የኬንያ ጦር በሽብር ጥቃት ጊዜ 'ወታደሮቹ ሳር ውስጥ ተደብቀው ነበር' መባሉን አጣጣለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኬንያ ጦር 'ኒው ዮርክ ታይምስ' ኢስላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሸባብ የማንዳ ቤይ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ጥቃት ሲፈፅም ወታደሮቹ ሳር ውስጥ ተደብቀው ነበር ሲል የፃፈውን ሪፖርት አጣጣለ።
የኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ እንደሚያትተው በወቅቱ የኬንያ ወታደሮች ሁኔታ ባልደረቦቻቸው የሆኑትን የአሜሪካ ወታደሮች አስፈርቷቸው ነበር።
ጋዜጣው አክሎም የአልሻባብ ታጣቂዎች በካምፑ በነበሩ ኬንያውያን የተሰጣቸው መረጃ ሳይጠቀሙ እንዳልቀረም ገልጿል።
ይሁን እንጅ የኬንያ ጦር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ፖል ንጁጉና፤ የተፈፀመው የሽብር ጥቃት ዝርዝር መረጃ ይህንኑ ለማጣራት የተሰማራው ቡድን የሚያመጣቸው ውጤቶች ሲታወቁ ግልፅ ይሆናል ብለዋል።
"የጋዜጣው ዘገባ ከምን እንደተነሳና የምርመራ ውጤቱ እስከሚጠናቀቅ እየጠበቅን ባለንበት ሰዓት መውጣቱ እንግዳ ነው፤ ምን እንደተፈጠረ ትክክለኛና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ሪፖርት የሚኖረን ምርመራው ሲጠናቀቅ ነው" ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ዘ ደይሊ ኔሽን የተሰኘው ጋዜጣም "ካምፕ ሲምባ በኬንያ ምድር ላይ አሜሪካ የደህንነት ኦፕሬሽን የምትሰራበት ቦታ ነው" ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጦሩን ባለሥልጣን ጠቅሶ ዘግቧል።
የጦሩ ባለሥልጣን እንደተናገሩት "በካምፑ ውስጥ የሆነው ነገር ምስጢራዊ ነው፤ እስካሁን አሜሪካዊያን ጥቃቱ በተፈፀመበት ጊዜ በርካታ ሠራተኞቻቸው መገኘታቸውን በተመለከተ ዝምታን መርጠዋል። በካምፑ ላይ ትዕይንቱን ሲያካሂዱ የነበሩት ራሳቸው ናቸው" ሲሉ ጣታቸውን ወደ እነርሱ ቀስረዋል።
ካምፕ ሲምባ በኬንያ የባህር ዳርቻ ከተማ ላሙ የሚገኝ ሲሆን የኬንያና የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይሎች ይጠቀሙበታል።
ባለፈው የፈረንጆቹ ጥር 5 በተፈፀመው ጥቃት አንድ የአሜሪካ ጦር አባል እና ሁለት ኮንትራክተሮች መገደላቸው ይታወሳል።
የኬኒያዋ ላሙ የባህር ዳርቻ ለሶማሊያ ድንበር ቅርብ ነች።













