እሷ ማናት? #4፡ ከሒሳብ ጋር በአጋጣሚ ነው የተዋደድነው

ኤቢሴ አዱኛ

በሒሳብ ትምህርት የዶክትሬት ዲግሪዋን (ፒኤች ዲ) ለማግኘት እየሰራች ነው። ሰዎች እምብዛም ገፍተው በማይሄዱበት የትምህርት ዓይነት እንዴት ውጤታማ ልትሆን እንደቻለች አጫውታናለች።

ስሜ ኤቢሴ አዱኛ ይባላል። ተወልጄ ያደኩት በነቀምት ከተማ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቴን በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተምርያለሁ። በአሁን ሰዓት ደግሞ የሦስትኛ ዲግሪ ትምህርቴን በዴንማርክና በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች እየተከታተልኩ ነው።

ሳብ መረጠሽ ወይንስ መረጥሽው ?

የሙያ ሕይወቴ ከሒሳብ ጋር የተቆራኘ ይሆናል ብዬ አልገመትኩም ነበር። ለመጀመሪያ ዲግሪ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በተመደብኩበት ወቅት የሒሳብ ትምህርት ሳልመርጥ በአጋጣሚ ደረሰኝ። ከዚያ በኋላ ግን እኔና ሒሳብ በጣም ተዋደድን። እኔ ልምረጠው ሒሳብ ይምረጠኝ የሚታወቅ ነገር የለም።

የሒሳብ ትምህርትን ከድሮም ፈርቼው አላውቅም። ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ትምህርቱ ሲደረሰኝ ጥሩ ነጥብ ማስመስገብ ጀመርኩኝ፤ እየወደድኩትም መጣሁ። በዚያ ላይ ይህ ትምህርት ለሴት ይከብዳል ለወንድ ደግሞ ይመቻል የሚል አመለካከት የለኝም።

ማንም ሰው ፍላጎት ካለው፣ ከጣረና በሥራ ካስደገፈው ይሳካል ብዬ ስለማስብ የሒሳብ ትምህርትን አጥብቄ ይዤ ቀጠልኩበት፤ እዚህም ደረስኩኝ።

ኤቢሴ አዱኛ

የፎቶው ባለመብት, Ebise

አሁንም ቢሆን ከምወዳቸው ትምህርቶች መካከል ትልቁን ቦታ የያዘው ሒሳብ ነው።

የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለሁ 'ጊዜ ቤት' ላይ ሌሎች ልጆች ሸምድደው በፍጥነት እንደሚሉት አልነበርኩም፤ ነገር ግን በልጅነቴ በተወሰነ ደረጃ ይህንን 'የጊዜ ቤት' እሠራ ነበር።

በዚያ ወቅት ተማሪ እያለሁ አባቴ የሒሳብ መምህር ስለነበረ በሒሳብ ጥሩ መረዳት እንዲኖረኝ አድርጓል። በጭንቅላቴ ሸምድጄ ከመያዝ ይልቅ ተረድቼ ማስላት ይቀለኝ ነበር።

የሒሳብ ጥቅም የተለያየ ነው። ለምሳሌ ሒሳብ በሁለት ይከፈላል፤ 'ፕዩር ማቴማቲክስና አፕላይድ ማቴማቲክስ' ተብለው ይለያሉ።

እኔ የምማረው 'አፕላይድ ማቴማቲክስ' በተጨባጭ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚጠቅም ነው። ለምሳሌ የምመረምራቸው ስሌቶች ኤች ሲቪ ለተባለው የጉበት ቫይረስ መፍትሔ ለማግኘት የሚረዳ ነው።

ስለዚህ ሒሳብ በሕይወታችን ያሉን ተጨባጭ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የሚረዳ የትምህርት ዓይነት ነው። ነገ የሚሆንን ነገር ለመተንበይ ሒሳብ ችግሮቻችንን በቁጥር አስልተን ለማስቀመጥ ይረዳናል።

የሒሳብ ምሁሮች ከስሌቱ በኋላ ቀመሩን ከነመፍትሔው ያስቀምጡልናል። የምህድስና ሙያ ያላቸው ሰዎች ደግሞ እንዲህ ዓይነት ቀመሮችን በሥራ ላይ ያውላሉ። ስለዚህ ከሒሳብ ሙያተኞች ይልቅ በምህንድስና ውስጥ የተሰማሩ ሰዎች በይበልጥ ማስረዳት ይችላሉ።

ውጣ ውረዶችን ለማለፍ በሥራም ሆነ በኑሮ እንደማንኛውም ሰው የተለያየ መሰናክል ይገጥመኛል። ነገር ግን የችግሩን ያህል ሳይሆን ነገሮችን ከአቅሜ አንፃር ነው የምገመግማቸው።

ችግር እንደሚያበረታኝና እንደሚያጠነክረኝ ስለማውቅ ሁሌም መውጫ ቀዳዳ ነው የምፈልገው። አንዳንዴ ሰዎች ፊቴንና ዕድሜዬን አይተው ይገምቱኛል። አንዳንዴ ጊዜ እንዲያውም በሴትነቴ ጭምር ለመመዘን ይሞክራሉ።

እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲገጥሙኝ ደግሞ እራሴን በደንብ አስተዋውቃለሁ። ምን ማድረግ እንደምችል፣ ማን እንደሆንኩ እና ፍላጎቴ ምን እንደሆነ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ሁሉ እናገራለሁ።

ይህ ደግሞ በሕይወቴ የምፈልገውን ነገር በሙሉ እንዳገኝ አድርጎኛል በዚያ ላይ ተግባቢ ሰው ነኝ።

ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ መማር ጊዜን ስለሚፈልግ የጊዜ እጥረት ያጋጥማል። የፒኤች ዲ ትምህርት ምግብ የምበላበት ጊዜ እንኳን አይሰጥም፣ ያስጨንቃል ደግሞም ድብርት ያስከትላል።

ቢሆንም ግን ያለኝን ጊዜ አብቃቅቼ ከጓደኞቼም ሆነ ከቤተሰቦቼ ጋር ጊዜ አሳልፋለሁ። ከዚህ ሁሉ ግን ያለንን ጊዜ በደንብ ከተጠቀምንበት የምንፈልገውን ማሳካት ይቻላል ብዬ አስባለሁ።

ፍቅር እና ፒኤች ዲ

እንደሚታወቀው በአገራችን ሴት ልጅ ስትበልጥ ወንዶች ብዙ ደስተኛ አይደሉም፤ ሁሉም እንዲዚህ ናቸው ማለቴም አይደልም ነገር ግን እንዲህ ዓይነት አስተሳብ አለ።

በሁሉም መንገድ ወንድ የበላይ ሆኖ አንዲታይ የሚፈልጉ አሉ። እንደእኔ አመለካለከት የትምህርት ደረጃ እና ፍቅር የተለያዩ ናቸው።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ለመጀመሪያ ዲግሪ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በተመደበችበት ወቅት የሒሳብ ትምህርት ሳትመርጥ በአጋጣሚ ደረሳት። በኋላ ግን ሒሳብና እርሷ በፍቅር ወደቁ።

ስኬቴ ችግር የሚሆንበት ካለ ለማስተናገድ አልችልም። የቤተሰቤ አባላት በማደርገው ጥረት ላይ በጣም የደግፉኛል። ጓደኛና የምወደው ሰው የምለውም ሰው ልክ እነደዚህ የሚደግፈኝ መሆን አለበት።

ለምን ትበልጠኛለች ካለ ግን ይህ ፍቅር ነው ወይንስ ቅናት?

ብዙ ሴቶች ያለንን አቅም የተረዳነው አይመስለኝም። እንችላለን ብለን ካመንን ማድረግ አያቅተንም። ይህን ከተረዳን ደግሞ በውበት፣ በጋብቻ እና በገንዘብ መወሰን የለብንም። እራሳችን ያለምነው ትልቅ ቦታ ላይ መድረስ እንደምንችል ማሰብና መጣር ነው ያለብን።

ስለዚህም የሚያጋጥሙንን መሰናክሎች በእራሳችን ማለፍ መቻል አለብን። እንደዚህ ወደፊት ከተራመድን አገራችንን ወደፊት ለመምራት አያቅተንም።

ያለንን አቅማችንንና መላ የማበጀት ጥበባችንን እንጠቀምበት ብዬ ለሴቶች ምክሬን እሰጣለሁ።