የኮምፒዩተር ትምህርት ለኬኒያ ሴት እስረኞች ሁለተኛ እድል ይሰጣቸው ይሆን?

ሴት እስረኞች

የ44 ዓመቷ ዶርካስ ፈገግ እያለች ከማረሚያ ቤቱ ኮምፒተሮች የአንዱን ዋነኛ የማንቀሳቀሻ ክፍል (ሴንትራል ፕሮሰሲንግ ዩኒት) በማውጣት ለአዳዲሶቹ የክፍሎቿ ልጆች እያንዳንዱ የኤሌክትሪክ ክፍል ለምን ለምን እንደሚያገለግል ታብራራለች።

"አሁን ማንኛውንም ነገር መስራት እችላለሁ። ኮምፒውተር ሳይቀር ልሰራላችሁ እችላለሁ" በማለት ታክላለች።

ዶርካስ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ብቸኛው የሴቶች ማረሚያ ቤት በሆነው እና ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት ላንጋታ ማረሚያ ቤት ከሚገኙ 500 ታረሚያዎች አንዷ ናት።

የተወሰኑት ታራሚዎች በድብደባ፤ ለውዝ እና ፍራፍሬ የመሳሰሉት ነገሮችን መንገድ ዳር በመሸጥ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ የተፈረደባቸው ናቸው።

ሌሎች ደግሞ ግድያ እና ከባድ ስርቆትን በመሳሰሉ ከባድ ወንጀሎች ምክንያት እድሜ ልክ የተፈረደባቸው ናቸው። ወንጀሉ ምንም ይሁን ምን በ2014 ከኬንያ ማረሚያ ቤቶች የወጣ አሃዝ እንደሚያመለክተው በሀገሪቱ ከሚገኙ ፍርደኞች ከ60 እስከ 80 በመቶው የሚሆኑት ተመልሰው ማረሚያ ቤት ይገባሉ።

የ31 ዓመቱ አገሬይ ሞካያ በማረሚያ ቤቱ ክፍል በር ላይ ቆሟል። ሰማያዊ እና ነጭ ቀለም መስመር ያለውን የደንብ ልብስ የለበሱ ታራሚዎች ደማቅ ብርቱካናማ ሹራቦች ደርበው በኮምፒዩተሮች ዙሪያ ተሰባስበው የተራቀቀውን ኮድ በጥቁር የኮምፒተር መተግበሪያ ገጾች ላይ ይተይባሉ።

ቴክኖሎጂን ማዕከል ያደረገው መልሶ ማቋቋሚያ መርሃግብር ''ቼንጅ ሀብ'' መስራች እና በጆሞ ኬንያታ የእርሻ ዩንቨርሲቲ መምህር ነው።

"ለሰዎች ሁለተኛ እድል የመስጠት ጉዳይ ነው" ይላል። "ከዚህ ቀደም ተሳታፊ ካልነበሩበት ኢኮኖሚ ተቋዳሽ እንዲሆኑ እድል የመስጠት ጉዳይ ነው።"

''ቼንጅ ሀብ'' ሴቶችን ከኮዲንግ እና ድረ ገጽ ዝግጅት እስከ ኮምፒውተር ጥገና ሁሉንም ነገር ያስተምራቸዋል። እንደ አግሬይ እምነት ከፍተኛ መጠን ያለውን የኬንያውያን ወደ ማረሚያ ቤት ተመልሶ የመግባት የሚቀንሰው የዚህ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ነው።

"ከዚህ በፊት የተፈረደበትም ሆነ ምንም ወንጀል ፈጽሞ የማያውቅ ሰው በህግ ፊት ተመሳሳይ ናቸው" ይላል። "ስለዚህ በኢኮኖሚው በስራ ፈጠራ ወይም በእድሎች ፊትም ተመሳሳይ መሆን እንዳለበት አስባለሁ።"

"የመለወጥ እድላቸውንና እና ለራሳቸው የሆነ ነገር ሊያደርጉ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች ከነፈግናቸው በዋናነት ውድቀታቸውን እያመቻቸልናቸው ነው።"

በሀሰተኛ ሰነድ ምክንያት ሶስት ዓመት የተፈረደባት ዶርካስ ግማሹን ከጨረሰች በኋላ በጥቅምት 2018 ከማረሚያ ቤቱ ተሰናብታለች።

"አምስት ልጆች አሉኝ፤ ባለቤቴም በህይወት የለም። ስለዚህ ለእኔ እጅግ ጠቃሚው ነገር ወደ እነዚህ ልጆች መመለስ ነው" ትላለች።

ከእስር ቤት ስትወጣ ልትጀምረው ላሰበችው አዲስ የልብስ ስራ ንግድ የሚሆናትን ድረ ገጽ አዘጋጅታ ጨርሳለች። "መኪና ስለሌለኝ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወርኩ እግሮቼን ለአቧራ አልዳርግም። ህይወቴን ይቀይረዋል፤ ጊዜ እና ገንዘብም እቆጥባለሁ" በማለት ታብራራለች።

በከፍተኛ ፍርድ ቤት ጠበቃ የሆኑት አቼይንግ ኦሬሮ እንደሚሉት የኬንያ የፍትህ ስርዓት መልሶ ከማቋቋም ይልቅ በቅጣት ላይ እጅጉን ያተኩራል። እናም ይህ ለውጥ ያስፈልገዋል።

"እስረኞችን መልሶ ለማቋቋ የተቀናጀ እና የታሰበበት ጥረት እየተደረገ ነው ብዬ አላስብም" ይላሉ።

"መልሶ ማቋቋምን ማካተት ወይም ቅጣትን ማዕከል ካደረገው አስተሳሰብ መውጣት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ግለሰቦች በመጨረሻ ከእስርቤት ይወጣሉ፡፡ እናም በማህበረሰብ ውስጥ ይበልጥ ጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ዋነኛው ስንቅ ትምህርቱ ነው።"

በሌላኛው የናይሮቢ አቅጣጫ በትንሽ እና ሞቃታማ ኩሽና ውስጥ የ35 ዓመቷ ራሀብ ንያዊራ ጣፋጭና ነጫጭ ማሳመሪያዎች በትልቁ ባለሁለት ደረጃ ኬክ ላይ በጥንቃቄ ትቀባለች፡፡

በዚህ ዓመት ነበር በከባድ የዘረፋ ወንጀል የተፈረዳበትን የስድስት ዓመት ቅጣት ጨርሳ ከላንጋታ ማረሚያ ቤት የወጣችው፡፡

"ከማረሚያ ቤት ጋር ልታወዳድሩት የምትችሉት ምንም ነገር የለም" ትላለች፡፡ "ማረሚያ ቤት ከቦታዎች ሁሉ አስከፊው ነው። ለእኔ ግን የሕይወት መስመሬን መቀየሪያ ሆነልኝ።"

ራሃብ አሁን የራሷን የዳቦና ኬክ ጋግሮ መሸጥ ስራ እያካሄደች ሲሆን፤ አንዲ ሴት እና ሁለት ወንድ ልጆቿን ወደዚህ ኩባንያ የማምጣት እቅድ አላት፡፡ "ለንግድ ስራዬ እድገት እጅግ የገዘፈውን ሚና የሚጫወተው ድህረ-ገጼ ነው ማለት እችላለሁ" በማለት በፈገግታ ታብራራለች፡፡

"በኬንያ ማንኛውም ቦታ አዳዲስ ደንበኞችን በቀጥታ እንዳገኝ ያግዘኛል፡፡"

ድህረ-ገጹን ያበለጸገችው ማረሚያ ቤት እያለች ነበር፡፡ "በቼንጅ ሀብ አማካኝነት ብዙ ነገሮችን ተምሬአለሁ፡፡ ለድህረ-ገጽ የሚያግዙትን ኤችቲኤም ኤል፤ ሲኤስኤስ እና ጃቫ ስክሪብትን ምንነት አውቄያለሁ፡፡ ለድህረ-ገጼ ሁሉንም ነገር የቀመርኩት ደግሞ እራሴ ነኝ፡፡" ትላለች።

"አሁን ሴት ልጄ ስታየኝ በጣም ኩራት ይሰማኛል፡፡"

እንደ አገሬይ እምነት አንዴ ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ የሴት ታራሚዎች ህይወት ፍጹም ሊቀይረው የሚችለው ለዚህ ለቴክኖሎጂ ያላቸው ቅርበት ነው፡፡

ለምን ሴት እስረኞች ላይ እንዳተኮረ ሲያብራራ"ሁሌም ቢሆን ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ ነገሮች ላይ የጾታ አድሎ አለ"ይላል።

"የአንዲት ሴት ህይወት ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ቻልኩ ማለት ተፅዕኖው ተያያዥነት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ለህጻናቱም ቢሆን ከኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ ጋር ገና በጊዜ ለመተዋወቅ እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡"

አግሬይ በኬንያ እንዳሉ የሚገመቱትን 8000 ሴት ታራሚዎች ለመድረስ ''ቼንጅ ሀብን'' ለማስፋፋት የገንዘብ ድጋፍ እያፈላለገ ነው። እስካሁንም በላንጋታ የሚገኙ 21 ታራሚዎች በእርሱ ፕሮግራም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ታራሚዎች የኮምፒዩተር ኮድ አንዲሰሩ እና ስሪዲ ማተሚያዎችን ተጠቅመው የተለያዩ መገልገያዎችን እንዲያበለጽጉ ከሚከፍሉ ኩባንያዎች ጋር አብሮ በመስራት ፕሮጀክቱን ዘላቂ የማድረግ እቅዶች አሉት፡፡

ከዚህ በኋላ ህልሙ ''ቼንጅ ሀብን'' በሀገሪቱ ውስጥ ወዳሉ ሁሉም ማረሚያ ቤቶች መውሰድ ነው፡፡

በሚገርም ሁኔታ የቴክኖሎጂ ፕሮጀክት መስራት እንደምትፈልግ ስታወራ ሁሉም ሰው ለምን የወንዶች ወይም የወጣቶች ማረሚያ ቤት አትሄድም? ይሉሃል።"

"የእኔ መልስ አዎ እሱም ጠቃሚ ነው፤ ነገር ግን ሁለተኛ ላይ የሚመጣ ነው እላቸዋለሁ፡፡ በሴቶች ማረሚያ ቤት ካሳካነው በኋላ ወደ ሌሎች እንሄዳለን።"