ኢራን ለሲአይኤ መረጃ አቀብሏል ያለችውን ግለሰብ በሞት ቀጣች

ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉ አገራት ግዙፍ የሚሳኤ ክምችት ያለባት አገር ናት።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉ አገራት ግዙፍ የሚሳኤል ክምችት ያለባት አገር ናት።

ኢራን የቀድሞ የመከላከያ ሚንስቴር ሠራተኛዋን ለአሜሪካ ምረጃ አቀብሏል በሚል ክስ በሞት መቅጣቷን አስታወቀች።

ሬዛ አስጋሪ የተባለው ግለሰብ የሞት ብይኑ የተፈጸመበት ባሳለፍነው ሳምንት መሆኑን የፍርድ ቤት ቃል አቀባይ ጎላምሁሴን ኢሰማኢሊ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ እንዳሉ የሞት ብይኑ የተፈጸመበት ሬዛ አስጋሪ የኢራንን የሚሳኤል ፕሮግራም ዝርዝር መረጃ ለአሜሪካ የስላል ተቋም (ሲአይኤ) እአአ 2016 ላይ አሳልፎ ሰጥቷል ተብሎ ነው።

አስጋሪ መረጃውን ሰጠ የተባለው ከኢራን መከላከያ ሚንስቴር ሠራተኝነት በጡረታ ከተገለለ በኋላ ነው። ቃል አባዩ አስጋሪ መቼ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ፣ የፍርድ ሂደቱ መቼ እንደተከናወነና ብይኑ ተግባራዊ የሆነው መቼ እንደሆነ ዝርዝሩን ከመናገር ተቆጥበዋል።

ቃል አቀባዩ ጎላምሁሴን ኢሰማኢሊ የሞት ቅጣቱ ስለተፈጸመበት ግለሰብ የተናገሩት ስለ ሌላ ለውጪ ኃይሎች ሰልሏል ተብሎ ስለተከሰሰ ተጠርጣሪ በገለጹበት ወቅት ነበር።

ቃል አቀባዩ እንደተናገሩት መሐሙድ ሙሳቪ-ማጃድ የተባለ ሌላኛው ግለሰብ ለሲአይኤ እና ለእስራኤል መንግሥት የስለላ ድርጅት ሞሳድ መረጃ አሳልፎ ሰጥቷል ተብሎ የሞት ፍርድ እንደተላለፈበት ተናግረዋል።

መሐሙድ ሙሳቪ-ማጃድ ለሲአይኤ እና ሞሳድ አሳልፎ የሰጠው መረጃ በሶሪያ የኢራን ጦር እንቅስቃሴን በተመለከተ ነው ተብሏል።

የአሜሪካ ባለስልጣን አስጋሪ በኢራን መንግሥት የሞት ፍርድ ተፈጻሚ እንዲሆንበት መደረጉን ተከትሎ ያሉት ምንም ነገር የለም።

ከአንድ ዓመት በፊት የኢራን የደኅንነት ሚንስቴር የአገሪቱን የኒውክሌር እና ሌሎች ወታደራዊ ተቋማት ዝርዝር መረጃ ለሲአይኤ አሳልፈው ሰጥተዋል ያላቸውን 17 ሰዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ እንደነበረ ማሳወቁ ይታወሳል።

በወቅቱ ሚንሰቴር መስሪያ ቤቱ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል በስም ያልጠቀሳቸው የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው እንዳሉ አሳውቆ ነበር።

በተመሳሳይ ከአንድ ወር በፊት የቀድሞ የኢራን መከላከያ ሚንስቴር መስሪያ ቤት ሠራተኛ የነበረው ጃላል ሃጂዛቫር ለሲአይኤ ሰልሏ ተብሎ በሞት ተቀጥቷል። በወቅቱ ሃጂዛቫር በክፍያ ለሲአይኤ ሲሰልል መቆየቱን አምኗል ተብሎ ነበር።