መመሪያን በመጣሳቸው ነው ብለዋል።
የሳን ኢስድሮ እንቅስቃሴ በቅርቡ ዓለም አቀፍ እውቅናን ማትረፍ ችሏል።
ከሁለት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ይህ እንቅስቃሴ የአርቲስቶች፣ የሙዚቀኞች፣ የጋዜጠኞችና የምሁራን ስብስብን የያዘ ሲሆን የኩባ ኮሚዩኒስት መንግሥት ያደርሰዋል የሚሉትንም ጭቆናን ለመቃወም ነው።
የቡድኑ አባላት ለቢቢሲ ሙንዶ እንደተናገሩት በመዲናዋ ሃቫና የሚገኘው ቢሯቸው በትናንትናው ዕለት በፖሊስ እንደተከበበ ነው።
ሌሊትም ላይ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 14 አባላቱ መካከል ሦስቱ ያሉበት እንደማይታወቅ ነው። የእንቅስቃሴው ስድስቱ አባላት ረሃብ አድማ ላይ ነበሩ።
ቡድኑ ከፖሊስ ጋር በነበረው የቃላት እሰጣገባ ምክንያት ስምንት ወር እስር የተፈረደበት ራፐር እንዲለቀቅ እየጠየቀ ነው።
የኩባ ባለስልጣናት ባወጡት መግለጫ ሳን ኢስድሮን ቢሮ የከበቡት ካርሎስ ማኑኤል አልቫሬዝ የተባለ ጋዜጠኛ የኮሮናቫይረስ መመሪያን በመጣስ በህንፃው ውስጥ በተቃውሞ በመሳተፉ ነው።
"እርምጃው የተወሰደው በሕጉ መሰረት ነው። የማንኛውንም ዜጋም ሆነ ተሳታፊዎችን መብት አልጣስንም" ይላል መግለጫው።
ሳን ኢስድሮ በበኩሉ በሰጠው ምላሽ "የማይረባ ሽፋን" ብሎታል።
ሳን ኢስድሮ ጥበብና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴን በማጣመር ውዝግብንም መፍጠር የቻለ ቡድን ነው። ማይክል ካስቲሎ የተባለው የቡድናቸው አባል ፖሊስ ለጥያቄ ሲፈልገው ተቃውሞውን ለማሳየት "አፉን ሰፍቶ" ነበር።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ሆኑ የአሜሪካ መንግሥት ዴኒስ ሶሊስ እንዲፈታና መንግሥት ከሳን ኢስድሮ እንቅስቃሴ አራማጆች ጋር ውይይት እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የኩባ መንግሥት በበኩሉ ሳን ኢስድሮ መንግሥትን ለመገልበጥ ከአሜሪካ ተልዕኮን ያነገበና በገንዘብ የሚደገፍ ነው ይላል። ሳን ኢሲድሮ በበኩሉ ይህንን ውንጀላ አይቀበለውም።

የፎቶው ባለመብት, EPA












