ኮሮናቫይረስ፡ ጳጳሳቷን በኮቪድ-19 እያጣች ያለችው የሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን

ምእመናን የፓትርያርኩን አስከሬን ሲሰናበቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደ ሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳትና ጫና ያሳረፈባቸው የእምነት ተቋማት በጣም ጥቂት ናቸው።

በባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ በሰርቢያና ሞንቴኔግሮ የሚገኙ የቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ ኃላፊዎችን በኮሮናቫይረስ አጥታለች።

የቤተክርስቲያኗ ኃላፊዎች ከኮሮናቫይረስ መከሰት በኋላ በተለመደው መንገድ የአምልኮና ሌሎች አገልግሎቶችን በመቀጠላቸው ለወረርሽኙ መዛመትና ለሞቱ ምክንያት እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ።

ባለፉት ወራትም በቤተ ክርስቲያኗ የተከሰተው ተከታታይ ሞት አስደንጋጭ ሆኗል።

  • ባለፈው ወር በሞንቴኔግሮ የሚገኙ ኤጲስ ቆጶስ አምፊሎሂጄ ራዶቪች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ህይወታቸው አለፈ።
  • በመቀጠልም በኤጲስ ቆጶሱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት ፓትርያርክ ኢሪኔጅ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ህይወታቸው አለፈ።
  • ባለፈው ሳምንት እንዲሁ ሌላኛው ኤጲስ ቆጶስ ዴቪድም በፓትርያርኩ የቀብር ሥነ ሥርዓት መገኘታቸውንም ተከትሎ ለሁለተኛ ጊዜ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል።
  • የኤጲስ ቆጶስ አምፊሎሂጄ ራዶቪች ተከታይ ጆዋንኪጄ በኮሮናቫይረስ በጠና ታመው የየቀን ተግባራቸውንም ማከናወን አልቻሉም ተብሏል።

የቤተ ክርስቲያኗ አመራሮች በኮሮናቫይረስ የታመሙም ሆነ የሞቱ ቢኖሩም በአሁኑ ወቅት ቤተክርስቲያኗ በአብዛኛው ሰርቢያውያን ዘንድ የህይወታቸው ማዕከል ናት።

በሰርቢያ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የማስተማር ሥራውን በወረርሽኙ ምክንያት በበይነ መረብ እንዲያደርጉ መመሪያ ቢወጣም ቤተክርስቲያኗ የቁርባን ሥርዓቷን አልተወችም።

የአገሪቱ መንግሥት ወረርሽኙን ለመቆታጠር ከአምስት በላይ ሰዎች በአንድ ቦታ ላይ እንዳይሰባሰቡ ያስተላለፈውን ትእዛዝ በመተላለፍ ቤተ ክርስቲያኗ የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ማካሄዷን ቀጥላለች።

"ምንም እንኳን የምዕመናን ቁጥር በተወሰነ መልኩ መቀነስ ቢያሳይም አሁንም ቢሆን በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያኖች የሚደረገው የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት አልተስተጓጎለም፤ በየጊዜው ይደረጋል" በማለት የእምነት ጉዳዮች ተንታኝ ዜልጅኮ ኢንጃክ ይናገራሉ።

"በሰርቢያውያን ዘንድ ቤተ ክርስቲያኗ ትልቅ ክብር አላት። ከአገሪቷም ሆነ ከየትኛው ብሔራዊ ተቋማት በበለጠ ትልቅ ክብር አላት" ይላሉ ተንታኙ።

"በባልካን አገራትም ሆነ በምሥራቅ አውሮፓ የአስተዳደር ሥርዓት፣ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች፣ ርዕዮተ ዓለማትም ሆነ መንግሥት በተደጋጋሚ ቢቀያየርም ሕዝቡ በፖለቲካውም ሆነ በምጣኔ ሀብቱ ይህ ነው የሚባል ማሻሻያ አላሳየም። ለሕዝቡ ቋሚና ዋነኛዋ ነገር ቤተ ክርስቲያኗ ናት" በማለትም ያስረዳሉ።

ሆኖም ሁለት ትልልቅ ጳጳሳት የቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር ተያይዞ በቤተ ክርስቲያኗ አሰራር ላይ ትችቶች እየተሰሙ ነው።

በሞንቴግሮ መዲና ፖዶጎሪጋ ለቅስተኛ ምዕመናን የኤጲስ ቆጶስ አምፊሎሂጄ ራዶቪች አስከሬን እጅና ግንባር በመሳምና በመሳለም ሲሰናበቱ ነበር። ኤጲስ ቆጶሱ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ህይወታቸው ከማለፉ በፊት የእምነት ተግባራት "የአምላክ ክትባት" ናቸው ብለው ነበር።

ፓትርያርክ ኢሪነጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለቀስተኛ ምዕመናን በቤልግሬድ ሴይንት ሳቫ ቤተክርስቲያን የተካሄደውን ፓትርያርክ ኢሪነጅ የቀብር ሥነ ሥርዓት በርቀት እንዲከታተሉት ተደርገዋል።

ሆኖም ከቀብራቸው በፊት በነበረው የፓትርያርኩ የስንብት ሥነ ሥርዓት ላይ መመሪያዎች አልተከበሩም ተብሏል፤ የእምነቱ ተከታዮች የሬሳ ሳጥኑ ላይ የተገጠመውን መስታወት በመሳምና በመሳለምም ክብራቸውን ሲገልፁም ነበር።

በነበረውም የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ቁርባኑ ሲፈፀም የነበረው በአንድ ማንኪያ እንደሆነም ተገልጿል። ይህም ሁኔታ ለኮሮናቫይረስ የማጋለጥ እድሉም ከፍተኛ እንደሆነም የተላላፊ በሽታዎች አጥኚ ዶክተር ጁሪክ ለቢቢሲ ሰርቢያ ተናግረዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ ሥነ ሥርዓቷንና አሰራሯን እንድታሻሻልና ካልሆነም መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ባለሙያው ጥሪ አድርገዋል።

ዶክተር ጁሪክ በተጨማሪም ስብሰባዎች የታገዱበት መመሪያ ወጥቶ ባለበት ሰዓት በቤተ ክርስቲያኗ ለምን ይህ ተግባራዊ እንደማይሆን ይጠይቃሉ።

"ሕግና መመሪያዎች ለአንዳንዶች ተግባራዊ እንደማይደረግ መጥፎ መልዕክትን አስተላልፏል። ይህ ሁኔታ መመሪያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በተጠየቀው ሕዝብ ዘንድ አመኔታን ያሳጣልም" ይላሉ።

በሰርቢያ የሚገኝ ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከፓትርያርኩ የስንብት ፕሮግራም ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ የወረርሽኙ መዛመት ሊኖር ይችላል በሚልም የጤና ባለሙያዎች ዝግጅት እያደረጉ ነው።

በቅርብ ቀናት ውስጥ በሰርቢያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱንም በመጥቀስ ሁኔታው የሚያሳዝን ነው ተብሏል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ቩሲክ በበኩላቸው "ሁላችንም ቢሆን ኃላፊነታችን ካልተወጣን ለሚያሳዝን ከፍተኛ አደጋ መጋለጣችን አይቀርም" በማለት አስጠንቅቀዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት መቀጠሏን በማስመልከት ምንም ከማለት የተቆጠበች ቢሆንም የቤተ ክርስቲያኗ ኃላፊዎችም ሆኑ ቁሶች ከቅዱስ ሲኖዶሱ አቅጣጫ እንዲቀመጥላቸው እየጠበቁ መሆኑን አሳውቀዋል።

ምንም እንኳን የፓትርያርኩን ሞት እንዲሁም የኤጲስ ቆጶስ ዴቪድን ሆስፒታል መግባት ተከትሎ አገልግሎት የሚሰጡ ኃላፊዎች ቁጥር ቀንሷል። ነገር ግን አሁንም ዝርዝር አቅጣጫ ይሰጣል በሚል እየተጠበቀ ነው ያለው።

እስከዚያው ግን ቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርኳን ለማስታወስ የምታደርገውን የሰባት ቀን እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች ቀጥለዋል። በዚህ ሳምንት መጨረሻ አርብ በነበረው ስነ ስርአትም ቄሶች ጭምብል አላጠለቁም ነበር።