በብሩንዲ ሙሽራው በደረሰበት የሞተር አደጋ ምክንያት ጥንዶቹ ሰርጋቸውን በሆስፒታል አደረጉ

በሰሜናዊቷ ብሩንዲ ኪሩንዶ ግዛት የሚኖሩ ሁለት ጥንዶች ሙሽራው ከቀናት በፊት በሞተር አደጋ ጉዳት ቢደርስበትም ሰርጋቸውን አንሰርዝም ማለታቸው ብዙዎችን አስደንቋል።
ቻርሎቴ ሙካንትዋሪና ጋቢን ንዳይዚጊየ የተባሉት ጥንዶችም የሰርጋቸውን ስነ ስርአት በሆስፒታል አከናውነዋል ተብሏል።
አደጋው ከደረሰ በኋላ ጓደኛው የአሁኑ ባለቤቱ ከጎኑ ያልጠፋች ሲሆን ህክምናውን እየተከታተለ ባለበትም ወቅት ሰርጋቸውን ፈፅመዋል።
ሰርጋቸውን የሚያስፈፅሙት ቄስ ሙሽሪትን ቀለል ያለ ልብስ እንድትለብስ ቢመክሯትም ነጭ ቬሎ ለብሳ እንደመጣች ተገልጿል።
"ይህችን የሰርጌን ቀን በጉጉት ስጠብቃት ነበር። በዚህች ቀን እንዲህ አይነት ችግር ማጋጠም ማለት ሰይጣን እየተፈታተነኝ እንደሆነ ነው የማስበው። ህይወቴን ያለዚች ቀን ማሰብም አልችልም" በማለት ቻርሎቴ ሊቢሲ ተናግራለች።
በርካታ የአካባቢው ሰዎች አደጋ ያልፈተናቸው ተጋቢዎችን ሰርግ ለመታደም ወደ ሆስፒታሉ እንደተመሙም ተገልጿል።
ሙሽራው ጋቢንም ሰርጉ መካሄድ አለበት በማለት በሃሳቧ በፀናችው ሙሽሪት ልቡ እንደተነካ የገለፀ ሲሆን በተለይም ሙሽሪት በአደጋው ምክንያት እንደገና ይራመድ አይራመድ ሳታውቅ መሆኑም አግራሞት መፍጠሩን አልደበቀም።
ሙሽራው ቃለ መሃላቸውን ሊፈፅሙ ሲሉ ለአጭር ጊዜ ቢገኝም ወዲያው ወደ ሆስፒታል አልጋው እንዲመለስ ተደርጓል ተብሏል።












