ትግል ለተሻለ የአካል ጉዳተኞች ማገገሚያ በሰሜን አፍሪካ

አሚና ስላኦዊይ
የምስሉ መግለጫ, ከሞሮኮው ትልቁ የአካል ጉዳተኛ ማዕከል ጀርባ ያለችው አሚና ስላኦዊይ ናት

አሚና ስላኦዊይ ከባለቤቷ ጋር በእረፍት ሽርሽር ላይ እያለች ነበር ከብስክሌት ወድቃ መጨረሻዋ ተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቼር) ላይ የሆነው፡፡

አደጋው የእሷን ብቻ ሳይሆን በሞሮኮ እና ሌሎች ሃገራት የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞችን ህይወት የቀየረ ነበር፡፡

አሚና ከሀብታም ቤተሰብ የመጣች በመሆኗ የምትፈልገውን ህክምና የማግኘት አቅም ነበራት፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ ሞሮኳውያን ጓደኞቿ ይህን ማድረግ እንደማይችሉ አሰበች፡፡

ከጥቂት ጓደኞቿ ጋር በመሆን የመሰረተችው የማገገሚያ ማዕከል ከ25 ዓመታት በኋላ 26ሺህ አካል ጉዳተኞች ህክምና፣ መገልገያ መሳሪያዎች እና ድጋፍ እንዲያገኙ አግዟል፡፡

"በመጀመሪያ ሁሉም ይስቁ ነበር፤ እብድ ናችሁ፡፡ የተሰባሰባችሁት መራመድ እንኳ የማትችሉ ናችሁ፤ በዛ ላይ ገንዘብም የላችሁ፡፡ ይባስ ብሎ የማገገሚያ ማዕከል ለመገንባት ታስባላችሁ? ይሉናል። እኛም መልሳችን አዎ ነበር" ትላለች አሚና።

ራስን በገንዘብ መቻል

ከአሚና ጋር እያወራን የድርጅቷ ግሩፕ ኤ.ኤም.ኤች ዋና መለያ በሆነው እና በካዛብላንካ በሚገኘው ኑር ማገገሚያ ማዕከል ኮሪዶር ወደ ታች እየተጓዝን ነው። በኮሪዶሩ ሁለቱም አቅጣጫ ህሙማን ክብደት የሚያነሱባቸው ከፍ ያለ ሙዚቃ የሚሰሙባቸው ሰፋፊ ክፍሎች አሉ፡፡

"የመድህን ዋስትና ያላቸው ወይም የሚከፍሉት ያላቸው ሰዎች ለአቅመ ደካማዎች ይከፍላሉ" ትላለች ድርጅቱ የመክፈል አቅም የሌላቸውን ሰዎች የሚያስተናግድበትን ፈጠራ የተሞላበት ዘዴ ስታብራራ።

ባለጸጋ ህሙማን ለራሳቸው መክፈል ለማይችሉ ታካሚዎች ድጎማ ያደርጋሉ
የምስሉ መግለጫ, ባለጸጋ ህሙማን ለራሳቸው መክፈል ለማይችሉ ታካሚዎች ድጎማ ያደርጋሉ

"አምስት ሰዎች በክፍያ በታከሙ ቁጥር አንድ ሰው በነጻ አገልግሎት ያገኛል፡፡ እናም ይህ የአሰራር ዘዴ ከአራት ወይም ከአምስት ዓመት በኋላ እራሳችንን እንድንችል አደረገን። የምናፈሰው መዋዕለ ንዋይ ተጨማሪ ትርፍ ስለሚያስገኝልን፤ ሰዎችን መርዳት አስችሎናል።

በነጻ ህክምና ከሚያገኙት ሰዎች መካከል ደግሞ ፈቲሃ ኤት ሞሃመድ አንዷ ናት። የቤቷን ደረጃዎች እያጸዳች እያለ ወድቃ ነበር የአካል ጉዳት ያጋጠማት። ቡድኑ የማገገሚያዋን 80 በመቶ ውጪ ሸፍኖላታል፡፡ በልዩ ሁኔታ የተሰራ ሞተር ሳይክልም ገዝቶላታል፡፡

ሞተር ሳይክሉን መንገድ ዳር ባላት መሸጫ ላይ የምትቸረችራቸውን የመዋቢያ እቃዎች ለመግዛት በየቀኑ ትጠቀምበታለች።

"አልጋ ውስጥ እያለሁና እናቴ ሁሉንም ነገር ስትሰራልኝ በተለየ አለም ውስጥ የምኖር ያክል ይሰማኝ ነበር፡፡ ሰውነቴ አይታዘዘኝም፤ በህይወት እንዳለሁ እንኳን አይሰማኝም ነበር፡፡"

"ሞተር ሳይክሌን መጋለብ እወዳለሁ:: አሁን ነጻነት ይሰማኛል" ትላለች፡፡

ከማገገሚያ ባሻገር

በየቀኑ 120 ያህል አካል ጉዳተኛ ሰዎች ከማገገሚያ እስከ ሰው ሰራሽ ተገጣሚ የሰውነት ክፍሎች እና የስነ ልቦና ድጋፍ ፍለጋ ወደ አሚና ቢሮዎች ይመጣሉ፡፡

"የግሩፕ ኤ.ኤም.ኤችን ለየት የሚያደርገው የማገገሚያ ወጪ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነገር ለመሸፈን መሞከራቸው ነው" ይላሉ በሞሮኮ የአጋርነት፤ ሴቶች፤ ቤተሰብ እና ማህበራዊ ልማት ሚኒስቴር የማህበራዊ ውህደት ዳይሬክተር አህመድ አይት ብራሂም፡፡

"አካል ጉዳተኞች ተመልሰው ከማህበረሰቡ ጋር መቀላቀላቸውን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ በመላው አፍሪካ በእርግጥም ለየት ያለ ነው፡፡"

ከድጃ ዊልቸር ላይ ሆና
የምስሉ መግለጫ, ከነርቭ ችግር ጋር በተያያዘ አካል ጉዳተኛ የሆነችው ከድጃ ከአሚና ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላታል

የአሚና ግሩፕ አሁን አካል ጉዳተኛ ህጻናትን ለመቀላቀል የሚያስችል ይበልጥ አካታች የሆነ አደረጃጀት ያለው ት/ቤት ከፍቷል፡፡ ይህ ደግሞ ከአካል ጉዳተኛ ህጻናት ከግማሽ በታቹ ብቻ ወደ ት/ቤት ለሚሄዱባት ሀገር እጅግ ወሳኝ ነው፡፡

የስምንት ዓመቷ ከድጃ ከነርቭ ችግር ጋር በተገናኘ አካል ጉዳተኛ ስትሆን ትምህርቷን በመከታተል ላይ ትገኛለች፡፡ የምትኖረውም ከክሊኒኩ አጠገብ ወላጆቿ በተከራዩት ጠባብ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ልጃቸው የሚያስፈልጋትን ድጋፍ እንድታገኝ ለማድረግ ማራካሽ ከምትባል ከተማ ወደዚህ የመጡት ከዓመት በፊት ነበር፡፡

"ማራካሽ እያለሁ ጓደኞች አልነበሩኝም፡፡ እዚህ ከመጣሁ በኋላ ነው ጓደኞች ማፍራት የጀመርኩት፡፡ እየተሻለኝ ሲመጣ የሆነ በጣም ደስ የሚያሰኘኝ ስሜት ይሰማኝ

አብዛኛውን የከድጃን የማገገሚያ ወጪ የሚሸፍነው የአሚና ግሩፕ ነው፡፡ ቤተሰቦቿ ከድጃ እንዴት ትበሳጭ እንደነበር እና አብዛኛውን ጊዜዋን አልጋ ላይ በጀርባዋ ተኝታ ታሳልፍ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ አሁን ግን ስዕል መሳል፤ ከሌሎች ልጆች ጋር መጫወት ብሎም ራሷን ችላ እስከመቆም ሳይቀር ደርሳለች፡፡

በእድገት ጎዳና ለመቀጠል ክሊኒኩ ከመላው አፍሪካ ሀብታም ህሙማንን ለመሳብ ጥረት እያደረገ ነው
የምስሉ መግለጫ, በእድገት ጎዳና ለመቀጠል ክሊኒኩ ከመላው አፍሪካ ሀብታም ህሙማንን ለመሳብ ጥረት እያደረገ ነው

አዳዲስ ተግዳሮቶች

ወደ ክሊንኩ ስንመለስ አሚናን ከድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስበሰባ ውስጥ ሆና አገኘናት፡፡ ምንም እንኳ ስኬታማ ቢሆኑም የግሩፑ ፈጠራ የታከለበት የገንዘብ አያያዝ ሞዴል አደጋ ስለተጋረጠበት የወደፊት ስልቶች ላይ እየተወያዩ ነው።

ችግር እየሆነ የመጣው የግል ክሊኒኮች ለሀብታም አካል ጉዳተኞች የሚሆን ተወዳዳሪ እና ቅንጡ የማገገሚያ ማዕከል ለመገንባት እያቀዱ መሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ እንደ ፈቲሃ እና ከድጃን ለመሳሰሉ መክፈል ለማይችሉ አካል ጉዳተኞች የህክምና ወጪ የሚሸፍኑት ሃብታሞቹ ናቸው፡፡

ነገር ግን ችግሩ ያ ብቻ አይደለም፡፡

"የበጀታችንን አንድ አስረኛ የምናወጣው መክፈል ለማይችሉ ህሙማን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን የመግዛት አቅማችን በየጊዜው እየቀነሰ ሲሆን ከመንግስትም ምንም አይነት ድጋፍ አናገኝም፡፡ በመሆኑም የገንዘብ ድጋፍ በምናገኝበት ዘዴ ላይ የበለጠ ፈጠራ ያስፈልገናል" ትላለች አሚና::

በቅርቡ ክሊኒኩ ለሀብታም ህሙማን የሚሆን 20 ራሳቸውን የቻሉ ክፍሎች ያለው አዲስ ቅርንጫፍ ከፍቷል፡፡

የማገገሚያ አማራጮች ውስን በሆኑባቸው እንዲሁም ከነጭራሹ በሌሉባቸው በመላው አፍሪካ የሚገኙ ብዙ ባለጸጋ አካል ጉዳተኞችን ቀልብም እየሳበ ነው፡፡

በዋናነት የሚመጡት ከሴኔጋል፤ ከኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና ከጊኒ ሲሆን፤ የሚመጡበትም ምክንያት ቅርበቱ እንዲሁም ዋጋው ከፈረንሳይም ሆነ ከሌሎች አውሮፓ ሀገራት በአስር እጥፍ ስለሚረክስ ነው፡፡

"ጊዜው ይሮጣል አሁን 25 ዓመት ሞላን፡፡ ቡድኑ እዚሁ እንዳለ ነው፡፡ ግን እስከመቼ?" ትላለች አሚና፡፡

"ግባችን እኛ ከዚህ ስንሄድ የሰራነው እንደማይጠፋ ማረጋገጥ ነው፡፡ ካዛብላንካ አጠገብ ሌላ ሆስፒታል ልንከፍት ነው፡፡ ከተሳካም ሌሎች በርካታ የማገገሚያ ማዕከላትን እንከፍታለን፡፡ በአፍሪካ የማገገሚያ መሪዎች መሆን እንፈልጋለን፡፡"

ይህ የቢቢሲ ተከታታይ ክፍል የተዘጋጀው ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡

#bbcinnovators