ኮሮናቫይረስ፡ የሰርቢያው ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ በኮቪድ-19 ሞቱ

የሰርቢያው ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ኢሪኔጅ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው አለፈ።

የ90 ዓመቱ ፓትርያርክ ከሳምንታት በፊት በኮሮናቫይረስ ለሞቱት የአንድ የቤተክርስቲያኒቱ ጳጳስ ሥርዓተ ቀብርን በርካቶች በተገኙበት ሲመሩ ነበር ተብሏል።

"እርስዎን በማወቄ ከፍተኛ ክብር ይሰማኛል። እንደ እርስዎ ያለ ሰው በሥጋ ቢለየንም በመንፈስ አይለየንም" በማለት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ቩሲክ በኢንስታግራም ገፃቸው ላይ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

ፓትርያርክ ኢሪኔጅ በወግ አጥባቂነታቸው የሚታወቁ ሲሆን በአገሪቷ የፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ተፅእኖ በማሳረፍ ይታወቃሉ።

ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ሆስፒታል የገቡት ፓትርያርኩ በተለይም በትናንትናው ዕለት የጤናቸው ሁኔታም አሽቆልቁሎ የመተንፈሻ ማገዣም መሳሪያ ተገጥሞላቸው ነበር።

ዜና እረፍታቸውም በዛሬው ዕለት ታውጇል።

ፓትርያርኩ የሰርቢያን መንግሥት ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ዝግጅቶችን እንዲያደርጉ ፈቅዷል በሚል የተቹ ሲሆን የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትንም "ከተፈጥሮ ያፈነገጠ፤ ነውር ሥራ" በማለትም መናገራቸውን የቢቢሲ ባልካን ዘጋቢ ጋይ ዴላውኔይ ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በጎሮጎሳውያኑ 2008 ነፃነቷን ያወጀችውን የኮሶቮን አገር መሆንም በከፍተኛ ሁኔታም ይቃወሙ ነበር።

ፓትርያርክ ኢሪኔጅ ጥቅምት 25/2013 ዓ.ም የነበረውን የቀብር ሥነ ሥርዓት ካካሄዱ ከሦስት ቀናት በኋላ ነው ሆስፒታል የገቡት።

በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በቀብራቸው ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ሲሆን በርካቶቹ ጭምብል አላጠለቁም፤ አካላዊ ርቀታቸውንም አልጠበቁም ነበር ተብሏል።

የፓትርያርኩንም ሰውነት በመሳምና በመሳለምም ተሰናብተዋቸዋል። ከዚህ በፊትም የሞቱት ጳጳስ አምፊሎሂጁ የኮሮናቫይረስ መመሪያዎችን በመጣስ በርካታ ሰዎች የሚሰባሰቡበት ቦታ ላይም ይገኙ ነበር ተብሏል።

ጳጳሱም በኮሮናቫይረስ ተይዘው ከሞቱ በኋላ በሞንቴኔግሮና ሰርቢያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመሆኑ የጤና ኃላፊዎችም ጥንቃቄ እንዲደረግ ቢያስጠነቅቁም በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ በርካቶች ታድመዋል።

በአገሪቷ ውስጥ 104 ሺህ ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 110 ግለሰቦች ህይወታቸውን አጥተዋል።

በደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያን መሪዎች ለወረርሽኙ የሚሰጡት ምላሽም አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል።

በዚህ ሳምንትም ቁርባን ማቁረብ ለኮሮናቫይረስ አያጋልጥም ብለው የፀኑት የግሪኩ ቄስ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ተፈፅሟል።

የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክም በኮሮናቫይረስ ታመው አገግመዋል።

የ82 ዓመቱ ኤጲስ ቆጶስ ኢሮንዮሞስ ግሪክ የጣለችውን የኮሮናቫይረስ መመሪያዎችን ቢደግፉም ቅዱስ ሲኖዶሱ ግን በቁርባን ላይ የተነሳውን ትችት ሊቀበል አልቻለም።