ትግራይ፡ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ተገለፀ

የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ

የፎቶው ባለመብት, Ministry Of Education Ethiopia

የኢትዮጵያ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ፈተናው ባለው ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ምክንያት መራዘሙን ነው የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በዛሬው ዕለት [ኅዳር 15/ 2013 ዓ.ም] በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት።

ባለፈው ዓመት በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ የነበረው የ8ኛ ክልል ክልላዊ ፈተና ግን ከታኅሳስ 1 እስከ 30 ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

የ8ኛ ክፍል ፈተና እንደየ ክልሎቹ ዝግጁነት የሚወሰን እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን ትምህርት ሚኒስቴሩ ባስቀመጠው ወቅትም ይሰጣል ተብሏል።

የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና መቼ እንደሚሆን ጊዜ ባይጠቀስም የትግራይ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ባሉ የሕግና ፀጥታን የማስከበር ሂደቶች መቋጫ እንዳገኙ እንደሚሰጥ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት ተማሪዎች በሚኒስቴሩ የተሰጠውን ውሳኔ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለፈተና እየተዘጋጁ እንዲጠባበቁም ሚኒስቴር ዴኤታው አሳስበዋል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶችን መዝጋትና ፈተናዎች እንዲራዘሙ ያደረገችው ኢትዮጵያ የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ኅዳር 22 እና 23 ቀን 2013 ዓ. ም ለመስጠት ማቀዷ ይታወሳል።

ከዚህም በተጨማሪ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከኅዳር 28 እስከ ታኅሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚሰጥም የትምህርት ሚኒስቴር ገልፆ ነበር።

በአገሪቱ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ዩኒቨርስቲዎች የተማሪዎችን ቅበላ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲያራዝሙም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ወስኗል።

ሚኒስቴሩ ለሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባስተላለፈው መልዕክት በተመደቡበት ያሉ ተማሪዎች በግቢያቸው እንዲቆዩ እና በየግቢያቸው የሚሰጧቸውን ማሳሰቢያዎችም እየተከታተሉ እንድትንቀሳቀሱ ብሏል።

ከአካባቢያቸው ያልተነሱ ተማሪዎች በቀጣይ ተለዋጭ ማስታወቂያ እስኪወጣ ድረስ በያሉበት እንዲቆዩም ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።

ባለፈው ዓመት በመላው ዓለም የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የትምህርት ተቋማት መዘጋታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ግን በተለያዩ ደረጃዎች የመማር ማስተማሩ ሂደት ይጀምራል ተብሎ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በትግራይ ውስጥ በተከሰተው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወሳል።