በኮሮናቫይረስ ምክንያት በማያቋርጥ የጫጉላ ሽርሽር ላይ ያሉት ሙሽሮች

ካሊድና ፔሪ የጫጉላ ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ወደ ሜክሲኮ ያቀኑት መጋቢት ላይ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Family handout

የምስሉ መግለጫ, ካሊድና ፔሪ የጫጉላ ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ወደ ሜክሲኮ ያቀኑት መጋቢት ላይ ነበር

ትውውቃቸው ከስምንት ዓመታት በፊት ነበር፤ የ36 ዓመቱ ካሊድና የ35 አመቷ ፔሪ።

ለስምንት ዓመታት በጓደኝነት ከቆዩ በኋላ ቤተሰብ ዘመድ ወዳጅ በተሰበሰበት፣ በግብጿ መዲና ካይሮ ድል ባለ ድግስ ተጋቡ።

ሠርጋቸው የካቲት 27/2012 ዓ.ም የነበረ ሲሆን ከጥቂት ቀናት በኋላም ለጫጉላ ሽርሽራቸው ወደ ሜክሲኮዋ ከተማ አቀኑ።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ገና እየጀመረ የነበረበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መቀመጫቸውን ዱባይ ያደረጉት ሙሽሮች ልክ እንደ በርካቶች ስጋትም አልገባቸውም።

ምንም እንኳን ሙሽሮቹ የተጨናነቁ ስፍራዎችን ቢያስወግዱም ቫይረሱ በሌሎች አገራት ላይ ባለመዛመቱ ጉዞዎች ሊሰረዙ ይችላሉ የሚለው ሃሳብ በጭራሽ ያላለሙት ጉዳይ ነው።

የጫጉላ ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ቤታቸው ለመመለስም መጋቢት አስር ቀን በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ አየር መንገድ ቲኬታቸውን ቆረጡ።

የገዙትም ቲኬት መሸጋገሪያቸው በቱርክ፣ ኢስታንቡል ነበር። "አውሮፕላን ውስጥ ሆነን ኢንተርኔት ማግኘት ችለን ነበር። ከቤተሰቦቻችንም መልዕከት ማግኘት ቻልን። ዱባይ እንዴት ልትደርሱ ነው? የውጭ አገር ዜጎች ወደ ዱባይ እንዳይገቡ መመሪያ ወጥቷል" የሚሉ ዜናዎችን ፔሪ ማንበቧን ታስታውሳለች።

ሆኖም በአውሮፕላን ውስጥ እያሉ ወደ ዱባይ መግባት እንደሚችሉ አስበው ነበር። ነገር ግን ኢስታንቡል ላይ ወደ ዱባይ ለመሳፈር ሲሞክሩ፤ መሳፈር እንደማይችሉ ተነገራቸው።

ልክ ከሜክሲኮ እንደተነሱ ነው ዱባይ መመሪያውን መተግበር የጀመረችው። በቱርክ ያለው የጉዞ ክልከላ ሁሉንም ዕቅድ አጨናገፈባቸው።

በአየር ማረፊያውም ለሁለት ቀናት ያህል ለማደር ተገደዱ። ቱርክ ያረፉት ለመሸጋገሪያ በመሆኑም ህጋዊ የሆነ የይለፍ ወረቀት (ቦርዲንግ ባስ) አልነበራቸውም። የመፀዳጃ ቤት ወረቀቶች፣ ልብሶችን መሸመት እንዲሁም ሻንጣቸውንም ማግኘት አልቻሉም።

ካሊድ በአየር ማረፊያ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Peri

ከዱባይ በተጨማሪ አማራጭ ብለው ያሰቧትም ግብጽም ማንኛውንም ጉዞ ማገዷን ተከትሎ፤ ሌላ እቅድ ማሰብ ነበረባቸው።

ስለዚህም ግብጻውያንን ያለ ቪዛ የሚያስገቡ አገራትን በጉግል በኩል መፈለግ፤ ይሄ ብቻ አይደለም በረራስ አላቸው ወይ የሚለውንም ማጣራት እንደነበረባቸው ፔሪ ታስረዳለች።

አማራጩም አንድ ብቻ ነበር! የማልዴቪስ ደሴት።

በህንድ ውቅያኖስ ተከበበው፣ በነጭ አሸዋና፣ አይንን በሚስብ የመሬት አቀማመጣቸው የማልዴቪስ ደሴቶች በዓለም ላይ ከሚያስደንቁና ልብን ከሚሰርቁ ውብ የተፈጥሮ ቦታዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

ካሊድና ፔሪ የጫጉላ ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ሜክሲኮን ከመምረጣቸው በፊት የማልዴቪስ ደሴቶችምም አስበዋቸው ነበር።

በዚህ ወቅት ግን የተፈጥሮ ውበትን የታደለው የውቅያኖስ ዳርቻ ወይም ደሴቶቹ ላይ መዝናናት መቻላቸው አይደለም የፈለጉት ትንሽ ምቾትን ብቻ ነው።

ለሁለት ቀናትም ያህል በአየር ማረፊያ ወንበሮች ላይ ሲያድሩ ስለነበርም ትንሽ እፎይታን ፈጠረላቸው።

"ማልዴቪስ እንደደረስን ደስታችንን መቆጣጠር አልቻልንም። በደስታም ተያየን ቢያንስ ከአየር ማረፊያ ወንበሮች ላይ መተኛትን ተገላግለን በአልጋ ላይ መተኛት መቻላችን ትልቅ ነገር ነው" በማለት የቴሌኮም ኢንጅነር የሆነው ካሊድ ይናገራል።

ከዚህም በተጨማሪ ሻንጣቸውን ማግኘታቸው ጭንቀታቸውን ቀለል አደረገላቸው። ሆኖም ችግሮቻቸው በሙሉ አልተቀረፉም።

"ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ጫና ሊደርስብን እንደሚችልም ማሰቡ በራሱ የራስ ምታት ነው የሆነብን፤ እዚህ ሆነን ሥራችንን መስራት አንችልም። ላፕቶፕም አላመጣንም" ትላለች ሚዲያ ውስጥ የምትሰራው ፔሪ "በጫጉላ ሽርሽር ላይስ ማን እሰራለሁ ብሎ አስቦ ላፕቶፕ ይይዛል?" በማለት ትጠይቃለች

ካሊድ ከሪዞርቱ ሰራተኞች ጋር

የፎቶው ባለመብት, Khalid

ባልና ሚስቱ ደሴቶቹ ላይ የሚያርፉበት ሪዞርትም ሲደርሱ የተወሰኑ እንግዶች ብቻ የነበሩ ሲሆን፤ እነሱም ወደ የአገራቸው ሊመለሱ ጥቂት ቀናት ብቻ የቀራቸው ነበሩ።

በርካታዎቹ እንግዶች በጥቂት ቀናት ውስጥ ሆቴሉን ለቀው ወደየአገራቸው ሲመለሱ፤ ሪዞርቱ ሊዘጋ እንደሆነ ለባልና ሚስቱ ተነገራቸው።

እንደገና ወደ ሌላ ደሴት፣ ሌላ ሆቴል ቢይዙም በተመሳሳይ ይሄኛውም ሆቴል ተዘጋ።

ችግራቸውንም የተረዳው የማልዴቪስ መንግሥት ተባብሯቸው ኦልሁቬሊ በምትባል ደሴት ላይ በምትገኝ ሪዞርት ውስጥ ነው ያሉት።

ባለስልጣናቱ ሪዞርቱ እንዲከፈት ከማድረግ በተጨማሪ የሚያርፉበትንም ዋጋ ስለቀነሰላቸው ሙሽሮቹ ባለስልጣናቱ እያደረጉላቸው ያለውን ትብብር ከልብም አመስግነዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሆቴሉ ሠራተኞችም እየተንከባከቧቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

"በተቻለ መጠን ሁሉም የሆቴሉ ሠራተኞች የተሻለ ጊዜ እንዲኖረን ይጥራሉ። ማታ ማታም ሙዚቃ ያጫውቱልናል፤ ሁልጊዜም ዲጄ አለ። አንዳንድ ጊዜም ሙዚቃ እየተጫወተ ማንም የሚደንስ ስለሌለ ትንሽ እንሳቀቃለን" በማለት ካሊድ ይናገራል።

በሪዞርቱ ሰባ ያህል የጫጉላ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ እንግዶች ቢኖሩም ልዩነቱ ፔሪ እንደምትለው " እነሱ የማልዴቪስ ደሴትን ለጫጉላ ሽርሽራቸው መርጠውት ነው። እኛ ግን አልመረጥነውም" ብላለች።

በአጠቃላይ በማልዴቪስ 300 ቱሪስቶች የሚገኙ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ደሴቷ አዳዲስ እንግዶች እንዳይገቡ ከልክላለች።

ምንም እንኳን የማልዴቪስ ደሴት ውብ ቦታ ቢሆንም፤ ተገደው ቢመጡበትም ከዚህ በባሰ ሁኔታ ሰዎች አማራጭ አጥተው የከፋ ቦታም ማሳለፍ እንዳለ ይረዱታል።

ሆኖም ማር ሲበዛም ይመራል እንደሚባለው በአሁኑ ወቅት ዋነኛው ምኞታቸው የጫጉላ ሽርሽራቸው ተጠናቆ ወደ ዱባይ መመለስ ነው።

ካሊድ በማልዴቪስ ደሴት

የፎቶው ባለመብት, Peri

በማልዴቪስ የውቅያኖስ ዳርቻው የተዝናኑት ለጥቂት ቀናት ብቻ ነው። ምክንያቱም ወቅቱ የሞንሱን አውሎ ንፋስ የሚነፍስበት በመሆኑ ኃይለኛ ዝናብ ይዘንባል። ከዚህም በተጨማሪ የረመዳን ፆምንም ለአንድ ወር ያህል እየፆሙ ነበር።

በተቻለ መጠን ወደ ሥራም ለመመለስ ቢሞክሩም የኢንተርኔቱ ደካማ መሆን ስብሰባዎችን እንዳይታደሙ አግዷቸዋል ።

ወደ መኖሪያ ቤታቸው መመለስም ቀላል አይደለም። ዱባይ መኖሪያቸውም ብትሆንም የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ዜጎች አይደሉም። ወደ ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራትም መመለስ አልቻሉም።

ምናልባት ማድረግ ይችሉ የነበረው ግብጽ ዜጎቿን ተመለሱ በምትልበት ወቅት ተመልሰው አስራ አራት ቀናትን በመንግሥት ለይቶ ማቆያ አሳልፈው አገራቸው መቀመጥ ነው። ነገር ግን ቤታቸው ዱባይ በመሆኑ ግብጽስ ረዥም ጊዜ የሚያስቆያቸው ጉዳይ የለም።

የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ባለስልጣናት ጋር በመደወልና እንደእነሱና መሰል አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ነዋሪዎችን ችግር እንዲፈቱም እየተማፀኑ ነው።

በረራዎች የማይገኙም ከሆነ በመንግሥታዊ መመላለሻዎችም እንዲጓዙ ፈቃድ የጠየቁ ሲሆን ምላሽም በመጠበቅ ላይ ናቸው።

"አየር መንገዱ ሥራ የሚጀምርበትን ቀን ማራዘሙን ዜና ስንሰማ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንገባለን። የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን፣ ሆቴልም ይሁን ቤታችን ለይቶ ማቆያ ውስጥ ግቡ ካሉን እንገባለን" በማለት ፔሪ ተናግራለች።

ካሊድና ፔሪ በሜክሲኮ

የፎቶው ባለመብት, Khalid and Peri

ለሁለት ወራት ያህል በሆቴል ውስጥ ያሉት ሙሽሮች ወጪያቸው እየናረ እንደሆነ ቢገባቸውም "ቤታችን እስከምንመለስ ድረስ ወጪያችንን ላንደምር ተስማምተናል። መቼ እንደምንመለስም አናውቅም" ብላለች።

ምንም እንኳን ከእነሱ በከፋ ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ሰዎች እንዳሉ ቢረዱም፤ ነገር ግን ጠብቀውት የነበረው አጠር ያለው የጫጉላ ጊዜ መራዘሙ እንዳሰላቻቸው አልደበቁም።

"በሪዞርቱ ውስጥ ያሉ እንግዶች በሙሉ ሄደው እኛ ሁልጊዜም የመጨረሻ ነን። ሠራተኞቹም ቻው በማለት እጃቸውን እንዳውለበለቡልን ነው። እነሱም ያሳዝናሉ። ሁለት ጊዜ እንዲህ አይነት አጋጣሚ አጋጥሞናል" የሚለው ካሊድ "እንደዚህ አይነት ቦታዎች በበርካታ ሰዎች እና በደስታ ሊሞላ ይገባ ነበር ሁኔታው ግን እንደዛ አይደለም" ብሏል።

አክሎም "ማልዴቪስ ደሴቶች ላይ መውጪያ እንዳጣን ለምናውቃቸው ሰዎች ስንናገር ብዙዎች ከት ብለው ይስቃሉ። 'ምናለበት እንደናንተ በሆንኩ ደስ የሚል ቦታ ነው' የሚሉም ብዙዎች ናቸው" የምትለው ፔሪ " እንደሚታሰበው ቀላልም አይደለም። ደስተኞችም አይደለንም። በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ላይ ነን፤ ከቤተሰባችን ጋር መሆን ያስደስተናል። በአሁኑ ሰዓት እሱን ለማግኘት የማልከፍለው ነገር የለም" ብላለች ፔሪ።

ኮሮና
Banner