ዩኒቨርስቲዎች የተማሪዎችን ቅበላ ላልተወሰነ ጊዜ አራዘሙ

የፎቶው ባለመብት, Facebook
በአገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተማሪዎችን ቅበላን ላልተወሰነ ጊዜ አራዝመዋል።
ተማሪዎችን ላልተወሰነ ጊዜ እንደማይቀበሉ ካስታወቁት ዩኒቨርስቲዎች መካከል አምቦ፣ ባህር ዳር ፣ ደብረ ማርቆስና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች ተጠቃሽ ናቸው።
ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ባወጣው አስቸኳይ ማስታወቂያ ተመራቂ ተማሪዎች ጥቅምት 27 እና 28 2013 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲገቡ ጥሪ ማስተላለፉን አስታውሶ፤ "አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ጥሪ አድርገንላችሁ የነበራችሁ የዩኒቨርስቲያችን ተማሪዎች ወደፊት በአዲስ ማስታወቂያ ጥሪ እስከምናስተላልፍ ድረስ ባለችሁበት እንድትቆዩ እናሳስባን" ብሏል።
አምቦ ዩኒቨርሲቲም በተመሳሳይ ጥቅምት 25 እና 26 2013 ዓ.ም ተጠርተው የነበሩ ተማሪዎች "አሁን በተፈጠረው አሁናዊ ሁኔታ የትራንስፖርት ችግር መፈጠሩን ተረድተናል። በመሆኑም በያላችሁበት ቆዩ" ብሏል።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲው መድረስ ከቻሉ ግን ተማሪዎችን እንደሚቀበል በተጨማሪ ገልጿል።
ወራቤ ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 30/ 2013 ዓ.ም ተማሪዎችን የመቀበል ጥሪ አስተላልፎ እንደነበረ አስታውሶ፤ "የምዝገባ ፕሮግራሙ የተለወጠ እና ላልተወሰነ ግዜ የተራዘመ መሆኑን አስታውቋል።
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲም "ተመራቂ ተማሪዎች አሁን ካለው ሀገራዊ ሁኔታ አንፃር ለደህንነታችሁ ባላችሁበት እንድትቆዩ" ሲል አሳስቧል።
የኢፌዴሪ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ የተማሪዎችን እንቅስቃሴ ተገትቷል ተብሏል።
ሚኒስቴሩ ለሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባስተላለፈው መልዕክት በተመደቡበት ያሉ ተማሪዎች በግቢያቸው እንዲቆዩ እና በየግቢያቸው የሚሰጧቸውን ማሳሰቢያዎችም እየተከታተሉ እንድትንቀሳቀሱ ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የተለየ ጉዳይ ሲያጋጥምም ለተቋሞቻቸው ሃላፊዎች እንድትሳውቁም በማለት መግለጫው አስፍሯል።
ከአካባቢያቸው ያልተነሱ ተማሪዎች በቀጣይ ተለዋጭ ማስታወቂያ እስኪወጣ ድረስ በያሉበት እንዲቆዩም አሳስቦናል።












