#10 እሷ ማናት፡ የሴቶች ጠንካራ ጎን የሚያሳይ ጥናት ላይ አተኩራለሁ
ዶ/ር ሜሮን ዘለቀ፣ ከዓለም ባንክ፣ ከተባበሩት መንግሥታትና ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በመሆን በጾታ፣ በስደተኞችና በሀይማኖት ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን ታካሂዳለች።
አሁን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጥናታዊ መጽሔት ከፍተኛ አርታኢ ናት። በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ በሲንጋፖርና በጅቡቲ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በተጋባዥ መምህርነት ታስተምራለች። የምርምር ሥራዎችን ታከናውናለች። ጥቂት የማይባሉ ጥናታዊ ጽሑፎችንም አሳትማለች። ለቢቢሲ ስለ ህይወት ልምዷ ለቢቢሲ እንዲህ አካፍላለች።

ተወልጄ ያደግኩት በነቀምት ከተማ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በነቀምት ካቶሊክ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በቤተል ኢቫንጀሊካል ነው የተከታተልኩት።
ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በአሜሪካን ሚሽን ገርልስ ስኩል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቀቅኩ።
በልጅነት ሕይወቴ ነቀምት እያለሁ ለቀረጹኝ አስተማሪዎች ትልቅ ሥፍራ እሰጣለሁ። የመጀመሪያ ዲግሪዬን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት አጠናሁ።
የመጀመሪያ ዲግሪዬን ትምህርቴን አጠናቅቄ እንደተመረቅኩኝ ወዲያውኑ ሁለተኛ ዲግሪዬን በሶሻል አንትሮፖሎጂ ሰራሁ።
አሁንም ወደ ሥራ ሳልሰማራ ጀርመን በመሄድ በባይሩት ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዲግሪዬን ተከታተልኩ። የሶስተኛ ዲግሪዬን እንዳገኘሁ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል በረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ ተቀጠርኩ።
አንድ ዓመት ተኩል ካስተማርኩ በኋላ ለድህረ ዶክትሬት ትምህርት ወደ ጀርመን ተመልሼ ሄድኩ።
የመማር ማስተማር ነጻነት
በማህበራዊ ሳይንስ ላይ ስሰራ የመማር ነጻነት ትልቁ ችግር ነበር። እኛ ማህበረሰብን እናጠናለን። ማህበረሰቡ ውስጥ ያገኘነውንና የገባንን ችግር መልሰን ለሕዝቡ እናቀርባለን። ይሁን እንጂ እኛ የማህበረሰብ ችግር የምንለውን መንግሥት መስማት አይፈልግም ነበር። እኔም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ አልፌያለሁ።
ሌላኛው መሰናክል ደግሞ የማህበራዊ ጥናት ቢሮ ቁጭ ተብሎ የሚሠራ ሳይሆን ሁል ጊዜ ወደ ማህበረሰቡ እየወረድን ነው የምናጠናው።
እኔ ደግሞ ልጆችና ቤተሰብ አሉኝ። ከዚህ ጋር መጋጨቱ አይቀሬ ነው። በተጨማሪም በእኛ ዩኒቨርስቲ እንኳ ብንወስድ ተምረው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ሴቶች ጥቂት ስለሆንን ድሮውንሙ ማህበረሰቡ ሴቶች ላይ ያለውን አሉታዊ አመለካከት እንዲያጠናክር ያደርጋል።
ለኛ ለሴቶች ከወንድ በበለጠ ራስን ማሳየት ችሎታን ማስመስከር ይጠበቃል። ይኼ በመላው ዓለም ያሉ ሴቶችን የሚገጥማቸው ነገር ነው።
'ግሎባል ያንግ አካዳሚ' በሚባል ድርጅት ስር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የሴት ተመራማሪዎችን ልምድ አንድ ላይ በማድረግ በመጽሐፍ መልክ ለማውጣት እየተሰራ ነው። እኔም በአፍሪካ ቀንድ ካሉ ተመራማሪዎች መካከል ተካትቼ እየሰራሁ ነው፤ የኔም ታሪክ ተካቶበታል።

የፎቶው ባለመብት, Meron Zeleke (Dr)
እንግዲህ የእነዚህ ሁሉ ሴቶች ታሪክ ሴት በመሆናቸው ብቻ ተመሳሳይ ልምድ ኖሯቸው አንድ ላይ እንዲጻፍ ከተደረገ ችግር አለ ማለት ነው።
በነገራችን ላይ ጥናቶች ብዙ ጊዜ ስለችግር ነው የሚያወሩት፤ እኔ ግን በጥናቴ፣ ለምሳሌ በጾታ ጉዳይ ላይ ስሰራ ሴቶች የሚጎዱበትን ብቻ ሳይሆን የማህበረሰብ ተወካይ መሆናቸውንና በብዙ ስፍራዎች የሚጫወቱትን በጎ ሚና፣ የማስታረቅ ስራዎች የሚሰሩ መሆናቸው ላይ አተኩራለሁ።
ሲቄን ብንወስድ ሴቶች የሚጎዱበት ሳይሆን ሌሎችንም የሚያስተምሩበት፣ የሚያስታርቁበት፣ የሚያስተካክሉበትና መብታቸውን የሚያስከብሩበት ነው።
ባሕልና ሰብዓዊ መብት
የባህልና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ሁሌም አከራካሪ ነው። ባህል የሰዎችን መብት ያጠናክራል ወይንስ ይጥሳል የሚለው ሁሌም ጥያቄ ነው።
አንትሮፖሎጂ እንዳጠና ሰውና እንደው በጠቅላላው የባህል ጥሩና መጥፎ የለውም። በባህላችን ውስጥ ያሉ መልካምና ሊቀርጹን የሚችሉ ነገሮችን ተጠቅመን ማደግ እንችላለን።
እኔ ጥናቴን በወሎ ከሚሴ በግጭት አፈታት ስርዓት ላይ ሠርቻለሁ። እዚያ ከመንግሥት የፍትህ ስርዓት ወይንም ፍርድ ቤት ከመሄድ ይልቅ ሰዎች በሼካዎች፣ በሀገር ሽማግሌዎች መዳኘትን ይመርጣሉ።
እንግዲህ ሰዎች ከመንግሥት ይልቅ ጉዳያቸውን አምነው ለእነዚህ ሰዎች ይዘው ይሄዳሉ ማለት ነው። ሥርዓተ ጾታንም በምናጠናበት ጊዜ እንዲያው በደፈናው ባህል ይጎዳል ብለን መነሳት የለብንም። እንደዚያ ካልን እንደ ሲቄ ያሉ ባህሎችን ልንተዋቸው ነው ማለት ነው።
ወደ ሰብዓዊ መብት ጉዳይ ስንመለስ ደግሞ ይህ መብት የቅንጦት ነው ይህኛው ቀድሞ መምጣት አለበት በሚል ጉዳይ አልስማማም።
የሰው መብት መሰረታዊ ነገር ነው እንጂ በቅደም ተከተል የሚመጣ አይደለም። ሰው ያለ መብቱ ሙሉ ሆኖ መኖር አይችልም።
ጊዜና ሥራ
ለእኔ ጊዜ በጣም ትልቅ ስጦታ ነው። ትልቅ ዋጋ ነው የምሰጠው። ሆኖም ግን አይ ምንም ችግር የለም ብዬ ብል ውሸት ነው። ቤተሰብም ሆነ ስራ እኩል ትኩረት ይሻሉ።
በቀን ያለንን 24 ሰዓት አብቃቅተን መጠቀም ይኖርብናል። ለእኔ በእዚህ መንገድ ትልቁ መርህ ስራዬን ቢሮዬ ጨርሼ መግባት ነው፤ ሁሌ ባይሳካልኝም።

የፎቶው ባለመብት, Meron Zeleke (Assistant Proffessor)
ቅዳሜና እሁድ ደግሞ ከልጆቼና ከባለቤቴ ጋር አሳልፋለሁ።
በተለይ ትልቁን ልጄን እንደ ጓደኛ አቅርቤ ለማሳደግ እሞክራለሁ። ሌላው በትምህርት ለመግፋት ለሚፈልጉ ሴቶች ብዙ ነገር የሚወሰነው እችላለሁ ብሎ በመነሳት ሲሆን በተጨማሪ ለነገሮች መልካም እይታ ሊኖረን ይገባል ብዬ አምናለሁ።
በሥራዬ ሲመጣ ግን ወንድ መሆን ወይ ሴት መሆን እዚህ ለመድረስ ያግዛል ወይም ያስቀራል ብዬ አላምንም።

እሷ ማናት? የሚለው ጥንቅራችን ያሰቡበትን ዓላማ ለማሳካት ብዙ ውጣውረዶችን ያሳለፉ ሴቶችን ታሪክ የምናስቃኝበት ነው።



















