አልሸባብ በፈፀመው ጥቃት ሶስት አሜሪካውያን ተገደሉ

የሶማሌ አልሸባብ ተዋጊዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አልሸባብ በምስራቅ አፍሪካ ከባድ ጥቃት ለመፈፀም ዝቷል

አንድ የአሜሪካ ወታደር እንዲሁም ሁለት አሜሪካውያን ሠራተኞች አልሸባብ እሁድ ማለዳ በኬኒያ ላሙ በሚገኘው የኬኒያ-አሜሪካ ጥምር ወታደራዊ ካምፕ ላይ በባደረሰው ጥቃት መገደላቸው ተሰማ።

እስላማዊው አማፂ ቡድን፣ አል-ሸባብ፣ የኬኒያና አሜሪካ ጥምር ጦር ካምፕ ባደረሰው ጥቃት ሌሎች ሁለት የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት ተጎድተዋል።

"የተጎዱት ሰዎች በአሁኑ ሰዓት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ከአካባቢውም እንዲወጡ ተደርጓል" ሲሉ የተናገሩት የአሜሪካ አፍሪካ (አፍሪኮም) ጦር አዛዥ ናቸው።

የዓይን እማኞች በስፍራው ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ልውውጥ እንዲሁም ፍንዳታ የነበረ ሲሆን ጥቁር ጭስ ሲትጎለጎል መመልከታቸውን ገልፀዋል።

የአሜሪካ አፍሪካ (አፍሪኮም) አዛዥ ጄነራል ስቴፈን ቶውንሴንድ " በደረሰው ጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ አባላቶቻችን ቤተሰቦችና ጓደኞች መጽናናትን እንመኛለን" ብለዋል።

"የአባላቶቻችንን መስዋዕትነት እንዲሁ በዘበት የተከፈለ አለመሆኑን ለማሳየት እንዲሁም አሜሪካውያንና ጥቅሞቿን የሚነኩትን ዝም እንደማንል ለማሳየት ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን ጥቃቱን ያደረሰውን አልሻባብ ላይ ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን።"

በዚህ ጥቃት ከሰው ሕይወት በተጨማሪ ስድስት የንግድ አውሮፕላኖች ላይም ጉዳት ደርሷል።

አልሸባብ ከአልቃይዳ ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሲሆን መቀመጫውን በሶማሊያ ያደረገ ነው።

ቡድኑ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በቀጠናው የተለያዩ ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።

የዛሬ ወር ገደማ በሶማሊያ በፈጸመመው ጥቃት 80 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።

አልሸባብ እኤአ በ2017 በሶማሊያ በነበረው ውጊያ ላይ አንድ የአሜሪካ ወታደርን መግደሉ ይታወሳል።

በካምፕ ሲምባ የሆነው ምንድን ነው?

ከአልቃይዳ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው የሚነገርለትና መቀመጫውን በሶማሊያ ያደረገው አልሸባብ በደቡብ ምስራቅ ኬንያ ላሙ ከተማ የአሜሪካና የኬንያ ጥምር ወታደራዊ ካምፕ ላይ ጥቃት ፈጸመ።

አልሸባብ ጥቃቱን መፈጸሙን ከገለጸ በኋላ እርምጃው ከአሜሪካና ኢራን ቅራኔ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ አስታውቋል።

የኬንያ መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ኮሎኔል ፖል ንጁጉና እንደገለጹት አልሸባብ ጥቃቱን ሲያደርስ በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ አራት የቡድኑ አባላት ተገድለዋል።

የአልሸባብ ወታደሮች በአሜሪካና በኬንያ ወታደሮች ጥቅም ላይ የሚውለውን ወታደራዊ ሰፈር ለመቆጣጠር በማሰብ ጥቃቱን እንደሰነዘሩ ቃል አቀባዩ አክለዋል። በአካባቢው የነበሩ የአይን እማኞች እንደገለጹት ደግሞ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ የነበረ ሲሆን ከቆይታ በኋላ ደግሞ ከባድ የተኩስ እሩምታ ተከትሏል።

Map

ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ ጥቂት የነዳጅ ማጠራቀሚያ ቦቴዎች በመፈንዳታቸው ከባድ ፍንዳታና ጭስ አካባቢውን እንደሞላው ኮሎኔል ፖል ንጁጉና ገልጸዋል።

ሮይተርስ በበኩሉ አልሸባብን ጠቅሶ "ሰባት አውሮፕላኖችና ሶስት የወታደር መኪኖችን በጥቃቱ አውድመናል" ማለቱን ዘግቧል። ሮይተርስ አክሎም አውሮፕላኖች ሲቃጠሉ የሚያሳይ ምስል በአልሸባብ መግለጫ ላይ መመልከቱን ነገር ግን በገለልተኛ ወገን አለማረጋገጡን ጨምሮ ዘግቦ ነበር።

የአሜሪካ አፍሪካ ጦር (አፍሪኮም) አዛዥ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት በማንዳ ቤይ አየር ማረፊያ ላይ ጥቃት መድረሱን አረጋግጠዋል። ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነ በመግለጽም "መረጃዎች በዝርዝር እንደደረሱኝ አሳውቃለሁ" ብለወው ነበር።

በአሜሪካ ወታደራዊ ስፍራ ላይ መሰል ጥቃት ሲደርስ ይሄኛው ሁለተኛው ነው። ባለፈው ዓመት ከሶማሊያዋ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ምዕራብ በኩል በምትገኘው ባለተጎድል ከተማ የአሜሪካና የሶማሊያ ወታደሮች በጋራ የሚጠቀሙት ወታደራዊ ካምፕ ላይ ጥቃት ተሰንዝሮ ነበር።

ባሳለፍነው አርብ ደግሞ በዝችው የኬኒያዋ ላሙ ከተማ አልሸባብ አድርሶታል በተባለ የመኪና ላይ ጥቃት ሶስት ሰዎች ሲሞቱ ሁለቱ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚታወስ ነው።

ወደ ሞምባሳ በመጓዝ ላይ የነበረውን የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ አንድ ግለሰብ ካስቆመ በኋላ በርካታ ጥይቶችን እንዳርከፈከፈበት የአይን እማኞች ገልጸው ነበር።

ኬኒያ ወደ ሶማሊያ ጦሯን ያዘመተችው እ.አ.አ. በ2011 ሲሆን ለዚህም ምክንያቴ ነው ብላ የነበረው ከሶማሊያ ወደ ግዛቷ ድንበር እያቋረጡ የሚፈፀሙ ጥቃቶችና እገታዎች በመበራከታቸው ነበር።

በአሁኑ ሰዓት የኬኒያ ጦር በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ስር ሲሆን በምዕራባውያን የሚደገፈውን የሶማሊያ መንግሥት በመደገፍ የሠላም ማስከበር ሂደቱን ይሰራል።