አውስትራሊያ ሽብር ጠንሳሽ ያለችውን አብዱል ናስርን ዜግነት ነጠቀች

የፎቶው ባለመብት, ABC News
አውስትራሊያ በአውሮፓውያኑ 2005 ተከታታይ የሽብር ጥቃቶችን በማቀናበር የተከሰሰውንና የአልጄሪያ ተወላጅ የሆነውን የእስልምና መምህር ዜግነት ነጠቀች፡፡
አብዱል ናስር ቤንብሪካ 15 ዓመት የተፈረደበት ሲሆን ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ሊለቀቅም ይችላል ተብሏል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፒተር ዱተን አውስትራሊያውያንን ለመጠበቅ ሲባል ዜግነቱን መሻሩ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
እርምጃው ቤንብሪካ በአውስትራሊያ እያለ ዜግነቱ የተነጠቀ የመጀመሪያ ግለሰብ ያደርገዋል፡፡
እንደ ኤቢሲ ዘገባ ከሆነ ጠበቃው በመንግስት ውሳኔ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
"በሀገራችን ላይ ከፍተኛ የአሸባሪነት ስጋት እየፈጠረ ያለ ግለሰብ ከሆነ አውስትራሊያውያንን ለመጠበቅ ስንል በሃገሪቱ ሕግ መሠረት የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን" ሲሉ ዱተን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡
በአውስትራሊያ ሕግ መሠረት መንግሥት ዜግነነት መንጠቅ የሚችለው ግለሰቦች አገር አልባ እንዳይሆኑ ተረጋግጦ ሁለት ዜግነት ያላቸው ከሆነ ብቻ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት የአውስትራሊያ ብሄራዊ የደህንነት ድርጅት አሲዮ በዚህ የመንግስት ስልጣን ላይ ስጋቶች እንዳሉት አስታውቋል። "ያልታሰበ ወይም ያልተጠበቀ የደህንነት ስጋት ሊኖር ይችላል" በሚል ምከንያቱን አስቀምጧል፡፡
ከ1989 ጀምሮ በአውስትራሊያ የኖረው ቤንብሪካ እ.ኤ.አ. በ 2005 በቁጥጠር ስር የዋለ ሲሆን የሽብርተኛ ድርጅት አባል በመሆን እና ተግባሮቹን በመምራት ጥፋተኛ ተብሏል፡፡
ሌሎች ስድስት ሰዎች ደግሞ በየአመቱ ሜልበርን የሚደረገውንና ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን የሚታደሙበትን የአውስትራሊያ የእግር ኳስ ፍፃሜ ጨዋታን ጨምሮ በርካታ ጥቃቶችን ለመፈጸም ያቀደውን ቡድን በመቀላቀል ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡
የቤንብራካ ቅጣት ህዳር 5 ቀን የተጠናቀቀን የ12 ዓመታት ያለአመክሮ መታሰርን ያካትታል፡፡ የአውስትራሊያ መንግሥት የእስር ጊዜውን እንዲያራዝም ለቪክቶሪያ ግዛት ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመልክቷል፡፡
በእንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች በሽብር ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ሰዎች እስራታቸውን ከጨረሱ በኋላ ለሦስት ዓመታት ያህል በእስር ቤት ሊቆዩ ይችላሉ፡፡
የቪክቶሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቤንሪካን በእስር ቤት ለማቆየት እስካሁን ሁለት ጊዜያዊ የ28 ቀናት ማራዘሚያዎችን ፈቅዷል፡፡
የቤንብሪካ ጠበቆች እየቀጠለ ባለው እስር ላይ ይግባኝ ጠይቀዋል፡፡












