አውስትራሊያ ሐሰተኛ ምስል በመለጠፉ ቻይና ይቅርታ ትጠይቀኝ አለች

የፎቶው ባለመብት, EPA
በቻይና መንግሥት የትዊተር ገጽ ላይ አንድ አውስትራሊያዊ ወታደር አፍጋኒስታናዊ ታዳጊን ሲገድል የሚያሳይ ነው የተባለ ሐሰተኛ ምስል በመለጠፉ ቻይና ይቅርታ እንድትጠይቅ አውስትራሊያ አሳሰበች።
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ስኮት ሞሪሰን በቴሌቭዥን ቀርበው "ቤጂንግ እንዲህ ያለ አስቀያሚ ምስል በመለጠፏ ልታፍር ይገባል" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ሁለቱ አገራት ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ ናቸው። ምስሉም ነገሮችን የሚያባብስ ነው ተብሏል።
ይህ ምስል የአውስትራሊያ ወታደሮች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ክስ የሚያቀርብ እንደሆነም ተገልጿል።
በያዝነው ወር መባቻ ላይ የወጣ ሪፖርት፤ እአአ ከ2009 እስከ 2013 ባሉት ዓመታት 25 አውስትራሊያውያን ወታደሮች 39 ንጹሀን የአፍጋን ዜጎችን ገድለዋል ብሏል።
የአውስትራሊያ መከላከያ ኃይል ሪፖርት ከፍተኛ ወቀሳ ያስከተለ ሲሆን፤ ፖሊስ ጉዳዮ ላይ ምርመራ ከፍቷል።
የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ሊያን ዛሆ፤ አውስትራሊያዊ ወታደር አንድ ጠቦት ያቀፈ ታዳጊ አጠገብ በደም የተነከረ ስለት ይዞ የሚያሳይ የተቀናበረ ምስል ለጥፈዋል ተብሏል።
የአውስትራሊያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፤ ምስሉ የአውስትራሊያ ወታደሮች ሁለት የአፍጋን ወጣቶችን በስለት ገድለዋል የሚለውን በመረጃ ያልተደገፈ ወሬ የተመረኮዘ ነው ብሏል።
ሆኖም ግን የተካሄደው ምርመራ ወሬውን የሚደግፍ አንዳችም መረጃ አላገኘም።
የቻይናው ቃል አቀባይ በትዊተር ገጽ ምስሉን የለጠፉት "የአፍጋን ንጹሀን ዜጎች እና እስረኞች በአውስትራሊያ ወታደሮች መገደላቸው ያስደነግጣል። ድርጊቱን እናወግዛለን። ተጠያቂ መሆን አለባቸው" ከሚል ጽሁፍ ጋር ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር ስኮት ሞሪሰን በበኩላቸው ትዊተር ላይ የተለጠፈውን ምስል እና ጽሁፍ "በጣም አስቀያሚ እና እጅግ የሚያበሳጭ። የቻይና መንግሥት በትዊቱ ሊሸማቀቅ ይገባል" ሲሉ ኮንነዋል።
አውስትራሊያ፤ ምስሉ "ሐሰተኛ" ስለሆነ ትዊተር ከመተግበሪያው ላይ እንዲሰርዘው ጠይቃለች።
















