ኮሮናቫይረስ፡ ፈረንሳይ ለጤና ባለሙያዎቿ 9 ቢሊዮን ዶላር በማውጣት የደመወዝ ጭማሬ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንሳይ መንግሥት ለጤና ባለሙያዎቹ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር የደመወዝ ጭማሬ ለማድረግ ተስማማ። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ሲታገሉ ለነበሩት ለእነዚህ የጤና ባለሙያዎች ጭማሬው ታሪካዊ ነው ተብሏል።
ስምምነቱም በትናንትናው ዕለት ከሰራተኛ ማህበራቱ ጋር ተፈርሟል። ከሰባት ሳምንታት በኋላ የተደረሰ ስምምነትም እንደሆነ ተገልጿል።
በኮሮናቫይረስ ክፉኛ በተጠቃችው ፈረንሳይ የጤና ባለሙያዎች ወረርሽኙን ለመታገል ያደረጉት ቆራጥነትና ፅናት ከህዝቡ ዘንድ የጀግና አቀባበል አሰጥቷቸዋል።
ሆኖም ከዕውቅናው በተጨማሪ የደመወዝ ጭማሬና ለሆስፒታሎች የሚደረገው ድጎማ እንዲሻሻልም በመጥራት ከፍተኛ ተቃውሞን ሲያሰሙ ነበር።
አንዳንድ ሰልፈኞችም አካላዊ ርቀትን ባለመጠበቅ ቅጣት ተላልፎባቸዋል። በአውሮፓ ውስጥ በቫይረሱ ክፉኛ በተመታችው ፈረንሳይ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 30 ሺህ ዜጎቿንም አጥታለች።
መንግሥት ለጤና ባለሙያዎቹ በአማካኝ በየወሩ 220 ዶላር (8400 ብር) ደመወዝ ጭማሬ ለማድረግም ተስማምቷል።
ስምምነቱንም አዲሱ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን ካስቴክስ "ለአገራችን የጤና ስርአት ታሪካዊ ነው" በማለት አሞካሽተውታል።
"ከሁሉም በላይ ይሄ ለህይወታቸው ሳይሳሱ ወረርሽኙን ለታገሉት የጤና ባለሙያዎች እውቅና ነው" በማለትም በፊርማው ስነ ስርአት እለት ተናግረዋል።
የደመወዝ ጭማሬ ፓኬጁ የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ በእንክብካቤ ማዕከላት ለሚሰሩ ሰራተኞችና የድጋፍ ሰጪ አካላትን ያካትታል።
ከዚህም በተጨማሪ 570 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ደግሞ በህዝብ የጤና ተቋማት ለሚሰሩ ዶክተሮች ተቀማጭ ይሆናል።
የደመወዝ ጭማሬው የአገሪቱ ብሄራዊ ቀን ለሆነውና የጤና ባለሙያዎች ወረርሽኙን ለመግታት እያደረጉት ያለውን ትግል የሚዘክረውን የባስቲል ቀን በፊት መሆኑ ብዙዎችን አስደስቷል።
በዓሉ በዛሬው ቀን የሚከበር ሲሆን በመዲናዋ ፓሪስም ከ 1 ሺህ 400 የሚበልጡ ነርሶች፣ ዶክተሮችና እንክብካቤ ሰጪዎችም ይሳተፋሉ ተብሏል።














