ኤም ቲ ኤን ለአልቃይዳና ታሊባን ጉቦ በመስጠት ተወነጀለ

አፍጋኒስታን

የፎቶው ባለመብት, AFP Contributor

በአፍሪካ ግዙፉ የሞባይል ኩባንያ ኤም ቲ ኤን አሸባሪ ለተባሉት ታሊባንና አልቃይዳ ቡድኖች ጉቦ በመስጠት በአሜሪካ ፌደራል ፍርድ ቤት ክስ ቀረበበት።

ኩባንያው ለእነዚህ ቡድኖች ገንዘብ የሰጠው አፍጋኒስታን ውስጥ የሚገኝና ትልቅ ኢንቨስትመንት ያደረገባቸው የኔትዎርክ ታዎሮች ላይ ጥቃት እንዳይደርስበት ለጥበቃ ነው ተብሏል።

በውንጀላው መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉ ሌሎች አምስት ኩባንያዎችም ያሉ ሲሆን ክሱ የቀረበው አፍጋኒስታን ውስጥ በተገደሉ የአሜሪካ ዜጎች ስም ነው።

በቀረበው ክስ እንደተባለው ሁለቱ አሸባሪ ቡድኖች ከኤም ቲ ኤን ያገኙትን ገንዘብ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2009 እስከ 2017 አፍጋኒስታን ውስጥ ላካሄዷቸው የጥቃት ዘመቻዎች ተጠቅመውበታል።

ይህ ደግሞ የአሜሪካን የፀረ ሽብር አዋጅን የሚፃረር ነው፤ ስለዚህም ኤም ቲ ኤን ይህን ህግ ተላልፏል ተብሏል።

ኩባንያው ግን በየትኛውም ቦታ ስራውን የሚያካሂደው ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንደሆነ ገልጿል።

ኤም ቲ ኤን በአፍሪካ ግዙፉ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከስምንት ትልልቅ ኩባንያዎች አንዱ ነው። ከ240 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች በላይም አለው ተብሎ ይታመናል።

በ2015 ያልተመዘገቡ ሲም ካርዶችን ባለመሰረዝ በናይጄሪያ ባለስልጣናት በቀረበበት ክስ 5 ቢሊዮን ዶላር እንዲቀጣ ተፈርዶበት፤ ከረዥም ክርክር በኋላ እንዲሁም የያኔው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮም ዙማ በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው ቅጣቱ ወደ 1.7 ቢሊዮን ዶላር እንደወረደለት የሚታወስ ነው።

የዛሬ ዓመትም በኢራን የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኤምቲኤን ኢራን ውስጥ እንዲሰራና የ 31.6 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት እንዲያሸንፍ ጉቦ ተቀብለዋል በሚል መታሰራቸውም ይታወሳል።