በጀነራል ሶሌይማኒ ቀብር ላይ ከ35 በላይ ሰዎች ተረጋግጠው ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, IPRES
በጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ በተፈጠረ መረጋገጥ ቢያንስ 35 ሰዎች መሞታቸውን የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
እንደ መገናኛ ብዙሃኑ ዘገባ ከሆነ፤ ተጨማሪ 48 ሰዎች በጀነራሉ የትውልድ ከተማ ኬርማን ተረጋግጠው ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በፕሬዝደንት ትራምፕ ትዕዛዝ የተገደሉት ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ በትውልድ ከተማቸው ግብዓተ መሬታቸው እየተፈጸመ ይገኛል።
በኢራቅ ባግዳድ ባሳለፍነው ዓርብ የተገደሉት ጀነራሉ፤ አስክሬናቸው ከኢራቅ ወደ ኢራን ሲጓዝ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢራቃውያን አደባባይ ወጥተው ሸኝተዋል።
ኢራቃዊያን የጀነራሉን አስክሬን ሲሸኙ ''ሞት ለአሜሪካ'' ሲሉ ተደምጠዋል።
ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ግለሰቦች መካከል አንዱ ነበሩ።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ጀነራሉ መገደላቸው ከተሰማ በኋላ ''የሶሌይማኒ የዓመታት የሽብር አገዛዝ አብቅቶለታል" ብለዋል።
"ሱሊማኒ በማንኛውም ሰዓት ሊቃጣ የሚችል የሽብር ሴራ በአሜሪካ ዲፕሎማቶች እና የጦር መኮንኖች ላይ ሲያሴር ነበር። ይህንን ሲፈጽም ያዝነው፤ አስወገድነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

በተያያዘ ዜና
- በተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ አሜሪካ ለማቅናት ቪዛ የጠየቁት የኢራኑ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ጃቫድ ዛሪፍ ቪዛ መከልከላቸው ታውቋል። ይህም የውጪ ሃገራት ባለስልጣናት ወደ ተባበሩት መንግሥታት እንደይጓዙ እክል በመፍጠር ስምምነት ጥሳለች የሚሉ ክሶች በአሜሪካ ላይ እየተሰነዘረ ነው።
- የኢራን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የአሜሪካ ወታደሮችን እና ፔንታጎንን አሸባሪ ሲል የሚፈርጀውን 'ሞሽን' አጽድቀዋል። ፓርላማው በተጨማሪም ጀነራል ቃሲም ሶሌይማኒ ይመሩት ለነበረው ጦር ኃይል ተጨማሪ በጀት አጽድቋል።
- ጀርመን አይኤስን ለመዋጋት ከምዕራባውያን ሃገራት ጋር ካሰማራቻቸው ወታደሮቿ መካከል የተወሰኑትን ከኢራቅ ልታስወጣ መሆኑ ታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ቃሲም ሱሊማኒ ማን ነበሩ?
ከእ.አ.አ. 1998 ጀምሮ ሜጀር ጀነራል ሱሊማኒ የኢራን ኩድስ ኃይልን ሲመሩ ቆይተዋል። ይህ ኃይል ከሃገር ውጪ የሚፈጸሙ ሚስጥራዊ ኦፕሬሽኖችን የሚያከናውን ነው።
ጀነራሉ በኢራቅ ውስጥ አይኤስ እና አል-ቃይዳን በመዋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው። ከዚህ በተጨማሪም፤ እኚህ የሽብር ቡድኖች እግራቸውን በኢራን እንዳይተክሉ ተከታትለው ድባቅ የመቷቸው ጀነራል ሱሊማኒ ነበሩ ተብሏል።
ጀነራሉ የሚመሩት ኃይል በሶሪያ ግጭት ውስጥ ተሳትፎ እንዳለው አምኗል። ለፕሬዝደንት በሽር አል-አሳድ ታማኝ ለሆኑ ወታደሮች የጦር ምክር ይሰጣል። እንዲሁም ለባሽር አል-አሳድ ታማኝ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሺያ ሙስሊሞችን አስታጥቋል። በኢራቅ ደግሞ አይኤስን እየታገሉ ለሚገኙ ለሺያ ሙስሊም ሚሊሻዎች ድጋፍ ያደርጋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የተከሰቱት ግጭቶች ጀነራሉ ኢራን ውስጥ እጅግ ዝነኛ ሰው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ጀነራል ሱሊማኒ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የኢራን ከፍተኛ የጦር ሽልማት ተቀብለዋል።
አሜሪካ በበኩሏ ጀነራሉ የሚመሩት የኩድስ ኃይል በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ አሜሪካን በጠላትነት በመፈረጅ በሽብር መናጥ ለሚፈልጉ ኃይሎች ፈንድ፣ ሥልጠና እና የጦር መሳሪያን ጨምሮ የቁስ ድጋፍ ያደርጋል ስትል ትወነጅላለች።
አሜሪካ እንደምትለው ከሆነ ይህ የኩድስ ኃይል ድጋፍ ከሚያደርግላቸው ኃይሎች መካከል፤ የሌባኖሱ ሄዝቦላ እንዲሁም የፍልስጤሙ እስላማዊ ጅሃድ ተጠቃሽ ናቸው።
የቀድሞ የሲአይኤ አለቃ የአሁኑ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ የኢራንን አብዮታዊ ጥበቃ እና ኩድስ ኃይሉን "የሽብር ቡድን" ሲሉ ከወራት በፊት ፈርጀውት ነበር።












