ኢራን ፡ አሜሪካ በሚሊዮኖች ዶላር የሚገመት የኢራን ነዳጅ በቁጥጥር ስር አዋለች

የፎቶው ባለመብት, US JUSTICE DEPARTMENT
አሜሪካ ወደ ቬኒዙዌላ እየሄዱ የነበሩ አራት የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሏልን አስታውቃለች። ነዳጁ እስከዛሬ ከተያዙት በሙሉ ከፍተኛ መጠን ያለው መሆኑም ተገልጿል።
1.1 ሚሊዮን በርሜል የሚሆነው ይህ ነዳጅ ሊያዝ የቻለው ከሌሎች አገራትም በተገኘ ድጋፍ እንደሆነ የአሜሪካ ፍትህ መስሪኣ ቤት አስታውቋል።
አሜሪካ እንደምትለው በመርከብ ተጫኖ ወደ ቬንዙዌላ ሲገጓጓዝ የነበረው ነዳጅ በአገሪቱ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ የጣሰ ነው።
በቬንዙዌላ የኢራን አምባሳደር በበኩላቸው የተያዙት መርከቦች ባለቤት ኢራን አለመሆኗን ገልጸዋል።
አሜሪካ ባለፍነው ወር ከኢራን የሚመጡ መርከቦችን በተመለከተ ክስ ማቅረቧን ተከትሎ ነው አንድ ዳኛ የነዳጅ መርከቦቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ትዕዛዛቸውን ያስተላለፉት።
የአሜሪካ ፍትህ መስሪያ ቤት አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ ''ነዳጁን የመያዝ ሥራው በስኬት ተጠናቋል'' በማለት በኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሚንቀሳቀስ በሚሊየኖች የሚቆጠር መጠን ነዳጅ ማያዙን አስታውቋል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ የኢራን ዋነኛ ጦር ክፍል ሲሆን አሜሪካ ግን የውጭ አገር የሽብር ቡድን በማለት ፈርጃዋለች።
''የተያዘው ነዳጅ አሁን በአሜሪካ ቁጥጥር ስር ነው'' ብሏል የፍትህ መስሪያ ቤቱ አራቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች መቼና የት እንደተያዙ ምንም ተጨማሪ መረጃ አልሰጠም።
የአሜሪካ ፍትህ መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው መርከቦቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የኢራን የባሕር ኃይል ነዳጁን ለማስመለስ በማሰብ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካና በስህተት ሌላ መርከብ ለመቆጣጠር መሞከራቸውን ገልጿል።
አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ለአሶሼየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ሲናገሩ ነዳጁን ለመያዝ መታደራዊ ኃይል እንደተጠቀሙና መርከቦቹ ግን በቁጥጥር ስር እንዳልዋሉ አብራርተዋል።
በቬንዙዌላ የኢራን አምባሳደር ሆጃት ሶልታኒ ሁኔታውን ''ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ'' ነው ብለውታል።
አክለውም ''ይህ አሁንም ተጨማሪ ውሸት ነው፤ ኢራን ላይ ሥነ ልቦናዊ ጫና ለማድረስ ሆን ተብሎ በአሜሪካ የተቀነባበረ የጦርነት ፕሮፓጋንዳ ነው'' ብለዋል በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት።
አሜሪካ በኢራንና ቬንዝዌላ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን የጣለች ሲሆን ይህም ነዳጅ ወደ ውጭ አገራት መላክንም ይጨምራል። በተጨማሪም አሜሪካ የቬንዝዌላውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ከስልጣን ማባረርና በኢራን የመሪዎችን ላይም ጫና መፍጠር ትፈልጋለች።
















