በብራዚል የሳኦ ፖሎ ፖሊስ አንዲት ሴት አንገት ላይ ቆሞ በመታየቱ ቁጣ ተቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በብራዚል ሳኦፖሎ ፖሊስ የአንዲት ጥቁር ሴት አንገት ላይ ቆሞ የሚያሳይ ምሰል በአገሪቱ ቴሌቪዥን ከተላለፈ በኋላ ሁለት ፖሊሶች በወንጀል ሊጠየቁ መሆኑ ተገልጿል።
ግለሰቧ እድሜዋ በሰላሳዎቹ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን አንዲት አነስተኛ ግሮሰሪ እንዳላትና ከመጠጥ ቤቷ ውስጥ ተጎትታ ወጥታ እጆቿ በካቴና እንደታሰሩ በመንገድ ላይ መጎተቷ ተገልጿል።
ይህ ክስተት በግንቦት ወር መፈፀሙ የተገለፀ ሲሆን የዓይን ምስክር የሆነ ሰው በስልኩ መቅረፁ ታውቋል።
የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ዶሪያ እንዲህ አይነት የመብት ጥሰትን እንደማይታገሱ ገልጸው፣ ግለሰቧን በመያዝና በማንገላታት የተሳተፉ ሁለቱም ፖሊሶች ከስራቸው መሰናበታቸውን አስታውቀዋል።
የፖሊሶቹ ማንነት እስካሁን ይፋ አልተደረገም።
አገረ ገዢው አክለውም በሳኦ ፖሎ 2ሺህ ፖሊሶች አካላቸው ላይ ካሜራ ተገጥሞላቸው ለስራ እንደሚሰማሩ ገልጸዋል።
ግለሰቧ በፖሊስ እንግልትና ስቃይ ሲደርስባት የሚያሳየው ምሰል የሳምንቱ መጨረሻ ላይ በፋንታስቲኮ ቴሌቪዥን ጣብያ ተላልፏል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ

ምስሉ በብራዚል ውስጥ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን ክስተቱን በአሜሪካ በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ጆርጅ ፍሎይድ ላይ ከደረሰው ጋር በማመሳሰል ንዴታቸውን ገልጸዋል።
ነጭ ፖሊስ ጆርጅ ፍሎይድ አንገት ላይ በመቆም መተንፈስ ከልክሎት ለሞት መዳረጉ ይታወሳል።
የፍሎይድ ሞት በአሜሪካ እና አውሮፓ ሰፊ ህዝባዊ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን በአንዳንድ ስፍራዎች ሰልፈኞች ከፖሊሶች ጋር ሲጋጩ ተስተውሏል።

















