በአፍሪካ ኮሮናቫይረስ እየተሰራጨ የሚገኘው በምን ያህል ፍጥነት ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከተቀረው ዓለም ጋር ሲነጻጸር ያነሰ ቢሆንም፤ በአንዳንድ አገሮች የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ አሳሳቢ ሆኗል።
በአህጉሪቱ 100,000 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙት በመቶ ቀን ነበር። ነገር ግን በቀጣዮቹ 18 ቀናት ቁጥሩ በእጥፍ ሲጨምር፣ በ20 ቀን ውስጥ ደግሞ 400,000 ደርሷል።
ቁጥሩ እየጨመረበት ያለው መንገድ በበሽታው ክፉኛ ከተጠቁ የዓለም ክፍሎች ጋር ተመሳሳይ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለውም፤ ወረርሽኙ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተሰራጭቷል።
ይህ ማለት ደግሞ ኮቪድ-19 ከያዘው ሰው ጋር ቀጥታ ንክኪ የሌለውም ሰው ለበሽታው ሊጋለጥ ይችላል ማለት ነው። ይህም የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ከባድ ያደርገዋል።
በአፍሪካ በከፍተኛ ሁኔታ የተጋለጡት የትኞቹ አገሮች ናቸው?
በግብፅ እና በደቡብ አፍሪካ በሽታው በስፋት ተሰራጭቷል። ግብፅ በቫይረሱ ሳቢያ በርካታ ሰዎች በማጣት ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት።
ደቡብ አፍሪካ እጅግ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣሉ አገሮች አንዷ ስትሆን፤ ግንቦት ላይ ገደቡ ሲላላ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
ናይጄሪያም አስጊ ሁኔታ ውስጥ ካሉ አገሮች አንዷ ናት። የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው ከሆነ በኮቪድ-19 ሳቢያ በሞቱ ሰዎች ቁጥር ከአህጉሪቱ ሁለተኛ ነች።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ሞሪታንያ ውስጥ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
በሌላ በኩል የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በአንጻራዊነት ጥቂት ህሙማን ነው ያስመዘገቡት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአፍሪካ ምን ያህል ሰዎች እየሞቱ ነው?
የአህጉሪቱ የጤና መዋቅር ደካማ ቢሆንም፤ የተመዘገበው የሞት መጠን ከሌሎች የዓለም ክፍሎች አንጻር ያነሰ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፤ ለዚህ ምክንያቱ አፍሪካ ውስጥ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ወጣቶች መሆናቸው ነው።
ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከ25 ዓመት በታች ሲሆኑ፤ ኮቪድ-19 በዋነኛነት የሚያጠቃው በእድሜ የገፉ ሰዎችን ነው።
ሌላው የሞት መጠን መለኪያ በበሽታው ከተያዙት መካከል ምን ያህሉ ሕይወታቸውን አጡ? የሚለው ነው። በዚህ መሠረት ከፍተኛ መጠን ያላቸው አምስት አገሮች ቻድ (8.5%)፣ አልጄሪያ (6.6%)፣ ኒጀር (6.2%)፣ ቡርኪና ፋሶ (5.5%) እና ማሊ (5.3%)ናቸው።
በጤናው ዘርፍ የተሰማራው አምሬፍ ኸልዝ አፍሪካ የተባለው የተራድኦ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ጊትሂንጂ ጊትሃይ እንደሚናገሩት፤ ከፍተኛ የሞት መጠን የሚያሳየው፤ ከተመዘገበውም በላይ ሰዎች በበሽታው እየተያዙ መሆኑን ነው። በተጨማሪም ምርመራ በስፋት እየተከናወነ አለመሆኑን ይጠቁማል።
አነስተኛ ሰው ከተመረመረ በበሽታው መያዛቸው የሚረጋገጠውም ጥቂት ሰዎች ይሆናሉ። የሞት መጠን ግን ይጨምራል።
በአፍሪካ ምን ያህል ምርመራ እየተከናወነ ነው?
አስር አገሮች በአህጉሪቱ ከተደረገው ምርመራ 80 በመቶውን ይሸፍናሉ። እነዚህም ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ጋና፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ሞሪሸስ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ሩዋንዳ ናቸው።
ሐምሌ ላይ ደቡብ አፍሪካ ከ1,000 ሰዎች 30 ስትመረምር፤ ዩናይትድ ኪንግደም 72፣ አሜሪካ ደግሞ 105 ሰዎች ነው የመረመሩት።
ናይጄሪያ በ1,000 ሰዎች የምርመራ መጠኗ 0.7 ሲሆን ጋና 10፣ ኬንያ ደግሞ ሦስት ሰዎች መርምረዋል።
በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ ጉዳዮች መምህር የሆኑት ቺልዶ ንዋንክዋር እንደተናገሩት፤ ቁጥሩ አጠቃላይ ወካይ እንደሆነ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ይላሉ።
የታንዛንያው ጆን ማጉፉሊ፤ የመመርመሪያ መሣሪያዎች ውጤት አስተማማኝ ስላልሆነ ከሚመዘገበው ውጤት ከፊሉን ብቻ ለሕዝብ እያስታወቁ ነበር።
በኢኳቶሪያን ጊኒ የዓለም ጤና ድርጅት ወኪል በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ቁጥር እያጋነኑ ነው ብላ ቁጥሩን ለተወሰነ ጊዜ ይፋ አለማድረጓ ይታወሳል።
በናይጄሪያዋ ካኖ ግዛት ሰኔ ላይ 1,000 ሰዎች ሞተው ነበር። ሆኖም ግን መንግሥት ምን ያህሉ በኮቪድ-19 እንደሞቱ አልገለጸም።















