የምርጫ ቅስቀሳ ወጎች

ድምጽ የሚሰጡ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የዘውዳዊው ሥርዓት ተገርስሶ፤ ደርግ 'ኢምፔሪያሊዝምን የማንበርከክ' የመሬት ከበርቴውን የማንቀጥቀጥ የቡርዧውና ፊውዳሉ ሥርዓትን የማውገዙ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች የሚሰበክበት ወቅት፤ በአንድ ወቅትም በሰሜን ኢትዮጵያ በምትገኝ ደሃና በምትባል አካባባቢ የደርግ ካድሬዎች የአካባቢውን ሕዝብ ሰብስቦ "የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ይውደም" በማለትም ጮክ ብለው መፈክሮችን ያሰማሉ።

ያው የተሰበሰበውም ሕዝብ " እኛ ምን አውቀን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ይውደም እንጂ" አሉ እየተባለ በአካባቢው ይወሳል።

ኢምፔሪያሊዝም፣ አናርኪስት፣ ቡርዧ፣ ሶሻሊዝም እንዲሁም ሌሎች ይደጋገሙ የነበሩ ቃላት ለሰው ባዕድ እንደሆኑ ዘመናትን ቀጥለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ መንግሥት የሚከተሏቸው ርዕዮተ ዓለማት፤ የሚያወጧቸው ፖሊሲዎች ወይም በተደጋጋሚ የሚሰሙ ቃላት እንደ ዴሞክራሲ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ግብርና መርህ ኢንዱስትሪ፣ ኒኦ ሊበራሊዝም እና ሌሎችም ከቃላት በላይ ምን ያህሉ ኢትዮጵያዊ ፅንሰ ሃሳቦቹን በጥልቀት ይረዳቸዋል?

በተለይም ምርጫዎች ሲቃረቡ በተለያዩ ሚዲያዎች በሚደረጉ ክርክሮች እነዚህን ፅንሰ ሃሳቦችና የተለያዩ የፖለቲካ ፕሮግራሞች መስማት የተለመደ ነው፤ እነዚህን ሃሳቦች ለሰፊው ሕዝብ እንዴት ይወርዳሉ? በምንስ መንገድ ይሰርፃሉስ? ድጋፍስ የሚያሰባስቡት እንዴት ነው የሚሉ ጥያቄዎችን ሊያጭሩ ይችላሉ።

የነዚህ ቃላትም ሆነ ፅንሰ ሃሳቦች ተመሳሳይ አገርኛ እሳቤስ የለም ወይ፤ ቃላቶቹ የተዋሱ ከመሆናቸው አንፃርና ገና ሲሰሙ ፊደል ያልቆጠረውን ማህበረሰብ የማግለል ስሜትስ አይፈጥሩም ወይ?

ካፒታሊዝም፣ ሶሻሊዝም የመሳሰሉ ሃሳቦችን፤ የፍራንዝ ፋኖንም ሆነ ማኦን ፅሁፎች ከልሂቃኑ በስተቀር አብዘኛው ማህበረሰብ ባያውቋቸውም የተማሪዎች እንቅስቃሴ 'መሬት ለአራሹን' በዋነኝነት አንግቦ መምጣቱ አርሶ አደሩንና በወቅቱ የነበረውን የተማረ ክፍል በአንድ ጎራም ያሰለፈ እንደነበር በወቅቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩት ዶ/ር ታዲዮስ ቦጋለ ያወሳሉ።

ከዘውዳዊው ስርአት መገርሰስ በኋላም ዕድገት በህብረት ዘምተው በነበረበት ወቅት በተወሰነ መልኩ የሕዝቡን ሥነ ልቦና ለማወቅ ዕድል ያገኙ ሲሆን የኢህአፓን ርዕዮተ አለም ለማስረፅ በሚሞክሩባቸው ወቅት ያጋጠማቸውን አሁንም ያወሱታል።

የቦረና ማህበረሰብ በተለይም ጉጂ ስለ ሶሻሊዝም ሆነ ኮሚዩኒዝም ርዕዮተ ዓለም ሲነግሯቸው ቃላቶቹን ባያውቋቸውም ፅንሰ ሃሳቦቹ አዲስ እንዳልሆኑ የነገሯቸውን በመጥቀስ።

"አብሮ መኖር ለኛ አዲስ አይደለም፤ ተሰባስቦ መኖርም ሆነ ያለውን ተካፍሎ መብላት፤ አብሮ መንቀሳቀስና ችግር ሲኖር ተሰባስበን ችግራችንን የመፍታት እነዚህ ቀድመው የነበሩ ባህሎቻችን ስለሆኑ የምትሉት ነገር አዲስ አይደለም። ለኛ ስለዚህ ጉዳይ ከምትነግሩን እኛ ኑሯችን እንዴት እንደሚሻሻል፣ መንገድ እንዴት እንደሚሠራ፣ ትምህርት ቤት እንዴት እንደሚሠራ፣ እነዚህን ነገሮች ነው በአብዛኛው የምንፈልገው እያሉ ነው ይሞግቱን የነበሩት" ይላሉ።

አንዳንድ ጊዜም እንዲህ ከተወሳሰቡ ሃሳቦች ሌላ ማሳካት የማይችሏቸውን ጉዳዮች ቃል በመግባት ብዙዎች ደግሞ የሚያወሷቸው ቀልዶች አሉ፤ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ ወቅት አንድ ሹም ሕዝቡን ምረጡኝ እያሉ ይቀሰቅሳሉ፤ እናም ከተመረጥኩ ይህን አደርጋለሁ፤ ይህን አደርጋለሁ ብለው ከሚዘረዝሯቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ "ድልድይ አሠራለሁ" ነበር።

የአካባቢው ሕዝብም ደግሞ "ድልድዩ ለምን ይሆን?" ብሎ መጠየቅ "ያው እንድትሻገሩበት ነው አሉ"፤ "ወንዝ እኮ በአካባቢው የለም" ሲሉ "ወንዙንም አመጣለሁ" ብለው መልሰዋል እየተባለ ፖለቲከኞች በምርጫ ወቅት ለመመረጥ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ይላሉ።

ብዙዎች የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትም የሚስማሙበት ጉዳይ ኢህአዴግ ምርጫ ሲቃረብ፤ የምርጫ ቅስቀሳው ወቅት እንዲሁ ለመመረጥ የማይሄድበት መንገድ እንደሌለ ነው። ሕዝቡን በጥቅማ ጥቅም ከመያዝ ጀምሮ፣ ማስፈራሪያዎች፣ መደለያዎችና እና እንዲሁም ሌሎችም፣ ሌሎችም።

ኢህአዴግ ስልጣን መያዝ ተከትሎ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ከሽግግር መንግሥቱ 1983 ዓ. ም. ጀምሮ በተቃዋሚነት የቆዩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በባለፉት ዓመታት ያደረጓቸውን ለፓርቲያቸው የሚደረጉ የድጋፍ ጥሪዎችንም ሆነ የምረጡኝ ቅስቀሳዎች ፈታኝ ነበሩ ይላሉ።

ይህ ፈታኝ ጉዞ የተጀመረው፤ በሽግግሩ ማግስት እንደሆነ የሚናገሩት ፕሮፌሰር በየነ በሽግግሩ ወቅት የቻርተሩን ጉባኤ አከናውነው የድጋፍ ጥሪ ለማድረግ ወደ ሆሳዕና ከተማ አቀኑ። በወቅቱም መቀስቀስ አትችሉም ተባሉ በዚህም ምክንያት ከመንግሥት ጋር ያላቸው ፍጥጫዎችና እሰጣ ገባ ሀ ተብሎ ተጀመረ።

የአካባቢው ማህበረሰብም አሻፈረኝ አለ መጀመሪያ ታስቦ የነበረው በአንዲት ጠባብ አዳራሽ ሊደረግ ታስቦ የነበረው ውይይት በትልቅ ስታዲየምም ተከናወነ።

በቦታውም ምንም እንኳን የሽግግር ጊዜ ከመሆኑ አንፃር ግድያዎችና ግጭቶች ከመበራከታቸው አንፃር የሰላምና የመረጋጋት ሁኔታ አስፈላጊነትን ቢያምኑበትም የኢህአዴግን ርዕዮተ ዓለምን በመቃወምና የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አስፈላጊነት ለሕዝቡ አስረዱ።

ለመምረጥ የተሰለፈ መራጭ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የተቃዋሚነትም ሕይወታቸውም ሀ ተብሎ ተጀመረ፤ ፖርቲያቸው እንዴት ከኢህአዴግ እንደሚለይ በፕሮግራማቸውም ሆነ በርዕዮተ ዓለማቸው ለማስረዳትም ከፍተኛ ሥራ መስራት ተጀመረ።

ሰፊውንም ሕዝብ በሚያገኙበት ሰዓት ለልሂቃኑ ብቻ የሚገቡ ፅንሰ ሃሳቦችንም ወደ ጎን በመተው የሚከተሉት ሶሻል ዴሞክራሲ (ማህበራዊ ዲሞክራሲ) ስለ ማኅበራዊ ፍትህ፣ የኃብት ክፍፍል፣ ዜጎች መሰረታዊ የሆነ ፍላጎታቸው እንዲሟላ፤ ሕዝቡ በሚገባው ቋንቋ በጤና፣ በትምህርት፣ በምግብ፣ በመኖሪያ ቤት ተደራሽነትን ማዕከል በማድረግ፤ የሕዝቡን ፍላጎትና ጭንቀቱን በዚያ መልክ እንደሚያቀርቡ ይናገራሉ።

"ያንን እምነት ወደ ሕዝቡ ማስተላለፉ ከባድ አልነበረም፤ ያኔም አልነበረም፤ አሁንም አይደለም" ይላሉ።

ከከተሜው አጀንዳዎች በተጨማሪ አርሶ አደሩ የምርት መጠኑን የሚያሳድጉባቸውን የምርጥ ዘር እንዲሁም የመሬትና ማዳበሪያ ጥያቄዎች ምርጫ ወቅት ላይ የሚነሱ ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው።

በተለያዩ ጊዜያትም በአርሶ አደሩ ዘንድ ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን እንደ መያዣ በማድረግ የምረጡኝ ቅስቀሳ ኢህአዴግ ይጠቀምበት እንደነበር የፕሮፌሰር በየነ ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተቃዋሚዎች ሲሉ በተደጋጋሚ ይሰማሉ።

"ተቃዋሚውን ከመረጣችሁ ምርጥ ዘርንም ሆነ ማዳበሪያ አንሰጥም ከሚሉ ማስፈራሪያዎች አልፈው፤ ሳይዘሩ መሬታቸው ፆሙን ያደረበት ሁኔታዎች፤ በጥቁር ገበያ እያወጡ እየሸጡ በብዙ እጥፍ ለመግዛትም የተገደዱ አሉ።

"የምትደግፉት የበየነ ጴጥሮስ ፓርቲ ሲመጣና ስልጣን ሲይዝ እናንተ ታገኛላችሁ፤ እንዲያውም በሄሊኮፕተር መጥቶ ያወርድላችኋል የሚሉና ወደ ኋላ የቀሩ መንግሥትን የማይመጥኑ ዘዴዎች ሁሉ ይጠቀሙ ነበር" ይላሉ።

ከዚህም በባሰ እርዳታንም ለምርጫ ቅስቀሳ ይጠቀሙባቸውም ነበር ይላሉ፤ በተለያዩ ጊዜ በሚከሰት የዝናብ እጥረት ምክንያት በሚከሰት የምግብ እጥረት የሚመጣው እርዳታ ለተቃዋሚ የድርጅት አባላት እንዲሁም ደጋፊዎች አይደርሳቸውም በማለት ይወነጅላሉ።

"በየነ ፓርቲ ሲያሸንፍ ያኔ ነው የምትበሉት ተብለው የእርዳታ እህል የሚከለከሉበት ኢሰብአዊ የሆነ ከሞራል መሰረት ውጭ ተግባራት ውስጥ ይገቡ ነበር" የሚሉት ፕሮፌሰር በየነ የአንዱ እርግማን ለአንዱ ምርቃት እንዲሉ እንዲህ አይነት "በደሎች" ድጋፍ ለማሰባሰብም ያመቻቸው ወቅት ነበር።

ማዳበሪያ እንዲሁም ምርጥ ዘር አንሰጥም የሚሉ ጉዳዮችም ህዝቡን እልህ አጋብተውትም እሳቸውም ሆነ ፓርቲያቸው የፖለቲካ ስራ ከሰሩበትና ከቀሰቀሱበት ሃድያ ዞንና ከምባታ ጠምባሮ 1992 ምርጫ ላይ ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ እንዲሸነፍበት ምክንያት የሆነው።

በ1992 ዓ. ም. ያሸነፉበትም የምርጫ ቅስቀሳም ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርን ለመስጠት ቃል በመግባት፤ ረኃብና የእህል ምግብ እጥረት ሲከሰት ደግሞ ያለው እርዳታ በፍትኃዊነት እንዲከፋፈል፤ የትምህርት ጥራት፣ ጤና ማዕከላት እንዲቋቋሙ የሚሉ ጉዳዮችን አንግበው ነበር።

በምርጫ ቅስቀሳቸውም ወቅት ሕዝቡም እሮሯቸውን ይነግሯቸው የነበረ ሲሆን፤ በተደጋጋሚም "ልማት አምጡልን፤ የመሬት እጥረትን ቅረፉልን፤ ኑሯችንን አቅልሉንም" ይሉ ነበር።

ምንም እንኳን የሕዝቡን ኑሮ በሚነካ መልኩና የገዥውን ፓርቲ ስህተቶች እየነቀሱ በማውጣት የምርጫ ቅስቀሳቸውን ቢያካሂዱም አባላቶቻቸው ከፍተኛ መዋከብ፣ ቀስቃሾች መታሰር፣ መገረፍ እንዲሁም በሌሎች ጥሰቶች ውስጥ መሆኑንም ፕሮፌሰር በየነ ምሳሌዎችን በማንሳት ይጠቅሳሉ።

አብዛኛውን ጊዜ ለምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጓቸው የስብሰባ አዳራሾች ሕዝብ እንዳይገባ መከልከል፤ በታጠቀ ኃይል መበተን አንዳንዴም ረዥም ኪሎ ሜትር ተጉዘው ሆቴሎች አታድሩም ተብለው መከልከል አጋጥሟቸዋል።

የምርጫ አስፈጻሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

"ለምርጫ ቅስቀሳ በሚል ቀድመን ሆቴል ይዘን ልክ እኛ መሆናችንን ሲያውቁ የለም፤ ተከራይቷል ይሉናል። እኔም ይህ ሁኔታ አጋጥሞኛል። ማደሪያ አጥተን ደጋፊዎቻችን ደሳሳ ጎጆዎቻቸውን የለቀቁበት አጋጣሚም አለ፤ ምን ይባላል ትውስታዎቼ መራር ናቸው" ይላሉ።

ብዙዎቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በቅስቀሳዎቻቸው ወቅት ይደርስብናል የሚሏቸውንም ግፎችም በተደጋጋሚ መስማት የተለመደ ነው።

የኢህአዴግን መምጣት ተከትሎ በአማራው ሕዝብ ከሌላው ብሔር በተለየ መልኩ በደል ይደርስበታል የሚል አላማን አንግቦና ይህንንም ለመቅረፍ እታገላለሁ ሲል የነበረውና በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የተቋቋመው የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) አባል የነበሩት ዶ/ር ታዲዮስ መጀመሪያ አካባቢ ለድጋፍ መውጣት የማይቻል ነበር ይላሉ።

አብዛኛውን ጊዜ መአህድ የድጋፍ እንቅስቃሴው የተገደበ እንደነበር የሚናገሩት ዶ/ር ታዲዮስ ፕሮፌሰር አስራትም የተወነጀሉት አስፈቅደው ደብረ ብርሃን ላይ ባደረጉት ስብሰባ መሆኑንም በማስረጃነት ይጠቅሳሉ።

ባገኟትም አጋጣሚዎችም ለድጋፍ በወጡበት ወቅት ከደጋፊዎቻቸው ዘንድ በብሔር ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝምን እንደማይደግፉ፣ ፓርቲያቸውንም ህብረ ብሔር ማድረግ እንደሚገባ ስለወተወቷቸውም የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያሰባስብ ፌደራሊዝም ለምን አይቀየስም በሚል ድርጅቱም ውስጥ ከፍተኛ ውይይት ካደረጉ በኋላ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን መሰረቱ።

ከኢህአዴግ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውም ሆነ በሌሎች ዘርፎች የሚለዩባቸውን ሁኔታዎች በጥልቀት ቢሰሩበትም ህዝቡ ተረድቶታል ላይ የሚለው ላይ ጥያቄ አላቸው።

"ስንቱ ነው ስለ መንግሥት አደረጃጀት፣ የፖለቲካ አወቃቀር የሚያውቀው፣ የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ ስለ ብሄረሰቦች እኩልነት ፅንሰ ሃሳቦች ብዙዎች ጠንቅቀው አያውቁም፤ የመሬትና ሌሎች የተፈጥሮ ባለሃብት ባለቤትነት፣ የልማት አካሄድ፣ የውጭ ፕሮግራምና ሌሎችም አሉ፤ ምን ያህሉ ያውቀዋል ማለት ከባድ ነው።" ይላሉ

ፕሮግራማቸውንም ሆነ ፖሊሲዎቻቸውን ለሰፊው ሕዝብ ግልፅ አለመሆናቸው እንዲሁም የሰው ልጅ ኑሮው እንዴት መሻሻል ይችላል የሚለው በነዚህ ርዕዮተ ዓለማት ሲተገበር ምን ይመስላል? በሚልም ከፅንሰ ሃሳብ በዘለለ መንገድ ለማስረዳትም እንደሚሞክሩ ዶ/ር ታዲዮስ ይገልፃሉ።

መነሻቸውም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ላይ ያሉ ጉድለቶችን ነቅሶ ማውጣት እንደመሆኑ መጠን ለምሳሌ የመሬት ባለቤትነት ለአርሶ አደሩ ማረጋገጥ፣ ማዳበሪያ በቀላሉ የሚገኝበት ሁኔታ እንደሚያሳልጡ ያነሳሉ" እኛ ለምሳሌ ብንመረጥ ማዳበሪያ ፋብሪካ እናቋቁማለን፤ ለሕዝቡም በቀላል ዋጋ እንዲሰራጭ ይደረጋል እንላቸዋለን" ይላሉ

የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ድህነት አረንቋ ውስጥ ያለ ሕዝብ ከመሆኑ አንፃር የሰውን ችግርና ቁስል የሚነኩ ነገሮችንም በሚናገሩበት ወቅት የሕዝቡ ስሜትም ወደነሱ ቢሆንም ያ ቀጣይነት እንደሌለውም አስተውለውታል።

"ዋነው ነገር ለሕዝቡ ካለበት ድህነት እንዴት ነው የምወጣው የሚለው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። እናም በሚደረጉ ስብሰባዎች ስሜታዊ የመሆንና ያንን ነገር የመከተል፤ ያ ወቅት ደግሞ ሲያልፍ የመተው፤ ቦግ፣ ብልጭ የማለት የመተው ነገር አለ" ይላሉ።

ፕሮፌሰር በየነም ሆነ ዶ/ር ታዲዮስ አፅንኦት ሰጥተው የሚናገሩት የምርጫ ቅስቀሳቸውም ሆነ የድጋፍ ጥሪያቸው ወከባ የተሞላበት መሆኑን ነው። የሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሾች ተከራይተው ሊገቡ ሲሉ ተይዟል መባል፣ ሕዝቡ ወደ አዳራሾቸ በሚመጣበት ጊዜ የሚመዘግቡ ካድሬዎች ማቆም፤ ቀበሌ ትፈለጋለህ ብሎ ከስብሰባ አዳራሹ መውሰድና ሌሎችንም ይጠቅሳሉ።

"አዳራሹም እንደምንም ተብሎ ከተገኝም ካድሬዎች ይረብሹና ስብሰባው እንዲቋረጥ ይደረጋል፤ በተለያየ ዘዴ፤ እኛም ይህንኑ ዘዴያቸውን ስለምናውቅ ተዘጋጅተን ነው የምንጠብቃቸው፤ ሕዝቡም ያውቃል፤ ቀበሌ አዳራሸ ላይ ውይይቶች ሲበተኑ ህዝቡ ቅሬታውን እየተናገረ ይወጣል" ይላሉ።

መራጮች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

ሆኖም በአዳራሽም ሆነ፣ በራሪ ወረቀቶችን በማደል፣ በመኪናም እየዞሩ የመኖሪያ ቤቶችን ችግሮች እንደሚቀርፉ፣ የግል ባለቤትነትንም እንደሚያረጋግጡ በሰፊው ሰርተዋል።

ሕዝቡም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅታቸው ወቅት ይሰጣቸው የነበረው ድጋፍም ከፍተኛና ተስፋቸውንም ያንሰራራ ነበር።

በአንድ ወቅት ወደ ጋሞጎፋ ሳውላ የሚባል ቦታ ስብሰባ ለማድረግ ባቀኑበት ወቅት ባነራቸውም ከተማው መሃል ተሰቅሎ ስለነበር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ወጥቶ በዘፈን ያቀልጠው ጀመር "መኢአድ ለዘላለም ይኑር፤ መኢአድ ያሸንፋል፤ መኢአድ የኛ ነው " የሚሉ መፈክሮችን ያሰሙበትን ሁኔታ አሁንም ዶ/ር ታዲዮስ ትናንት የተፈጠረ በሚመስል መልኩ ያስታውሱታል።

ምንም እንኳን የሕዝብ ድጋፍ ከፍተኛ ቢሆንም ኢህአዴግ በከፍተኛ ሁኔታ በሚያደርጋቸው መደለያዎችም ጫና እንዳሳደሩባቸውም ዶ/ር ታዲዮስ ይናገራሉ። በገጠር ያለ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲሁም በከተማውም ላሉ ደሃ እናቶች ለቡና ተብለው የሚሰጥ ብር እንዲሁም ተደጋጋሚ ግብዣዎች ለውጥ እንዳለው ነው።

"ያው እንግዲህ ምርጫ ሲመጣ እናቶች ያው አንቺ የምታራምጅውን አላማ አይደለም የሚመለከቱት፤ እነሱ የሚያዩት ካለው የኑሮ ችግር የቡና መግዣ ማግኘታቸውን ነው" ይላሉ።

የኢዜማ ሥራ አስፈፃሚና በአንድ ወቅት አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህን ወክለው ብቸኛ ተቃዋሚ የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው ኢህአዴግ በምርጫው ሰሞን ወቅት ኢህአዴግ በእያንዳንዱ ጓዳ ጎድጓዳ መግባት እንደቻለ ነው።

"ጋዝ የምትፈልግ ከሆነ ጋዝ፤ ለዛ ሰሞን ምንም ችግር የለውም። አንዷ ሴትዮ አስታውሳለሁ መርጠው ሲወጡ 'የታለ የጋዙ ገንዘብ' ብለው በሳቅ ገድለውናል እና በደንብ ነው የሚደርሷቸው" በማለት ተቃዋሚዎች ህዝቡን ይደርሳሉ ወይ? ለሚለው ጥያቄም "እንዴት አድርገው ነው የሚደርሱት ሊደርሱ አይችሉም" ይላሉ።

"በያንዳንዱ ቤት ውስጥ የሚመርጣቸውንም ስለሚያውቁ ተንከባክበው ነው የሚይዙት፤ የቀበሌ ሰዎችም እነማን እንደሚመርጡ በዝርዝር ያወቃሉ" ብለዋል።

ምንም እንኳን እንዲህ በየቤቱ መድረስ ባይችሉም በዓመታት ውስጥ ለየትኛው አካባቢ ምን አይነት መልእክት ነው በሚልም ሰፊ ከሆነ መልዕክት ወደታች በሚወርድ መንገድ በያንዳንዱ ቤት ውስጥ ሊገባ በሚችል መልኩም ቅስቀሳ አድርገዋል።

ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ከሆነ በራሪ ወረቀቶች ያዘጋጃሉ፣ ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ በመኪና ላይ የሚደረጉ ቅስቀሳዎቸን ለማከናወን የተቀዱ የድምፅ መልእክቶች ይተላለፋሉ።

"መድረክን ምረጡ፤ መድረክን ስትመርጡ ነፃ ትወጣላችሁም" ይላሉ።

ጠጅ ቤቶች የመሳሰሉ የሕዝቡ ቦታዎች ፎርማል የሆነ ቅስቀሳ ባይኖርም በራሪ ወረቀቶች ሰጥተው ይመለሳሉ ምናልባት ቤታቸው ሆነው ቢያነቡት በሚል ቢሆንም፤ አንዳንዶች ግን እዛው አይተው ወዲያው ጥያቄ እንዲሁም ንግግሮችን ይጀምራሉ፤ ውይይቶችም ቦታው ላይ ይጦፋሉ፤ ከግል ጉዳይ ጀምሮ እሰከ የአገሪቱ ፖለቲካ ውጥንቅጦች ይነሳሉ።

በተቻለ መጠን በሰውኛ ቋንቋ፣ ሰው በሚረዳው መንገድ ቢያስረዱም የአገሪቱን አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ በማየት ጉንጭ አልፋ ክርክሮች ይበዛባቸዋል ይላሉ።

"በኛ አገር እንዳለመታድደ ሆኖ ስለ ፌደራሊዝምና የብሔር ብሄረሰቦች ጥያቄ ብዙውን ነገር ይሸፍነዋል፤ ተጨባጭ የማይሆኑና ለሕዝቡ ውስብስብ የሆኑ የልሂቃን ውይይቶች ይደረጋሉ። በሚዲያዎችም ላይ ሕገ መንግሥታዊ የሚል ጠቅላላ ርዕስ ይመጣና ሕገ መንግሥት አተረጓጎም ጭቅጭቆች ውስጥ በመግባት፤ ሰብአዊ መብት እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ ግንባታ የሚሉ የፅንሰ ሃሳብ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ጉንጭ አልፋ ክርክሮች ይካሄዳሉ" ይላሉ።

ለምሳሌ ለአዲስ አበባው ነዋሪ ትኩረት መሰጠት የሚገባቸው ጉዳዮች የመጠጥ ውሃ ችግር፣ የትምህርት ቤት ዋጋ ማነት፣ ራስ ምታት የሆነው የቤት ኪራይ ብዙ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና መከራከሪያ ሲሆኑም አይሰሙም።

ከተወሳሰቡ ሃሳቦች በተጨማሪ የአካል ጉዳተኞች፣ የኤች አይ ቪ ህሙማን እንዲመዘገቡና እንዲመርጡ፤ ለሕይወታችሁ ዋጋ ስጡ የሚሉ መልእክቶች ያሉበት በራሪ ወረቀቶች ሊበተኑ ሲሉ ስማቸውን መጥራት የማይፈልጉ አንድ ፖለቲከኛ እንዲህ አይነት መልዕክት አይተላለፍም አሻፈረኝ ብለው ሁሉንም ሰዎች በእኩል የማስተናገድ ቦታ እንደሌላቸውም ያሳያቸውን ጊዜም ያስታውሳሉ።

በምርጫ ቅስቀሳዎች ውስጥ ለሚደረጉ የትራንስፖርት፣ በራሪ ወረቀቶችን እንዲሁም ሌሎች ወጭዎች የብዙ ፖለቲካ ፓርቲዎች ራስ ምታት እንደመሆኑ መጠን ፓርቲዎችም ወጭዎቻቸውን ለመሸፈን ከመገደዳቸው አንፃር በአንዳንድ አጋጣሚዎችም ፈረሱን ሽጦ የተወዳዳረ እጩና የእርሻ በሬውን ሽጠው የተወዳደሩ እንዲሁም ሌሎችንም መስዋዕትነቶችን መከፈላቸውን ፕሮፌሰር በየነ ይጠቅሳሉ።

በሌሎች አገራት በሚደረገው አቅም ያላቸው ሰዎች ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ እንደማያደርጉም ፕሮፌሰር በየነ ይናገራሉ።

"የኢትዮጵያ ሃብታሞች ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ አያደርጉም፤ ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ ብለው ነው የሚፈሩት፤ ሌላው ቀርቶ እኛን በአደባባይ ቆመው ሰላምታ እንኳን መስጠት ያስፈራቸዋል። አይደፍሩም" ይላሉ

People queuing to vote

የፎቶው ባለመብት, AFP

የ1997 ምርጫ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የ1997 ዓ. ም. ምርጫ እንደ ትልቅ ምዕራፍ ይታያል በነበሩት የጦፉ ውይይቶችና መድረኮች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጣምረው በአንድ ግንባር መምጣትና በምርጫ ቅስቀሳዎች።

በ1992 ዓ. ም. የነበረውን የሃድያ ድል አንድ ተሞክሮ ሆኖ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ቢያስተባብሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ኢህአዴግን ማሸነፍ ይቻላል በሚል በውጭ አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም ክልል አቀፋዊና አገር አቀፋዊ ፓርቲዎቸን በማስተባበር የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ህብረት በሚልም አስራ አምስት ፓርቲዎች በአንድ መድረክ የመጡት በ1997 ዓ. ም. ነበር።

በመኢአድ አስተባባሪነት አራት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘውን ቅንጅት የተፈጠረውም በዚሁ በ1997 ዓ. ም. ነበር።

ወቅቱም አብዛኛው የአለም አቀፍ ማህበረሰቡም የመድብለ ፓርቲ ስርአት እንዲገነባ ብዙ ከመጣሩ አንፃር፤ ኢህአዴግ የምርጫውን ሜዳ ክፍት ማድረግ አለበት የሚሉ ግፊቶችም እንደነበሩ የሚያወሱት ፕሮፌሰር በየነ የተለያዩ አለም አቀፍ መንግሥታት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ብዙ ድጋፎችን አድርገዋል።

በ1997ቱም ምርጫ መላውን ኢትዮጵያ ለማዳረስ ተንቀሳቅሰዋል። ሶማሌ ክልል የተወሰኑ ችግሮች ስለነበሩ በዛ በኩል መንቀሳቀስ ባይችሉም በትግራይ፣ አማራ ክልል፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ወጭዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መኪኖች ተከራይተው፤ ትልልቅ 'ሜጋ ፎን' ከላዩ ላይ አድርገው፤ በየከተማው ስብሰሰባዎችን በመጥራት ቅስቀሳዎችን አድርገዋል።

ከአለም አቀፉም ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ ይደረግ ስለነበር የምርጫ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ለሁለት ወራትም ያህል ቀን ተሌት ሳይሉ ቀስቅሰዋል።

ተፋዞና በፍርሃት ተሸብቦ የነበረው ፖለቲካ ያንሰራራበት ክርክሮች ባልተለመደ መልኩ ቀደም ብለው የተጀመረበት ጊዜም ነው።

በተቀናጀ መልኩ ከፍተኛ ቅስቀሳ የተደረገበትም ጊዜ እንደሆነም ሶስቱም ፖለቲከኞች ይስማማሉ። በዚህም ውጤታማ መሆን እንደቻሉ ፕሮፌሰር በየነም ሆነ ዶ/ር ታዲዮስ አስምረው የሚናገሩበት ነው። እንደ ምሳሌም ደ/ር ታዲዮስ ከተወዳደሩበት ልደታ ክፍለ ከተማ ከተመዘገበው 26ሺ መራጭ ሲሆን እሳቸውም ወደ 24 ሺ አካባቢ አግኝተዋል።

መጪው ምርጫ

ከአስራ ስምንት ወራት በፊት የመጣው ለውጥ እንደ አንድ እመርታ የሚያዩት ዶ/ር ታዲዮስ በምርጫው ሃገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ ሊካሄድ አይገባም ከሚሉ ወገኖች ናቸው። በየቦታው ግጭቶችና ግድያዎች ተበራክተዋል፣ መንቀሳቀስ አይቻልም፣ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ሕዝብን በአዳራሽ መሰብሰብ፤ ሕዝብን ማግኘት እንደሚያስፈልግም ሳይታለም የተፈታ በመሆኑ እሱን ማድረግ ከባድ ነው ይላሉ።

"ሕዝቡን ለማግኘት የፀጥታው ሁኔታ ከባድ ስለሆነ፤ ፕሮግራም ሳይነገር፣ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊሠራ የሚገባው ጉዳይ ምንም ሳይባል ምርጫው እንዴት ሊካሄድ ይችላል?" የሚል አቋም ነው ያለን

ፕሮፌሰር በየነ በበኩላቸው አሁን ካለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ አለመረጋጋቶች በመኖራቸው እንቅስቃሴያቸውን የገደበው ሲሆን የምርጫ ቅስቀሳቸውም ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንደሚፈጥር ያስባሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ግን አለም አቀፍ ማህበረሰቡና መንግሥታት በአሁኑ ሰዓት ስልጣን ላይ የወጣውን ቡድን ያለ ጥያቄ ድጋፍ የሚያደርግበት ጊዜ ፈተና እንደሚሆንባቸውና ከዚህ ቀደም የነበሩ ድጋፎች በሙሉ ታጥተዋል ይላሉ።

"1997ን ብንወስድ በወቅቱ የነበረው የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ለውጥ ይፈልግ ስለነበር ይደግፈን ነበር፤ እንዳሁኑ ስልጣን ላይ ያለውን አካል በጭፍን መደገፍ አልነበረም" ይላሉ

ኢዜማ በበኩሉ በተለየ መልኩ ለአዲስ አበባ ማኒፌስቶ እያዘጋጀ ሲሆን በዚህ ዘመን የምርጫ ቅስቀሳውን ደግሞ ለየት የሚያደርገው ማኅበራዊ ሚዲያን በሰፊው ለምርጫ ቅስቀሳ ሊጠቀሙ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ነው። እያንዳንዱ እጩ የራሱም ገፅ ይኖረዋል፤ በፌስቡክም የምረጡኝ ቅስቀሳ መልዕክትም የሚያስተላልፍ ይሆናል።