አል ሻባብ ፡ በሽብር የተከሰሰው የአልሸባብ አባል እስር ቤት ውስጥ ራሱን አጠፋ

ራሺድ ቻርለስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ራሺድ ቻርለስ

ከአምስት ዓመት በፊት በምሥራቃዊ ኬንያ ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ላይ በተፈጸመን የሽብር ጥቃት ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበረው የተባለው ግለሰብ እስር ቤት ውስጥ እራሱን አጠፋ።

በፈረንጆች 2015 ዓ ም ለ148 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ጥቃት በማቀናበር የተከሰሰው ታንዛኒያዊ ራሺድ ቻርለስ ነው ራሱን ያጠፋው።

የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ፖሊስና የእስር ቤት ኃላፊዎችን ጠቅሰው እንደዘገቡት በጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ለአራት ቀናት በቆየ የዕገታና የግድያ ጥቃት ውስጥ እጁ አለበት የሚባለው ይህ ተከሳሽ ራሱን ያጠፋው እስር ቤት ውስጥ ነው።

ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ላይ ጥቃት ካደረሱት ውስጥ አራቱ ቀንደኛ አቀናባሪዎች በጥቃቱ ወቅት መገደላቸው ተነግሯል።

ራሱን አጠፋ የተባለው ይህ ታንዛኒያዊው ቻርለስና ሁለት ሌሎች ግብረ አበሮቹ ባለፈው ዓመት ነበር ክስ የተመሰረተባቸው። የአልሸባብ አባላት እንደነበሩም ፖሊስ መግለጹ ይታወሳል።

ሟች ራሺድ ቻርለስ እድሜ ልክ ፍርደኛ ነበር። ራሱን ከማጥፋቱ በፊት ቻርለስ የአእምሮ ጤና መቃወስ ገጥሞት ሐኪም ይጎበኘው እንደነበር የኬንያ ጋዜጦች ጽፈዋል።

ዴይሊ ኔሽን በበኩሉ ፍርደኛው ራሱን ያጠፋው የብርድ ልብስ ቁራጭ ገምዶ ራሱን በመስቀል ነው።

ኬንያ በተደጋጋሚ የአልሸባብ ጥቃቶች ሰለባ ሆናለች። የ2015ቱ የጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ጥቃትም በርካታ ተማሪዎችን ለሞት የዳረገ ነበር።

አልሸባብ እንደሚለው ኬንያ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ከላከች ጀምሮ ጠላት አገር አድርጎ እንደቆጠራትና ጥቃቱንም ወደፊት እንደሚገፋበት ዝቷል።