ኢራን ከጀነራሏ ግድያ ጋር በተያያዘ በፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ የእስር ማዘዣ አወጣች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢራን በጥር ወር ላይ ኢራቅ ውስጥ ከተገደሉባት ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ ግድያ ጋር በተያያዘ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዲታሰሩ ማዘዣ አወጣች።
የኢራን አቃቤ ሕግ አሊ አልቃስሚር እንዳሉት ፕሬዝዳናት ትራምፕን ጨምሮ ሌሎች 35 ሰዎች የግድያና የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ዓም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖልም ተከሳሾቹን ለመያዝ በሚደረገው ጥረት እንዲተባባራቸው ተጠይቋል።
ቢሆንም ግን ኢንትርፖል በሰጠው ምላሽ የኢራንን ጥያቄን እንደማይመለከተው አሳውቋል።
የአሜሪካ የኢራን ልዩ ተወካይ በበኩላቸው ኢራን ያወጣችው የእስር ማዘዣ ከፕሮፓጋንዳ የዘለለ ማንም የምር የሚወስደው አይደለም ሲሉ አጣጥለውታል።
የኢራን የጦር መሪ የነበሩት ሱሌይማኒ በፕሬዝዳንተ ትራምፕ ትዕዛዝ በተፈጸመ ጥቃት ኢራቅ መዲና ባግዳድ ውስጥ በሚገኘው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ ነበር የተገደሉት።
ትራምፕ ጀነራሉን በመቶዎች ለሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮች ሞትና ወደፊት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በማቀድ እጃቸው አለበት በሚል ከሰዋቸዋል።
የጀነራሉን ግድያ ተከትሎ ኢራን የአሜሪካ ወታደሮች ይገኙባቸዋል በተባሉ ኢራቅ ውስጥ የሚገኙ ጦር ሰፈሮችን በሚሳኤሎች መደብደቧ ይታወሳል።
በእስር ማዘዣ ትዕዛዙ ላይ ትራምፕን ጨምሮ 36 የአሜሪካና የሌሎች አገራት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች ተካተዋል።
ፕሬዝደናት ትራምፕ በዝርዝሩ ቁጥር አንድ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከስልጣን ከወረዱ በኋላም ቢሆን ተይዘው እንዲቀርቡ የማድረጉ ጥረት ይቀጥላል ሲሉ የኢራን አቃቤ ሕግ ተናግረዋል።
የኢራን ምክትል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ሞሐሲን ባሓርቫንድ እንዳሉት የአገሪቱ ሕግ አውጪ በጀነራሉ ላይ ለተፈጸመው ግድያ የሰው አልባ አውሮፕላኑን ያንቀሳቀሱትን ሰዎች ጨምሮ ተጠያቂ ሰዎችን በመለየት ክስ ይመሰርታል ብለዋል።












