ኮሮናቫይረስ፡ አሳሳቢው የኮቪድ-19 ምልክትን የማያሳዩ በሽታውን የሚያዛምቱ ሰዎች ነገር

ልክ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቀውስ ዓለምን ማስጨነቅ ሲጀምር ተመራማሪዎች ይበልጥ የሚያስፈራና የሚያሳስብ አንድ ለየት ያለ ነገር አስተውለው ነበር።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እንደ ሳል፣ ትኩሳት፣ የምግብ ጣዕምን መለየት አለመቻል የመሳሰሉ ምልክቶችን ሲያሳዩ ሌሎች ግን ከነጭራሹ በኮቪድ-19 ስለመያዛቸው የሚያመለክቱ ምንም አይነት ምልክቶችን አያሳዩም።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ምን ያህሎቹ ምንም አይነት ምልክት እንደማያሳዩ ማወቅና ወረርሽኙን እያባባሱ ያሉት እነሱ መሆናቸውን ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ነው።
ጥር 2019 ሲንጋፖር ውስጥ አንድ የሠርግ ሥነ ሥርዓትን ለመታደም የተሰበሰቡት ሰዎች ቫይረሱ በመላው ዓለም እንዲሰራጭ ምክንያት እንሆናለን ብለው አላሰቡም ነበር።
እሁድ ቀን ነበር፤ ሁሉም ታዳሚዎች እንደተለመደው የክት ልብሳቸውን ለብሰው ሙሽሪትና ሙሽራን ይጠባበቃሉ። እነዚህ ሰዎች ያላወቁት ግን ከመካከላቸው ከቻይና የመጡ ሁለት የ56 ዓመት ጥንዶች ቫይረሱ እንዳለባቸው ነው።
ሁሉም ቦታ ቦታቸውን ሲይዙ ጥንዶቹ ምንም አይነት በቫይረሱ የመያዝ ምልክትም ሆነ ህመም አልነበረባቸውም። በወቅቱ ሳልና ማስነጠስ ብቻ ነበር በብዙው ሰው ዘንድ እንደ ወረርሽኙ ምልክት ይታዩ የነበሩት።
የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ ሲጠናቀቅ ወዲያውኑ ቻይናውያኑ ጥንዶች ወደ ማረፊያቸው ተመለሱ። ነገር ግን በሦስተኛው ቀን ሚስትየው የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን ማሳየት ጀመረች፤ በሚቀጥለው ቀን ደግሞ ባለቤቷም ምልክቶቹን ማሳየት ጀመረ።
ማንም ያላስተዋለው ነገር እነዚህ ጥንዶች ኮሮናቫይረስ ከጀመረባት የቻይናዋ ዉሃን ከተማ መምጣታቸውን ነው።
በሚቀጥሉት ሳምንታት የሠርግ ሥነ ሥርዓቱን ከታደሙ ሰዎች መካከል ሦስት ሲንጋፑራውያን ኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው።
ሌላ ተመራማሪዎቹን ግራ ያጋባው ደግሞ በዚያኑ ቀን በተመሳሳይ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሌላ ሠርግ ላይ የታደሙ የ56 ዓመት ሲንጋፖራዊ ሴት ቫይረሱ ተገኘባቸው።
በወቅቱ ስለኮሮናቫይረስ የነበረው ግንዛቤና የዓለም ጤና ድርጀት ይሰጣቸው የነበሩት መረጃዎች ውስን ስለነበሩ ቫይረሱ እንዴት በዚህ ፍጥነት ሊዛመት ቻለ የሚለው ጥያቄ አስፈሪ ነበር።
ጉዳዩ ያሳሰባቸው ባለስልጣናት የሠርግ ሥነ ሥርዓቱን ሙሉ ሁኔታ ከቤተክርስቲያኒቱ ካሜራዎች ለመመልከት ወሰኑ። ያገኙት ነገርም አስደንጋጭ ነበር።
የ56 ዓመቷ ሴት ከሰዓታት በኋላ በተካሄደ ሠርግ ላይ ሲታደሙ የተቀመጡበት ወንበር ሁለቱ ከቻይና የመጡ ጥንዶት ተቀምጠውበት የነበረው ተመሳሳይ ወንበር ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምንም እንኳን ሁለቱ ቻይናውያን ጥንዶች የቫይረሱን ምልክቶች ባያሳዩም በሠርግ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከታደሙ ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች በአካባቢው የተገኙ ሰዎች ላይም ጭምር ቫይረሱን አስተላልፈዋል።
በወቅቱ ሲንጋፖር ቫይረሱን ለመቆጣጠር በወሰደችው እርምጃ አድናቆት ቢቸራትም ወዲያው ግን ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ መሆን ጀመሩ።
በዚህ ሠርጉ ላይ የታደሙት ሰዎች ላይ መሰረት ተደርጎ በተሰራ ጥናትም ኮሮናቫይረስ የያዘቸው ሰዎች በመጀመሪያዎቹ ከ24 እስከ 48 ሰዓታት ውስጥ ቫይረሱን የማሰራጨት እድላቸው በእጅጉ ከፍተኛ ነው።
እንደውም በዚህ ጊዜ የሚያስተላልፉበት መጠን ምልክቶቹን ማሳየት ከጀመሩ በኋላ ከሚያስተላልፉበት መጠን በእጅጉ ከፍ ያለ ነው።
መጀመሪያ ላይ የቻይና ባለስልጣናት ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው አይተላለፍም ቢሉም አሁን ግን በዚህ መንገድ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።
ሳይንቲስቶች እንደደረሱበትም በበሽታው የተያዘ እያንዳንዱ ሰው ቫይረሱን ከአንድ እስከ ሦስት ወደሚደርሱ ሰዎች ሊያዛምት ይችላል።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉትም በበሽታው የተያዙ ሰዎች የበሽታው ምልክቶችን ከማሳየታቸው በፊት አንስቶ ቫይረሱን ወደ ሌሎች ማስተላላፍ ይችላሉ።
በበሽታው በመያዝና ምልክቶቹ መታየት በሚጀምርበት ጊዜ ያለው የመራቢያ ጊዜ ከአንድ ቀን አስከ ሁለት ሳምንት የሚወስድ ነው።
ለንደን በሚገኘው ኢምፔሪያል ኮሌጅ ውስጥ የተላላፊ በሽታዎች ክፍል ውስጥ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ዌንዲ ባርክሌይ እንደሚሉት በሳምባ ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች ምንም ምልክት ሳያሳዩ ከሰው ወደ ሰው የመተላላፍ ባህሪይ አላቸው።
ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ይመስላል በርካታ የዓለማችን አገራት ዜጎች ወደ ውጪ ሲወጡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ማድረግ የሚያስገድዱ ሕጎችን ያስቀመጡት።


















