የዩኒቨርስቲ መምህርቷ ሞዴል ገነት ጸጋይ፡ "ውበት ባመኑበት ነገር ጠንክሮ መሥራት ነው"

የፎቶው ባለመብት, Genet Facebook
ገነት ለቤተሰቧ አስራ አንደኛ ልጅ ናት። አስራ ሁለት ልጆች ወልዶ ባሳደገው ቤተሰብ ውስጥ ታላላቆቿን አርዓያ እያደረገች ነው ያደገችው።
ስለቤተሰቧ ስትናገርም "ሁሉም ቆንጆ እንድሆን ይፈልግ ነበር" ብላለች ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር በነበራት ቆይታ።
የመቀለ ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል ተማሪ እያለች ነበር ወደ ቁንጅና ውድድር የተቀላቀለችው። ውድድሩን ግን ለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን ለማሸነፍ አልማ የተካፈለችበት ነበር።
ያሰበችው አልቀረም በ2003 'ወይዘሪት ትግራይ' ሆና ዘውድ ደፍታለች።
"ወይዘሪት ትግራይን ሳሸንፍ፤ ገና ከቤት የወጣሁበት ጊዜ ነበር። ውጪ ስላሉ ነገሮችና የህይወት ፈተናዎች የማውቀው ነገር አልነበረም" በማለት የምታስታውሰው ገነት፣ በቀጣዩ ዓመትም [2004] በአገር አቀፍ የቁንጅና ውድድር አሸንፋ 'ወይዘሪት ኢትዮጵያ' ተብላለች።
ከዚያ በኋላም ወደ ዓለም አቀፍ መድረኮች ተቀላቀለች።
"ለእኔ እነዚህ መድረኮች እጅግ ደስ የሚሉ ግን ከባድ ነበሩ። የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ስለነበርኩ፣ በመሃል ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተንቀሳቀሱ መስራት ቀላል አልነበረም።"
ገነት ጸጋይ በ'ሚስ ዎርልድ' የተካፈለችው ገና ተማሪ እያለች ነበር። በዚህ ምክንያትም በአሜሪካ በትልልቅ የፋሽን መድረኮች የመስራት እድል አግኝታለች።
ዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር መድረኮች፤ ዳጎስ ያለ ልምድና ችሎታ፣ የዳበረ አቅምና ልምድ ያላቸው ተወዳዳሪዎችና ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ነው። በዚህም የተነሳ ለተወዳዳሪውም ሆነ ለተሳታፊው የሚፈጥሩት ተጨማሪ እድል በርካታ የመሆኑን ያክል፣ ፈተናውም በዚያው ልክ የበዛ መሆኑን ትናገራለች።
"ከዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ነጥብ ስመረቅ፤ ሁሉም ሰው የትምህርት ውጤቴን ለማመን ይቸገር ነበር። ብዙ ጊዜ የቁንጅና ሥራዎች ላይ ነሽ፤ እንዴት ውጤትሽ እንዲህ ሊሆን ቻለ? ይሉኝ ነበር" የምትለው ሞዴል ገነት፤ "የምፈልገውን ለመሆን ቀን ከሌት እተጋ ስለነበር ስኬታማ መሆን ችያለሁ" ትላለች።
በአንዲት ወጣት ሴት ሕይወት ውስጥ፤ ከሕይወት ግብ የሚያሰናክሉ በርካታ አጋጣሚዎች ሊከሰቱ ቢችሉም፤ ተግዳሮቶቹን ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይሮ ማለፍ መቻልን ደግሞ ትልቁ ነገር እንደሆነ ትናገራለች።
"መሬት ላይ ያለው ሃቅ ለሴት ልጅ ቀላል ባይሆንም፤ ማንኛውንም ነገር ለመስራት ስነሳ መሰናክል ይሆንብኛል ብዬ የማስቀምጠው ነገር የለም።"

የፎቶው ባለመብት, Focus Studio/Genet Tsegay
ቁንጅና ምኑ ላይ?
በ2018 የዩክሬይን ወይዘሪት በመሆን ዘውዱን ያነሳችው ቬሮኒካ ዲዱሴንዶ፤ ልጅ እንዳላት ሲታወቅ ከአራት ቀን በፊት የተሰጣትን የቁንጅና ዘውድ ተነጥቃለች።
በዚህ ምክንያት የዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር ሕጎችን እንዲቀየሩ ሕጋዊ እርምጃ እንደምትወስድ በዚህ ሳምንት ገልጻ ነበር።
የ'ሚስ ወርልድ' ውድድር እናት ወይም ባለትዳር የሆነች ሴት በቁንጅና ውድድሮች እንዳትሳተፍ የሚከለክል ሕግ አለው።
ትዳር ወይም ወሊድ የሴት ልጅ ውበትና ቅርጽ ስለሚቀይሩ፣ የቤተሰብ ኃላፊነትን ስለሚጨምሩ፤ መድረኩ የሚፈጥራቸውን የበጎ ፈቃድ ሥራዎች፣ ፋሽንና ሌሎችን በቂ ጊዜና ትኩረት ሰጥተው ለመስራት ይገድባቸዋል ተብሎ እንደሚታመን፤ በኢንዳስትሪው የሚገኙ ቆነጃጅት ያነሳሉ።
"እንደዚህ አይነት አመለካከቶች የሴትን ልጅ ጥንካሬና ብርታት ጥያቄ ውስጥ ከሚያስገቡ ሰዎች የሚመነጩ ናቸው" የምትለዋ ሞዴል ገነት፤ ለሴት ልጅ "ኃላፊነትና ትዳርን ሳይሆን ማንኛውም ነገር ስንጀምር ፈልገነውና ልባችን ፈቅዶ ነው ወይ የምንጀምረው? የሚለውን ማወቁ ጠቃሚ ነው" ትላለች።
"ከሁሉም ይልቅ እኛን የሚገነባን ትምህርት ነው" የምትለው አርክቴክት ገነት፤ "የሚያዳግታት ነገር ሁሉ አሸንፋ ለመውጣት ማንኛዋም ሴት መማር አለባት። በዚህ መልኩ አስተሳሰባችን ስለሚያድግ መድረስ የምንፈልገው ስፍራ ለመድረስና ዓላማችንን ለማሳካት አቅም እናገኛለን" ብላ ታምናለች።
ሞዴልና አርክቴክት ገነት ጸጋይ፤ አሁን በተለያዩ የፋሽንና የቁንጅና መድረኮች ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ወጣት ሴቶች የምታሰለጥንበት ዓለም አቀፍ ተቋም አላት።
ይህ 'ኢትዮጵያን ቢዩቲ ክሪምስ' የተሰኘ ኩባንያ፤ በየዓመቱ የወይዘሪት ኢትዮጵያ ውድድሮችን በማዘጋጀት፤ በወይዘሪት ዓለም፣ ወይዘሪት ኢንተርኮንትነንታል፣ በወይዘሪት ግራንድ ኢንተርናሽናል፣ በወይዘሪት ኢንተርናሽናል ላይ የሚወዳደሩና የሚሳተፉ አራት ሴቶችን ይልካል።
እስከ አሁን፤ ወደ ፊሊፒንስ፣ ጃፓን፣ ኢንዶኔዥያና አሜሪካ ኩባንያው አወዳድሮ የመረጣቸውን ቆነጃጅቶች ልኳል።
"በቁንጅናው ኢንዳስትሪ ይህን ፈጥሬያለሁ። ውበት ግን ውጫዊው ብቻ ሳይሆን በራስ መተማመን ነው። ለእኔ፤ የራስ መተማመን ያላትና ራስዋን የምትችል ሴት ቆንጆ ናት። ትልቅ ውበት ብዬ የምወስደው ደግሞ ባመኑበት መስክ አብዝቶ መስራት ነው። ዓለም ላይ ከባዱ ነገር ፍላጎትን አለማወቅ ነው ብዬም አምናለሁ።"

የፎቶው ባለመብት, Genet Facebook
ገነት ጸጋይ ማን ናት?
አርክቴክት ገነት፤ በአሁን ወቅት ባለትዳርና የልጆች እናት ናት።
ባለፈው ዓመት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ'ላንድስኬፕ አርክቴክቸር' ሁለተኛ ዲግሪዋን ይዛለች። በዩኒቨርሲቲውም የአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል መምህርት ናት።
በሙያዋ ቤቶችን ማስዋብንና ዲዛይን ማድረግን ስትሰራ፤ ልብሶቿንም ራሷ ዲዛይን በማድረግ አዘጋጅታ ትለብሳለች።
"ሥራ ለመስራት ግን ውስጤ እስካመነበት ድረስ ቦታ አልመርጥም። በማህበራዊ ኑሮዬ እና ተማሪዎቼን ለማስተማር ስሄድ የተለያየሁ ሰው ነኝ። ውጪ ላይ ፋሽን እከተላለሁ፤ ሳስተምር ግን እንደማንኛውም ሰው ስለምሆን ተማሪዎች ብዙም አያውቁኝም። 'ፋሽን ላይ ያለ ሰው ግን እንዲህ በትምህርትም ስኬታማ ይሆናል እንዴ?' የሚሉኝ ሰዎች አሉ። "
በህይወታችን ውስጥ ልናገኘው የምንፈልገው ነገር በቀላሉ አይገኝም የምትለው ገነት "አላማዬን የሚያስተኝ ከሆነ ፈጽሞ ወደ ህይወቴ እንዲገባ አልፈቅድለትም" በማለት ህይወታቸውን በጥንቃቄ ከሚመሩ ሰዎች ጎራ መሆንዋን ትናገራለች።
"እናትነት ልዩ ተፈጥሯዊ ምስጢር ነው። ከራስ በላይ የሚኖርበት ምክንያት የሚሰጥ ጸጋ ነው። ብዙ ሰው ትዳር ሲመሰርት ሁሉም ጫና ሴቷ ላይ ነው የሚወድቀው ብሎ ይሰጋል። ለእኔ ግን እንደዚህ አይደለም፤ ምርጫችንና ውሳኔያችንን ነው የምንኖረው። ሴት ልጅ ራሷን የምትችል ከሆነ፤ አስጠጊ አያስፈልጋትም።"
















