ኢራቃዊያን የጀነራሉን አስክሬን ሲሸኙ ''ሞት ለአሜሪካ'' ሲሉ ተደምጠዋል
በፕሬዝደንት ትራምፕ ትዕዛዝ የተገደሉት ጀነራል ቃሲም ሱሊይማኒ አስክሬን ከኢራቅ ወደ ኢራን እየተሸኘ ነው።
የጀነራሉን አስክሬን ለመሸኘት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢራቃዊያን አደባባይ የወጡ ሲሆን፤ ''ሞት ለአሜሪካ'' ሲሉም ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የጀነራሉ አስክሬን ወደ ኢራን ከተሸኘ በኋላ በተወለዱበት ከተማ ገብዓተ መሬታቸው የፊታችን ማክሰኞ ይፈጸማል ተብሏል።
ኢራቃዊያኑ አስክሬኑን ለመሸኘት ከንጋት ጀምሮ ነበር ወደ አደባባይ መትመም የጀመሩት። ብዙዎቹም የኢራቅን ሰንደቅ ዓላማ፣ የጀነራል ሱሊማኒን እና የኢራናዊውን የሃይማኖት መሪ አያቶላህ አሊ ካህሜኒን ምስል ይዘው ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ የተገደለው ጦርነት ለማስቆም እንጂ ለማስጀመር አይደለም ማለታቸው ይታወሳል።
በኢራን እና በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ የነበሩት ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ በፕሬዝደንት ትራምፕ ትዕዛዝ እንዲገደሉ ከተደረገ በኋላ፤ ትራምፕ 'ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት አስጀመሩ' ያሉ በርካቶች ነበሩ።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ግን የሱሊማኒ ''የዓመታት የሽብር አገዛዝ አብቅቶለታል" ብለዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ከፍሎሪዳ ግዛት ሆነው በሰጡት መግለጫ፤ "የአሜሪካ ወታደሮች በቅንጅት ባካሄደው ኦፕሬሽን፤ ቁጥር አንድ የዓለማችንን አሸባሪ ገድለዋል" ብለዋል።
"ሱሊማኒ በማንኛውም ሰዓት ሊቃጣ የሚችል የሽብር ሴራ በአሜሪካ ዲፕሎማቶች እና የጦር መኮንኖች ላይ ሲያሴር ነበር። ይህንን ሲፈጽም ያዝነው፤ አስወገድነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, Joe Raedle
በሌላ ዜና ጀነራሉ ከተገደሉ ከ24 ሰዓታት በኋላ አሜሪካ ዛሬ ጠዋት ሌላ የአየር ጥቃት በኢራቅ ፈጽማ እንደነበር የኢራቅ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል። ምንም እንኳን ይህ ዜና በአሜሪካ በኩል ባይረጋገጥም ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው ቅዳሜ ንጋት ላይ በተፈጸመው የአየር ጥቃት ተጨማሪ 6 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ፤ የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ኩድስ ኃይል አዛዥ በትራምፕ ትዕዛዝ ከተገደሉ በኋላ በቀጠና አሜሪካ ጠል እንቅስቃሴዎች ተንሰራፍተዋል።
ይህንን ተከትሎም የትራምፕ አስተዳደር በቀጠናው ለሚገኙ ዲፕሎማቶች እና አጋሮቿ ደህንነት ሲባል ተጨማሪ 3000 ወታደሮች ወደ መካከለኛው ምስራቅ እንደሚልኩ አስታውቀዋል።
ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ውስጥ ቁንጮ ከሚባሉ ግለሰቦች መካከል አንዱ ነበሩ።
ፔንታጎን (የአሜሪካ የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት) ጀነራል ሱሊማኒ "በፕሬዝደንቱ ትዕዛዝ" ተገድለዋል ሲል ማረጋገጫ ሰጥቷል።
ጀነራሉ የተገደሉት አሜሪካ በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ አየር ማረፊያ ላይ በወሰደችው የጦር እርምጃ መሆኑ ታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኢራን ምላሽ
ሃይማኖታዊ መሪው አያቶላ አሊ ካሃሜኒ በአሜሪካ ላይ አጸፋዊ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ ዝተዋል።
የጀነራሉ መገደል በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ያለውን ውጥረት ከፍ አድርጎታል።
የኢራን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ጃቪድ ዛሪፍ በትዊተር ገጻቸው ላይ አይኤስ፣ አል ኑስራህ፣ አል-ቃይዳ የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖችን ሲዋጋ የነበረውን ጀነራል የመግደል እርምጃ እጅግ አደገኛ እና የሞኝ ውሳኔ ነው ብለውታል።
አሜሪካ ሙሉ ኃላፊነቱን ትወስዳለችም ተብሏል።
አሜሪካ ዜጎች በፍጥነት ኢራቅን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበች
ጀነራሉ በትራምፕ ትዕዛዝ ከተገደሉ በኋላ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ውጥረት አይሏል።
በባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ፤ ዜጎች በተቻላቸው ፍጥነት ከኢራቅ ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል።
ኤምባሲው በቅርቡ በተቃዋሚዎች የደረሰበትን ጥቃት ተከትሎ ምንም አይነት አገልግሎት እንደማይሰጥ አስታውሶ፤ የአሜሪካ ዜጎች ወደ ኤምባሲው በፍጹም እንዳይቀርቡ አሳስቧል።
ከተቻላቸው በአየር ካልሆነ ደግሞ ወደ ጎረቤት ሃገራት በየብስ ከኢራቅ እንዲወጡ አስጠንቅቋል።
ኢራቅ፤ በኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ጆርዳን፣ ሶሪያ እና ቱርክ ትዋሰናለች።
ከኢራቅ በአየር መውጣት የማይችሉ አሜሪካዊያን፤ በየብስ ሳዑዲ ሁነኛ አማራጫቸው እንደሆነች ይታመናል።
የእስራኤል ጦር በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል
የጀነራሉን ግድያ ተከትሎ የእስራኤል ጦር በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
ኢራን የጀነራሏን ግድያ ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ አጋር በሆነችው እስራኤል ላይ በሌሎች ቡድኖች አማካኝነት ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች የሚል ግምት አለ።
በሂዝቦላ ወይም ሃማስ አማካኝነት አልያም ደግሞ ኢስላሚክ ጅሃድ በተሰኘው ቡድን በጋዛ በኩል እስራኤል ላይ የአጸፋ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል የሚሉት ግምቶች ከፍ ያሉ ናቸው።
የእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር እና መከላከያ ሚንስትሮች እስራኤል በተጠንቀቅ ላይ እንዳለች ይፋ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ቤይናሚን ኔታኒያሁ በግሪክ የነበራቸውን ጉብኝት አቋርጠው ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸውም ተነግሯል።
ጀነራል ሱሊማኒ በኢራን መንግሥት ውስጥ ሁለተኛው ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው ነበሩ። እርሳቸው የሚመሩት ኃይል ተጠሪነቱ በቀጥታ ለሃይማኖታዊ መሪው አያቶላ አሊ ካሃሜኒ ሲሆን ጀነራሉ በኢራናውያን ዘንድ እንደ ጀግና ነው የሚታዩት።
አያቶላ የጀነራሉን ግድያ ተከትሎ በኢራን የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሃዘን አውጀዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት አስተያየት ሰሳይሰጡ የአሜሪካን ባንዲራን በትዊተር ገጻቸው ላይ ለጥፈው ቆይተው ነበር።
የተፈጠረው ምን ነበር?
ፔንታጎን ባወጣው የጽሑፍ መግለጫ "በፕሬዝደንቱ ትዕዛዝ፤ ከሃገር ውጪ የሚኖሩ አሜሪካዊያንን ደህንነት ለመጠበቅ የአሜሪካ ጦር በወሰደው የመከላከል እርምጃ ቃሲም ሶሌኢማኒን ገድሏል" ብሏል።
"ጥቃቱ ኢላማ ያደረገው የወደፊት የኢራንን ጥቃት ለማስወገድ ነው። አሜሪካ ዜጎቿን እና ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ በማንኛውም አካል ላይ፤ በየትኛውም የዓለማችን ሥፍራ ቢገኙ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዷን ትቀጥላለች" ይላል የፔንታጎን መግለጫ።
ፔንታጎን ከዚህ በተጨማሪም፤ ጀነራሉ በኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን ለመግደል ሲያሴር ነበር ብሏል።
አሜሪካ ይህን ጥቃት የሰነዘረችው አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ ነበር። በወቅቱ የኤምባሲው አሜሪካዊያን ጠባቂዎች ከሰልፈኞቹ ጋር ተጋጭተው ነበር።
ፔንታጎን እንደሚለው ከሆነ ጀነራል ሱሊማኒ በኤምባሲው ላይ ጥቃቱ እንዲቃጣ ፍቃድ ሰጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በአየር ማረፊያው በወሰደችው ጥቃት ከጀነራሉ በተጨማሪ የኢራቅ ሚሊሻ መሪ አቡ ማሃዲ አል-ሙሃንዲስ እንደተገደሉ የኢራን አብዮት ጥበቃ አስታውቋል።
የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ፤ ከፍተኛ የጦር ኃላፊዎቹ የተገደሉት የአሜሪካ ሄሊኮፕተሮች በወሰዱት እርምጃ ነው ብሏል።
የጀነራሉን ግድያ ተከትሎ የተሰጡ አስተያየቶች፡
አሜሪካ
የጀነራል ሱሊማኒ ግድያ በአሜሪካ ሁለት ጎራዎችን ፈጥሯል።
የፕሬዝደንት ትራምፕ የፖለቲካ አጋር የሆኑት ሪፐብሊካኖች 'ሱሊማኒ የአሜሪካ ጠላት ነው' በማለት ግድያውን ደግፈዋል።
የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ማይክ ፖምፔዮ፤ ኢራቃዊያን የጀነራሉን ግድያ ተከትሎ ደስታቸውን ሲገልጹ የሚያሳይ ምስል በትዊተር ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
በሌላ በኩል ዲሞክራቶች የሱሊማኒን ግድያ አጥብቀው ኮንነዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ጀነራሉ እንዲገደሉ ትዕዛዝ ከመስጠታቸው በፊት ከአሜሪካ ኮንግረስ ፍቃድ መጠየቅ ነበረባቸው እያሉ ነው።
ኢራን
ኢራናውያን በጀነራል ሱሊማኒ ግድያ ብስጭታቸውን እየገለጹ ነው።
የኢራን ባለሥልጣናት በበኩላቸው ይህ የጦርነት ትንኮሳ ነው ብለውታል።
ሄዝቦላ
ሄዝቦላ የሺዓ ሙስሊም ፓርቲ እና የሚሊሻ ቡድን ነው።
ከኢራን የፍይናንስ፣ የቁስ እና የሥልጠና ድጋፎችን የሚያገኘው ሄዝቦላ መቀመጫውን በሌባኖስ መዲና ቤይሩት አድርጓል።
ሳይድ ሃሳን ነስረላህ የሄዝቦላ መሪ ሲሆኑ ጀነራል ሱሊማኒ ቢገደሉም የእርሳቸውን ፈለግ እንደሚከተሉ ገልጸዋል።
አሜሪካ ይህን 'ትልቅ ወንጀል' ፈጽማ የፈለገችውን ማሳካት አትችልም ማለታቸውን እና ለግድያው አሜሪካ ሙሉ ኃላፊነቱን እንደምትወስድ ተናግረዋል።
ሶሪያ
የሶሪያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር የአሜሪካን እርምጃ ኮንኗል።
የሶሪያ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሳና፤ የውጪ ጉዳይ ሚንስትርን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሶሪያ ለኢራቅ አለመረጋጋት አሜሪካ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳላት የሚያረጋግጥ ነው ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ቃሲም ሱሊማኒ ማን ነበሩ?
ከእአአ 1998 ጀምሮ ሜጀር ጀነራል ሱሊማኒ የኢራን ኩድስ ኃይል ሲመሩ ቆይተዋል። ይህ ኃይል ከሃገር ውጪ የሚፈጸሙ ሚስጥራዊ ኦፕሬሽኖችን የሚያከናውን ነው።
ጀነራሉ በኢራቅ ውስጥ አይኤስ እና አል-ቃይዳን በመዋጋ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው። ከዚህ በተጨማሪም፤ እኚህ የሽብር ቡድኖች እግራቸውን በኢራን እንዳይተክሉ ተከታትለው ድባቅ የመቷቸው ጀነራል ሱሌይማኒ ነበሩ ተብሏል።
ጀነራሉ የሚመሩት ኃይል በሶሪያ ግጭት ውስጥ ተሳትፎ እንዳለው አምኗል። ለፕሬዝደንት በሽር አል-አሳድ ታማኝ ለሆኑ ወታደሮች የጦር ምክር ይሰጣል። እንዲሁም ለበሽር አል-አሳድ ታማኝ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሺዓ ሙስሊሞችን አስታጥቋል። በኢራቅ ደግሞ አይኤስን እየታገሉ ለሚገኙ ለሺዓ ሙስሊም ሚሊሻዎች ድጋፍ ያደርጋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የተከሰቱት ግጭቶች ጀነራሉ ኢራን ውስጥ እጅግ ዝነኛ ሰው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ጀነራል ሱሊማኒ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የኢራን ከፍተኛ የጦር ሽልማት ተቀብለዋል።
አሜሪካ በበኩሏ ጀነራሉ የሚመሩት የኩድስ ኃይል በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ አሜሪካን በጠላትነት በመፈረጅ በሽብር መናጥ ለሚፈልጉ ኃይሎች ፈንድ፣ ሥልጠና እና የጦር መሳሪያን ጨምሮ የቁስ ድጋፍ ያደርጋል ስትል ትወነጅላለች።
አሜሪካ እንደምትለው ከሆነ ይህ የኩድስ ኃይል ድጋፍ ከሚያደርግላቸው ኃይሎች መካከል፤ የሌባኖሱ ሄዝቦላ እንዲሁም የፍልስጤሙ እስላማዊ ጅሃድ ተጠቃሽ ናቸው።
የቀድሞ የሲአይኤ አለቃ የአሁኑ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ የኢራንን አብዮታዊ ጥበቃ እና ኩድስ ኃይሉን "የሽብር ቡድን" ሲሉ ከወራት በፊት ፈርጀውት ነበር።














