ኬኒያ፡ በላሙ ሶስት አሜሪካውያን ከተገደሉ በኋላ የሰዓት እላፊ ታወጀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኬኒያ መንግሥት በላሙ የኬኒያና አሜሪካ ጥምር ጦር ወታደራዊ ካምፕ ላይ አልሸባብ ጥቃት ፈጽሞ ሶስት አሜሪካውያን ከተገደሉ በኋላ ሰዓት እላፊ አወጀ።
አልሸባብ በላሙ በተደጋጋሚ ጥቃት የሰነዘረ ሲሆን የበርካታ ኬኒያውያን ሕይወት ማለፉም ይታወሳል።
የሰዓት እላፊው ከምሽቱ ሶስት ሰዓት እስከ ንጋት አስር ሰዓት ድረስ ይቆያል ተብሏል።
በኬኒያ የሚታተመው ስታር ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ፣ የሰዓት እላፊው የተጣለው የጸጥታ ባልደረቦች የሚያደርጎትን የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ ለማገዝ እንዲሁም የሚኖሩ አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎች ለመከታተል እንዲረዳቸው ነው ተብሏል።
የኬኒያዋ ላሙ የባህር ዳርቻ ለሶማሊያ ድንበር ቅርብ ነች።
በስታር ጋዜጣው ላይ የተጠቀሱት የለላሙ ፖሊስ ኃላፊ፣ ሙቻንጊ ኪኦኢ፣ በሰዓት እላፊው ወቅት መኪኖች እንዲንቀሳቀሱ አይፈቀድላቸውም። በቀንም ፖሊስ መኪኖችን ላይ ፍተሻ ያካሂዳል ማለታቸው ተዘግቧል።
እሁድ እለት በጦር ካምፑ ላይ አልሸባብ ባደረሰው ጥቃት ከሰው ሕይወት በተጨማሪ አውሮፕላኖችና መኪኖችም ተቃጥለዋል።
በጦር ካምፑ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች ተጨማሪ ጥቃት ሊኖር ይችላል በሚል አካባቢያቸውን ለቅቀው ወደ ሌላ ስፍራ ሄደው ነበር።
ከዚህ ቀደም በዝችው የኬኒያዋ ላሙ ከተማ አልሸባብ አድርሶታል በተባለ የመኪና ላይ ጥቃት ሶስት ሰዎች ሲሞቱ ሁለቱ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚታወስ ነው።
ወደ ሞምባሳ በመጓዝ ላይ የነበረውን የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ አንድ ግለሰብ ካስቆመ በኋላ በርካታ ጥይቶችን እንዳርከፈከፈበት የአይን እማኞች ገልጸው ነበር።
ኬኒያ ወደ ሶማሊያ ጦሯን ያዘመተችው እ.አ.አ. በ2011 ሲሆን ለዚህም ምክንያቴ ነው ብላ የነበረው ከሶማሊያ ወደ ግዛቷ ድንበር እያቋረጡ የሚፈፀሙ ጥቃቶችና እገታዎች በመበራከታቸው ነበር።
በአሁኑ ሰዓት የኬኒያ ጦር በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ስር ሲሆን በምዕራባውያን የሚደገፈውን የሶማሊያ መንግሥት በመደገፍ የሠላም ማስከበር ሂደቱን ይሰራል።
አልሸባብ በሶማሊያና በኬኒያ
መቀመጫውን በሶማሊያ ያደረገው አልሸባብ በምስራቅ አፍሪካ አሁንም የደህንንት ስጋት እንደሆነ መቀጠሉ እየተገለፀ ነው።
አልሸባብ በሶማሊያና በኬኒያ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን የፈፀመ ሲሆን እኤአ በ2013፣ 67 ሰዎችን የቀጠፈው የዌስት ጌት ሞል ጥቃት የሚታወስ ነው።
በ2014 ደግሞ 148 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የጋሪሳ ጥቃት የተፈፀመውም በአልሸባብ ነበር።
በ2017፣ በሶማሊያ ከ500 በላይ ሰዎችን የገደለው በመኪና ላይ የተጠመደው ቦምብ ፍንዳታም የተቀነባበረው በአልሸባብ መሆኑ ይታወቃል።
በ2019 ደግሞ በኬኒያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው ዱሲት ዲ2 ሕንፃ ላይ የደረሰውና ከ21 ሰዎችን የሞቱበት ጥቃትንም የፈፀመው አልሸባብ ነበር።
የአልሸባብ አማፂያን በሶማሊያና በኬኒያ ላሙ የሚገኙ ወታደራዊ ካምፖች ላይ የደረሱ የተለያዩ ጥቃቶችን መፈፀሙን በተደጋጋሚ ጊዜ ተናግሯል።
አሜሪካ የአልሸባብን እንቅስቃሴ ለመግታት ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች ፈፅማለች።















