አፍጋኒስታን ፡ "የአውስትራሊያ ወታደሮች 'ደም እንዲለምዱ' የአፍጋኒስታን እስረኞችን እንዲገድሉ ይደረግ ነበር" ሪፖርት

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአውስትራሊያ መከላከያ አካል የነበረው ልዩ ኃይል አፍጋኒስታን በነበረ ጊዜ ወታደሮቹ ደም እንዲለምዱ የአፍጋኒስታን እስረኞችን ተኩሰው እንዲገድሉ ያበረታታ እንደነበር አንድ ሪፖርት አጋለጠ።
በአውስትራሊያ መንግሥት ተቀባይነት ባገኘው በዚህ ሪፖርት ላይ ወታደሮች 39 አፍጋኒስታዊያንን በዚሁ መንገድ እንደገደሉ ምርመራው አመልክቷል።
አፍጋኒስታን ሰላም ለማስከበር ዘምቶ የነበረው የአውስትራሊያ መከላከያ ሠራዊት ይህንን የጦር ወንጀል መፈጸሙን አስረግጦ ለመናገር ላለፉት አራት ወራት ጉዳዩን ሲመረምር ቆይቷል።
የምርመራ ውጤቱም በመላው ዓለም በጉጉት ሲጠበቅ ነበር።
በትንሹ 19 የሚሆኑ የቀድሞና የአሁን ወታደሮች በዚህ የጦር ወንጀል በቀጥታ ሊጠየቁ ይችላሉ ተብሏል።
ይህ አሰቃቂ "የጦር ወንጀል" የተፈጸመው በጎሮጎሳውያኑ አቆጣጠር ከ2009 እስከ 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ነው።
በግፍ የተገደሉት ደግሞ የአፍጋን ገበሬዎች፣ ንጹሐንና እና አስረኞች ናቸው።
ይህ ዓመታትን የወሰደው የምርመራ ሪፖርትን የመሩትና ይፋ ያደረጉት ሜጀር ጄኔራል ጀስቲስ ፖል እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ጉዳዩ ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ግንኙነት የነበራቸው 400 ሰዎችን ቃለ ምልልስ አድርገዋል።
በመጨረሻ ያገኙት የምርመራ ውጤታቸው እንደሚያሳየው ከሆነ ጦሩ አፍጋኒስታን በቆየባቸው ወቅት ልምድ የሌላቸው ወጣት ወታደሮች ደም እንዲለምዱና ሰው የመግደል ድፍረትና ወኔ እንዲያገኙ ለማስቻል በእስር ላይ የነበሩ አፍጋኒስታዊያንን ተኩሰው እንዲገድሉ ይበረታቱ ነበር።
ይህን ድርጊትም በተደጋጋሚ አድርገውታል።
ከዚህ በተጨማሪ በግፍ የተገደሉ አፍጋኒስታዊያን በተለይም ገበሬዎች በውጊያ የሞቱ ለማስመሰል ሲባልም የጦር መሣሪያ የሚከማቹበትና የጦር አውድማ ላይ ወስዶ ሬሳቸውን የመጣል ተግባር ይፈጸም ነበር ይላል ሪፖርቱ።
ሰላማዊ በሆኑ ዜጎች ላይም ሰቅጣጭ የሚባል ግፍ ይፈጸም እንደነበር ተብራርቷል በሪፖርቱ።
በጥናቱ የመጀመርያ ምዕራፍ ተሳትፎ የነበራቸው ሳማንታ ክሮምቮትስ ለቢቢሲ ስለተፈጸመው ግፍ ሲናገሩ "ድርጊቱ ይፈጸም የነበረው በተደጋጋሚና ሆን ተብሎ ነበር" ብለዋል።
በዚህ ድርጊት ላይ ምናልባትም 25 የሚሆኑ የአውስትራሊያ ልዩ ኃይል አባላት በቀጥታ ተሳትፈውበታል።
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሪሰን ባለፈው ሳምንት ለዜጎቻቸው "አስቸጋሪና ለማመን የሚከብድ ሪፖርት" በዚህ ሳምንት ሊሰሙ እንደሚችሉ ከወዲሁ ጥቆማ ሰጥተው ነበር።
ሪፖርቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ጠ/ሚኒስትር ሞሪሰን ለአፍጋኑ ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒ ደውለው ይህ ሪፖርት ስላጋለጠው ሀቅና ስለተፈጸመው አሳፋሪ ተግባር "ጥልቅ ሐዘን" እንደተሰማቸው በስልክ ነግረዋቸዋል።
አፍጋኒስታን በሪፖርቱ ላይ እስካሁን ያለችው ነገር የለም።
ሞሪሰን ጥፋተኞቹ ላይ ክስ የሚመሰረት ልዩ መርማሪ ቡድን እንደሚቋቋም ይፋ አድርገዋል። ሆኖም ጥፋተኞቹ የእጃቸውን እስኪያገኙ ዓመታት ሊወስድ ይችላል ብለዋል የአውስትራሊያ ሚዲያዎች። የፍርድ ሒደቱም ቢሆን ሌላ በርካታ ዓመታትን እንደሚወስድ ይጠበቃል።
አውስትራሊያ በአሁኑ ሰዓት 400 የሚሆኑ ወታደሮቿ ከአሜሪካን ወታደሮች ጋር በመሆን በአፍጋኒስታን የሰላም ማስከበር ውስጥ ይገኛሉ።
በዚህ ዓመት መጀመርያ የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በአፍጋኒስታን የጦር ወንጀል ተፈጽሞ ከሆነ በሚል አሜሪካንና ሌሎች ጦራቸውን ያስገቡ አገራት ላይ ምርመራ መጀመሩ ይታወሳል።












