ደቡብ አፍሪካዊቷ የዘንድሮው 'ሚስ ዩኒቨርስ' ቁንጅና ውድድር አሸነፈች

የፎቶው ባለመብት, Paras Griffin
ደቡብ አፍሪካዊቷ ዞዚቢኒ ቱንዚ የዘንድሮውን 'ሚስ ዩኒቨርስ' ቁንጅና ውድድር አሸናፊ ሆናለች።
ዞዚቢኒ አሸናፊ የሆነችው በተለያዩ ዙሮች ላይ ባደረገቻቸው አልባሳት፤ እንዲሁም ለቀረቡላት ጥያቄዎች መልሶች ዳኞችንና አድናቂዎቿን ማስደመም በመቻሏ ነው።
የፖርተሪኳዋ ማዲሰን አንደርሰንና የሜክሲኮዋ ሶፊያ አራጎን ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነዋል።
ዞዚቢኒ በጥያቄና መልስ ወቅት በዋናነት ለሴት ልጅ ጠቃሚው ነገር መሪነት ነው ብላለች።
"ለዘመናት በታዳጊ ሴቶችም ሆነ በአጠቃላይ ሴቶች የታጣው መሪነት ነው፤ ስለማንፈልግ ሳይሆን ማህበረሰቡ ሴቶች አይገባቸውም በሚል ስላስቀመጠው ነው" ብላለች።
ዞዚቢኒ በኢንተርኔትም ላይ አንድ ዘመቻ ጀምራ ነበር፤ ደቡብ አፍሪካውያን ወንዶች ለሴቶች የፍቅር ደብዳቤ እንዲፅፉላቸው።
እነዚህንም የፍቅር ደብዳቤዎች አሰባስባ በሃገሯ ሰንደቅ አላማ በታጀበ ባህላዊ ልብሷ ላይ አካታው ነበር።












