ኢራን ፡ ጎምቱውን የኒኩሊየር ሳይንቲስት ማን ገደላቸው? ለምን?

ሳይንቲስቱ ሙሕሲን ፋኽሪዳዛን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሰውየውን እንኳንስ ሌላው ዓለም፤ ኢራኒያዊያንም በቅጡ አያውቋቸውም። ካለፈው አርብ በፊት ስማቸውን የሚያውቅ ኢራናዊ ብዙ አልነበረም።

ሳይንቲስቱን ሙህሲን ፋኽሪዳዛን በርካታ ኢራናዊያን ባያውቋቸውም ቅሉ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጠንቅቀው ያውቋቸዋል። ኢራናዊያን ባያውቋቸውም የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ግን መሐመድ ቢን ሰልማን አሳምረው ያውቋቸዋል። ኢራናዊያን ባያውቋቸውም የአሜሪካ የደኅንነት ሰዎች አሳምረው ያውቋቸዋል።

የኢራን ሚዲያ ጉምቱውን ሳይንቲስት ሙህሲን ተገድለውም ስማቸውን ማግነን አልፈለጉም። እንዲያውም ብዙም ቁልፍ ሰው እንዳልነበሩ ነው የሚያወሱት።

"ሰውየው አገር በቀል የኮቪድ-19 መድኃኒት ለመፍጠር ተመራማሪ ነበሩ" ሲሉ ነው ስማቸውን የሚያነሷቸው።

ማርክ ፊዝፓትሪክ በለንደን የስትራቴጂ ጥናት ተቋም ተመራማሪ ናቸው። የኢራንን የኒክሉየር ፕሮግራም በቅርብ ከሚከታተሉ ምሁራን አንዱ ናቸው።

ግድያውን ተከትሎ በጻፉት የትዊተር መልዕክት "የኢራን ኒኩሊየር ፕሮግራም በአንድ ግለሰብ ላይ የሚንጠለጠልበት ዘመን አልፏል" ሲሉ የሰውየው ሞት መሬት ላይ ብዙም የሚቀይረው ነገር እንደሌለ አስገንዝበዋል።

ሆኖም ሳይንቲስቱ የዋዛ እንዳልነበሩ የሚያውቁ ያውቃሉ። በተገደሉበት ወቅትም ከፍተኛ አጀብ ውስጥ ነበሩ። ይህም የሳይንቲስቱን ቦታ የሚጠቁም ነው። ይህን ሁሉ ጥበቃ አልፈው የሰውየውን ነፍስ ከነጠቁት ነፍሰ ገዳዮቹ ጀርባ ማን እንዳለ የሚጠቁም ነው።

እስከአሁን ለሳይንቲስቱ ሞት ኃላፊነት የወሰደ የለም። ነገር ግን እርምጃው ፖለቲካዊ እንዲመስል ነው የተደረገው፣ ከኒኩሊየር ጋር ላለማያያዝም ተሞክሯል። ይህ የኢራንም ፍላጎት ጭምር ነው።

በዚህ ረገድ ሁለት ምክንያቶች ጎልተው ይነሳሉ።

አንዱ የጆ ባይደን መምጣት ነው። የትራምፕ በጆ ባይደን የመሸነፍ እውነት ኢራን የሻከረ ግንኙነቷ እንዲለሰልስ የሚያደርግ ዕድል ይዞ ይመጣል የሚል ፍርሃት አለ። ይህ ከኢራን ጠላቶች መርዶ ነው።

ሁለተኛው መላምት ኢራንን በጉምቱው ሳይንቲስት ግድያ አስቆጥቶ ስሜት ውስጥ በመክተት የአጸፋ እርምጃ እንድትወስድ ለማድረግ ነው። የአጸፋ እርምጃ ከወሰደች ደግሞ አካባቢው ሌላ ዙር ረብሻ ውስጥ ስለሚገባ የባይደን ወደ ስምምነቱ መመለስን ያዘገይ ይሆናል የሚል ነው።

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ግድያውን ተከትሎ "ጠላቶቻችን አስጨናቂ ሳምንት ነው እያሳለፉ ያሉት" ያሉትም ይህንኑ ለማመላከት ነው።

"ዓለም አቀፉ ሁኔታ እየተቀየረ እንደሆነ ጠላቶቻችን ተገንዝበዋል። ያልተረጋጋ ሁኔታ ለመፍጠር የሞከሩትም ለዚህ ነው" ብለዋል የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሩሐኒ።

ሩሐኒ የኢራን ጠላቶች ሲሉ የትራምፕ አስተዳደርን፣ ሳዑዲንና እስራኤልን ማለታቸው ነው።

ኢራንና ሳዑዲ የጆ ባይደን መምጣትና በትራምፕ መውጣት ምቾት ሊሰማቸው አልቻለም። ይህ ሁኔታም መካከለኛው ምሥራቅን የፖለቲካ አሰላለፍ በተወሰነ ደረጃ የሚቀይር ውጤት ሊኖረው ይችላል።

ሳይንቲስቱን ሆስፒታል ውስጥ ለሞት ያበቃው ጥቃት የተፈጸመበት መኪና

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ሳይንቲስቱን ሆስፒታል ውስጥ ለሞት ያበቃው ጥቃት የተፈጸመበት መኪና

ጆ ባይደን በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ግልጽ እንዳደረጉት ወደ ኢራን የኒኩሊየር ስምምነት መመለስን ይሻሉ።

ይህ ስምምነት በባራክ ኦባማ ዘመን ጆ ባይደን ምክትል ሳሉ የጸና ነበር፤ ትራምፕ እስኪሰርዙት ድረስ።

በዚህ ለውጥ ፖለቲካዊ ድንጋጤ ውስጥ የገቡት ሳዑዲና እስራኤል በድብቅ ተገናኝተው ለመምከርም ተገደዋል።

ናታንያሁና ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን በአዲሷ የሳዑዲ ከተማ ኒዮም እሑድ ዕለት በምስጢር መገናኘታቸው የእስራኤል ሚዲያዎች አጋልጠዋል።

የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን የናታንያሁ ወደ ሳዑዲ፣ ኒዮም መምጣት ዜና ሐሰት ነው፤ አልተወያየንም ብለዋል።

ናታንያሁ በዚህ ኒዮም በተሰኘችው አዲስ ከተማ ውስጥ በነበረው ዝግ ስብሰባ ልዑል አልጋ ወራሹን መሐመድ ቢን ሰልማንን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንደ ሳዑዲና ባህሬን እንዲሁም ኢምሬትስ ሁሉ ለማደስ ጥያቄ ቢያቀርቡም አልተሳካላቸውም ተብሏል።

በስብሰባው ማግስት ሰኞ ዕለት በኢራን የሚደገፈው የሁቲ ሚሊሻ በየመን ባደረሰው ጥቃት የዓለም ቁጥር አንዱን ሀብታም ኩባንያ አራምኮን ጉዳት አድርሶበታል።

በቀይ ባሕር ዳርቻ ጂዳ የሚገኘውን የዚህ ነዳጅ ኩባንያ ንብረቶች በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አራምኮ የሳዑዲ አረቢያ ጉሮሮ እንደማለት ነው።

የኢራን ወግ አጥባቂ ሚዲያዎች የሁቲዎቹን ጥቃት "የጀግነነት ጥግ" ሲሉ አሞካሽተውታል።

"ይህ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። የሳዑዲና የእስራኤል ግንኙነት መደረጉን ተከትሎ ሆን ተብሎ የተሰነዘረ ጥቃት ነው" ይላል ማህር ዜና አገልግሎት። መልዕክቱም በኢራን ላይ አንዳች ነገር የምታስቡ ከሆነ በደንብ አስቡበት ለማለት ነው።

እርግጥ ነው ሳዑዲ በጥቃቱ ተቆጥታለች። አጋሯ አሜሪካም ነገሩ አበሳጭቷታል።

እንዲያውም ናታንያሁና ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን በኒዮም ያደረጉት ምስጢራዊ ስብሰባን ያመቻቹት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ናቸው። በዚያው ሰሞን ኳታርና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስን ጎብኝተው ነበር።

ይህ ሁሉ ከመሆኑ ከ2 ሳምንታት በፊት ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የደኅንነት አማካሪዎቻቸውን ምክር ጠይቀው ነበር።

"የኢራንን የኒክሊየር ማብላያን ልንመታው የምንችልበት ዕድል እንዴት ነው" ሲሉ ከአማካሪዎቻቸው ጋር ተማክረዋል ተብሏል።

ትራምፕ ነጩን ቤተ መንግሥት ከመሰናበታቸው በፊት በኢራን ላይ ከፍ ያለና የማያዳግም ጉዳት አድርሰው መውጣት ይሻሉ ይላሉ የአሜሪካ ሚዲያዎች።

በጥር ወር ትራምፕ የኢራኑን ኃያል ኮማንደር ቃሲም ሱለይማኒን በማስወገዳቸው ከፍ ያለ ኩራት እንደተሰማቸው ሲናገሩ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እርምጃውን ቢያወግዘውም ቅሉ።

"ኮማንደሩን አስቁመነዋል፣ ፈጣን እርምጃ ነው የወሰድነበት፣ በእኔ ትዕዛዝ ነው ያስወገድነው" ብለው ነበር ትራምፕ ስለ ሱለይማኒ ግድያ ሲናገሩ።

ይህ የሚያመለክተው ትራምፕ ከነጩ ቤተ መንግሥት ከመውጣታቸው በፊት ቁልፍ የኢራን ሰዎችን የማስወገዱን ነገር ሊያበረታቱ እንደሚችሉ ነው።

ግድያው በአሜሪካ በኩል በቀጥታ ባይፈጸምም በእጅ አዙር ደግፈው ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ነው።

ሌላዋ ተጠርጣሪ እስራኤል ናት። ይህ ግድያ እስራኤል ሳታውቀው ሊፈጸም አይችልም የሚሉ ሰዎች ናታንያሁ በ2018 የተናገሩትን ንግግር መዘው ያወጣሉ።

በቴሌቪዥን በተላለፈ አንድ መግለጫቸው ቤንያሚን ናታንያሁ ሙህሲን የተባሉትን እኚህን ጎምቱ የኒክሊየር ሳንቲስት ስም ጠቅሰው ነበር።

ይባስ ብለውም፤ "ይህንን ስም በደንብ ያዙልኝ" ሲሉ የሙህሲን ፋኸሪዛደህ ነገር ጠበቅ አድርገውት ነበር።

ይህ የሚያመላክተው እስራኤል በግድያው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ልትኖርበት እንደምትችል ነው።

እርግጥ ነው እስራኤል የጆ ባይደን መምጣት ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን እንዳስጨነቅ ላያስጨንቃት ይችላል።

ሆኖም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ የሚጠበቁት ሚስተር አንተኒ ብሊንከንና በመካከለኛው ምሥራቅ ያላቸው አቋም እስራኤልን አሳስቧታል።

ሚስተር ብሊንከን ቀንደኛ የኒክሊየር ስምምነት ደጋፊ ናቸው።

ሚስተር ብሊንከን አሜሪካ ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም ማዛወሯን ጭምር በግልጽ የተቹ ሰው ናቸው።

የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አሊ ኻመኒ ለግድያው ጠንከር ያለ አጸፋዊ ምላሽ እንደሚኖር ፍንጭ ሰጥተው ነበር። ሆኖም ይህ እውን ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።

ሌላኛው የኢራን ባለሥልጣን ሞህሲን ረዚ ጥቃቱ መፈጸሙ የኢራን የደኅንነት መሥሪያ ቤት ድክመት አለበት ሲሉ ያልተለመደ ትችት ሰንዝረዋል።

ግድያው ሊኖር እንደሚችል ቀድሞ መረጃ በመጥለፍ ደርሶ ማምከን ነበረበት ብለዋል።

የእኚህን ባለሥልጣን ቅሬታ ብዙ ኢራናዊያን ተጋርተውታል።

እንዴት በወታደራዊና ደኅንነት ትልቅ ስም ያላት ኢራን አንድዬ ኒክሊየር ሳንቲስቷን ግድያ ማስቆም አቃታት የሚለው ኢራናዊያንን አስቆጥቷል።

ሳይንቲስቱ የተገደሉት በጠራራ ፀሐይ ነው። ገዳዮቹም አልተያዙም። ምናልባት ኢራን ገዳዮቹን ለመያዝ በሚል በርካታ የተቃዋሚ ድምጾችን እንደምታፍን ይገመታል።

አሁን ለሳዐዲና እስራኤል እጅግ ውድ ወዳጅ የነበሩት ባለውለታቸው ዶናልድ ትራምፕ ነጩን ቤተ መንግሥት የመልቀቂያ ጊዜያቸው እየተቃረበ ነው።

ይህ እውነታ የኢራን ጠላቶችን የልብ ምት የሚጨምር ነው።

ጭንቀታቸው ደግሞ ትራምፕ ቀዳደው የጣሉትን የኢራን ኒክሊየር ስምምነት ባይደን ከተመለሱበት እየደቀቀች የነበረችው ጠላታቸው ኢራንና ምጣኔ ሀብቷ ዳግም ያንሰራራሉ ከሚል የመነጨ ነው።

ማዕቀብ እያከሳት የምትገኘው ኢራን ዶናልድ ትራምፕ ስልጣናቸውን የሚያስረክቡበትን የጥር ወር ከማንኛውም አሜሪካዊ በላይ በጉጉት ትጠብቀዋለች።

ጠላቷ ትራምፕ ከነጩ ቤተ መንግሥት መውጣታቸው ለኢራን ትልቅ ተስፋ ነው። አሁን በጉምቱው የኒክሊየር ሳይንቲስቷ መገደል ተነሳስታ በአካባቢው ሌላ ጫጫታ የሚፈጥር የበቀል እርምጃ መውሰድ የማትሻውም ለዚሁ ነው።

ዋናው ነጥብ ኢራን በዚህ ሰዓት ብቸኛ ተስፋዋ የሆነውን የጆ ባይደንን አስተዳደር ማስቀየምም አትሻም።

የበቀል እርምጃ ከወሰደችም የባይደን አስተዳደር ወደ ስምምነቱ ካልተመለሰ ብቻ ነው የሚሆነው ይላሉ የአካባቢው ተንታኞች።

የውድ ሳይንቲስቷ ሞት ቢያንገበግባትም ያላት አማራጭ ሐዘኗን ዋጥ ማድረግ ብቻ ነው።