ትምህርት ፡ ፌስቡክ ላይ በተሰራጨ ምስል ምክንያት ታሪኩ የተቀየረው ቦረና የሚገኘው ትምህርት ቤት

በቦረና ዞን በዱቡሉቅ ወረዳ የሚገን ትምህርት ቤት ከመታደሱ በፊት (በስተግራ) ከታደሰ በኋላ (በስተቀኝ)

የፎቶው ባለመብት, Dabeso Wariyo

በቦረና ዞን በዱቡሉቅ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጎዳና ጨርፊ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአካባቢያቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ የተነሳ የአካባቢያቸውን ነዋሪዎች በማስተባበር ትምህርት ቤት በአቅራቢያቸው ገንብተው ነበር።

ትምህርት ቤቱ እንደሚጠበቀው በአግባቡ የተገነቡ ክፍሎች እና አስፈላጊው ነገር የተሟላለት አልነበረም። ከዚያ ይልቅ ግድግዳው ከእንጨት፣ ጣሪያው ደግሞ በላስቲክ የተሸፈና ሲሆን ጥሩ የሆነ በር እንኳን እንዳልነበረው ያስታውሳሉ።

ከዚህም የተነሳ ጣሪያው ስለሚያፈስ በየዓመቱ መስከረም ሲመጣ ታድሶ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ ይደረግ ነበር።

አቶ ጎዳና እንደሚሉት ትምህርት ቤቱ መቀመጫ ስላልነበረው ተማሪዎች ይቀመጡ የነበረው በዱካ በተገኘው ነገር ላይ ነበር።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተማሪዎቹ የደንብ ልብስና የምገባ ፕሮግራም መጀመሩን በፌስቡክ ላይ በማየታቸው በአካባቢኣቸው ያለውን ትምህርት ቤት የማሳደስ የማሳሻል ሃሳብ እንደመጣላቸው አቶ ጉዳና ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚያን ጊዜ አንድ የትምህርት ቤቱ መምህር በቦረና ዞን ዱቡሉቅ ወረዳ የሚገኘውን ይህን ትምህርት ቤት የሚያሳይ ምሰልን ከአዲስ አበባ አስተዳደር ተግባር ጋር በማነጻጸር በፌስቡክ ላይ መለጠፉን ያስታውሳሉ።

የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ምስሉን ተቀባበሉት።

ከዚያ በኋላ በአገር ውስጥና በባሕር ማዶ የሚገኙ ሰዎች ትምህርት ቤቱን ለማደስ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መጠየቅና መወያየት መጀመራቸውን ይጠቅሳሉ።

ይህንን የተመለከቱ ግለሰቦች በመሰባሰብ ኮሚቴ አንድ ኮሚቴ አዋቅረው ሃሳብ መለዋወጥ እንደጀመሩ የኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ዳበሶ ዋሪዮ ስለሁኔታው ለቢቢሲ ሲናገሩ "ቀልድ የሚመስለው ነገር ነው ወደ ቁም ነገር የተለወጠው" ይላሉ።

"መጀመሪያ ላይ አንድ የያቤሎ ነዋሪ 30 ሺህ ብር እለግሳለሁ አሉ። ከዚያ በኋላ አሜሪካ የሚኖሩ ሰዎችም ማገዝ እንደሚፈልጉ ጻፉልኝ። እኛም በፍጥነት ኮሚቴ አዋቅረን የባንክ ሒሳብ ከፍተን አሳወቅናቸው፤ በአጭር ጊዜ አንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺህ ብር ሰበሰብን" ሲሉ ይናገራሉ።

በተሰበሰበው ገንዘብም ፈራርሶ የነበረውን ትምህረት ቤት በብሎኬት ገንብተው ለመማር ማስተማሩ ዝግጁ ማድረጋቸውን አቶ ዳበሶ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ትምህርት ቤቱን አስገንብተን የጨረስነው ሦስት ወር በሚሆን ጊዜ ውስጥ ነው። ለግንባታውም አንድ ሚሊዮን የሚሆን ብር ወጪ ተደርጎበታል፤ ገንዘቡም በፌስቡክ በኩል ባደረግነው ጥሪ የተሰበሰበ ነው።"

አቶ ዳበሶ አክለውም በፌስቡክ ተጠቅመው እንዲህ አይነት የኅብረተሰቡን ችግር የመቀርፍና በቋሚነት የሚያገለግል ሥራ በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

"ከፌስቡክ ተነስተን እንደዚህ አይነት ቁምነገር በመስራታችን ደስተኛ ነኝ፤ የኮሚቴው አባል በመሆኔም በጣም ደስተኛ ነኝ። አሁን ሁለተኛ ፕሮጀክት ጀምረናል፤ . . ." ይላሉ።

የወረዳው ነዋሪ የሆኑት አቶ ጎዳና በበጭራሮ ግድግዳ በላስቲክ ጣሪያ ተማሪዎችን እውቀት ለመስጠት ሲጥር የነበረው ትምህርት ቤት በበጎ ፈቃደኞች ጥረትና ድጋፍ ገጽታው ተለውጦ በማየታቸው ደስታቸው ወደር እንደሌለው ይናገራሉ።

"መጀመሪያ ልጆች የሚቀመጡበት ቦታ አልነበራቸውም፤ ደብተር የሚያስቀምጡበትም አልነበረም፤ ትልቅ ችግር ነበር። አሁን ሁሉም ስለተሟላላቸው በጣም ደስተኛ ነኝ" ሲሉ የመማሪያ ክፍሎች ብቻ ሳይሆን መቀመጫ መሟላቱ የፈጠረባቸውን ስሜት ለቢቢሲ አጋርተዋል።