ዘ ዊኬንድ የግራሚ ሽልማት "ሙሰኛ" ነው ሲል ተናገረ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ካናዳዊው ሙዚቀኛ ዘ ዊኬንድ፣ አቤል ተስፋዬ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ዘንድ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውን የግራሚ ሽልማት ሙሰኛ ነው አለ።
ከዚህ ቀደም የግራሚ ሽልማቶችን ያሸነፈው ዘ ዊኬንድ ለዘንድሮው ዓመታዊ የግራሚ ሽልማትም አልታጨም።
ሙዚቀኛው ያወጣው አልበም ከፍተኛ ተቀባይነትን ማግኘቱን ተከትሎ እንዲሁም በተለይም በአልበሙ የተካተተው 'ብላይንዲንግ ላይትስ' የተሰኘው ዜማው ተወዳጅ የሙዚቃ ሰንጠረዦችን በአንደኛ ደረጃ መምራቱን ተከትሎ ለግራሚ ሽልማት መታጨት ብቻ ሳይሆን በርካታ ሽልማቶችን ያሸንፋልም ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
"የግራሚ ሽልማት አሁንም ቢሆን ሙሰኛ ነው" በማለት በትዊተር ገፁ ላይ ያሰፈረው ሙዚቀኛው አክሎም "ለእኔም፣ ለአድናቂዎቼም ሆነ ለሙዚቃ ኢንዱስትሪው ሲባል ግልፅነትን እንጠብቃለን" ብሏል።
የግራሚ ሽልማት ኃላፊዎች በበኩላቸው የሙዚቀኛውን ቅር መሰኘት እንደተሰማቸው ገልፀው ነገር ግን በየዓመቱ ድንቅ ችሎታ ያላቸው ሙዚቀኞችም ሽልማት ላያገኙ ይችላል በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
'አፍተር ሃወርስ' የተሰኘው አልበሙ ከፍተኛ ሽያጭ በማስመዝገብ የዓመቱን ክብረ ወሰን የጨበጠ ሲሆን 'ብላይንዲንግ ላይትስ' የተሰኘውና በዚህ አልበም የተካተተው ሙዚቃው በአሜሪካ የሙዚቃ ሰንጠረዥን ለረዥም ጊዜ በመቆጣጠር ከአስሩ ምርጥ ተካቷል።
ከኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች በካናዳ ተወልዶ ያደገው ዘ ዊኬንድ (አቤል ተስፋዬ) በቅርቡ በሙዚቃው ስፍራ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ኤምቲቪ፣ ቪኤምኤና የአሜሪካ የሙዚቃ ሽልማቶችን አግኝቷል።
በየካቲት ወርም በአሜሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ስፍራ በሚሰጠው ሱፐር ቦውል የእግር ኳስ ጨዋታ በእረፍት ሰዓት ላይ ይዘፍናል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
በርካታ የአሜሪካ ሚዲያዎችም ሪፖርት እንዳደረጉት ሙዚቀኛው ከሽልማቱ እንዲወጣ የተደረገው በሱፐር ቦውል በመዝፈኑ ነው ተብሏል።
በሱፐር ቦውል እንዲዘፍን የተለያዩ ስምምነቶች ላይ መደረሱንና ገደብም ተቀምጧል ቢባልም የሽልማቱ አዘጋጆች በበኩላቸው የሙዚቀኛው ለግራሚ ያልታጨው ከእነዚህ ስምምነቶች ጋር በተያያዘ ነው የሚለውን አይቀበሉትም።
የዚህን ዓመት የግራሚ ሽልማትን እጩነትን የምትመራው ቢዮንሴ በዘጠኝ ዘርፍ ሲሆን፤ ከእሷ በተጨማሪም ዱዋ ሊፓ፣ ቴይለር ስዊፍትና ሮዲ ሪችም በስድስት ዘርፎች ታጭተዋል።












