ኢራን የኑክሌር ሳይንቲስቷን ግድያ እንደምትበቀል ዛተች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኢራኑ ፕሬዝደንት ሐሰን ሩሃኒ ለአገራቸው ዋነኛ የኑክሌር ሳይንቲስት ግድያ እስራኤልን ተጠያቂ በማድረግ፤ ግድያው የኢራንን የኑክሌር መረሃ ግብር ፍጥነት እንደማይቀንሰው ተናገሩ።
ፕሬስደንቱ ጨምረውም በሳይንቲስቱ ሞህሲን ፋክሪዛዴህ ግድያ የኢራን ጠላቶች ምን ያህል በጠለቀ "በተስፋ መቁረጥና በጥላቻ" ውስጥ እንዳሉ ያሳ ነው ብለዋል።
እስራኤል ከኢራን በኩል Iየቀረበባትን ክስ በተመለከተ ምላሽ ባትሰጥም፤ ቀደም ሲል ሞህሲን ፋክሪዛዴህ ኢራን በድብቅ ከምታካሂደው የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ ጀርባ አሉ ስትከስ ነበር።
ኢራን በዋነኛው የኑክሌር ሳይንቲስቷ ሞህሲን ፋክሪዛዴህ ላይ የተፈጸመውን ግድያ እንደምትበቀልም አሳውቃለች።
ፋክሪዛዴህ ትናንት አርብ በዋና ከተማዋ ቴህራን አቅራቢያ ባልታወቁ ሰዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት ሆስፒታል ተወስደው ነበር ህይወታቸው ያለፈው።
የኢራን ሐይማኖታዊ የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ ወታደራዊ አማካሪ ሆሴን ዲጋን እንዳሉት ግድያውን በፈጸሙት ላይ ኢራን "በመብረቃዊ ጥቃት" እንደምትበቀላቸው ተናግረዋል።
የምዕራባዊያን የስለላ ተቋማት እንደሚሉት ሳይንቲስቱ ፋክሪዛዴህ ኢራን በድብቅ እያካሄደች ነው ከሚሉት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ ፕሮግራም ጀርባ ያሉ ቁል ሰው ናቸው።
ነገር ግን ኢራን እያካሄደች ያለው የኑክሌር መረሃ ግብር ለሰላማዊ ዓላማ አገልግሎት የሚውል እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጻለች።
ግድያውን ተከትሎ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ "መንግሥታዊ የሽብር ተግባር" ያሉትን እንዲያወግዝ ጠይቀዋል።
"ሽብርተኞች ታዋቂውን ኢራናዊ ሳይንቲስት ዛሬ ገደሉት" ሲሉም ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
የሳይንቲስቱ መገደል የተሰማው ኢራን እያዳበረችው ያለው የዩራኒየም መጠን መጨመሩን በተመለከተ ስጋት እንዳለ መገለጹን ተከትሎ ነው። የዳበረ ዩራኒየም ለሰላማዊና ለወታደራዊ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ መረሃግብሮች ወሳኝ ግብአት መሆኑ ይታወቃል።
ሳይንቲስቱን መገደል ይፋ የሆነው የኢራን መከላከያ ሚኒስቴር ትናንት አርብ ባወጣው መግለጫ ነበር።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጠው መግለጫ ላይ "የታጠቁ ሽብርተኞች በሚኒስቴሩ ውስጥ ያለው የምርምርና ጠፈጠራ ድርጅት ኃላፊ የሆኑትን ሞህሲን ፋክሪዛዴህ ይጓዙበት የነበረው መኪና ላይ ጥቃት ፈጽመዋል" በማለት ገልጿል።
የሳይንቲስቱ ጠባቂዎች ከጥቃት ፈጻሚዎቹ ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውንና በዚህም መካከል "ሞህሲን ፋክሪዛዴህ በጠና ቆስለው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው" አብራርቷል።
የህክምና ባለሙያዎች የሳይንቲስቱን ህይወት ለማትረፍ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ህይወታቸው ማለፉን የመከላከያ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ላይ ይፋ አድርጓል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢራን አምባሳደር የሆኑት ማጂድ ታካት ራቫንቺ ግድያው ሆን ተብሎ በአካባቢው ቀውስ ለመፍጠር የተፈጸመና ግልጽ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው በማለት በግድያው ውስጥ የእስራኤል እጅ ስለመኖሩ የሚያመለክቱ ማስረጃዎች እንዳሉ ተናግረዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታኒያሁ ከሁለት ዓመት በፊት ስለኢራን የኑክሌር ፕሮግራም ማብራሪያ በሰጡበት ጊዜ የኑክሌር ሳይንቲስቱን ስም በተለይ ጠቅሰው ነበር።
ሆኖም ግን ግድያውን በተመለከተ አስካሁን ድረስ ከእስራኤል በኩል የተሰጠ ምንም አይነት አስተያየት የለም።














