ሲዳማ: 10ኛው የኢትዮጵያ ክልል

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሲዳማ ዞን ቀጣይ ዕጣ ፈንታን ለመወሰን ረቡዕ ዕለት በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ዞኑ የአገሪቱ 10ኛው ክልል የመሆን ድምጽ ማግኘቱን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
በዚህም መሰረት በሕዝበ ውሳኔው በመሳተፍ ከተመዘገበው ህዝብ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት፤ ማለትም 98.51 በመቶው ዞኑ ክልል እንዲሆን የሚያስችለውን ድምጽ ሰጥተዋል።
በሕዝበ ውሳኔው ውጤት መሰረትም እስካሁን ድረስ ዞኑን በስሩ አድርጎ ሲያስተዳድረው የቆየው የደቡብ ክልል ኃላፊነቱን አዲስ ለሚመሠረተው የሲዳማ ክልል ያስተላልፋል።
ዋና መቀመጫውን በሲዳማ ዞን ውስጥ በምትገኘው በሐዋሳ ከተማ ያደረገው የደቡብ ክልል ለሁለት የምርጫ ዘመን ያህል መቀመጫውን ከአዲሱ የሲዳማ ክልል ጋር ተጋርቶ እንደሚቆይ ቀደም ሲል ተገልጿል።
በሕዝበ ውሳኔው መሠረት አዲስ የሚመሠረተው የሲዳማ ክልል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አንድ አባል ይሆናል።
የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 47 አንድ ክልል ክልልነቱ የሚረጋገጠው ሃሳቡ ለምክርት ቤት ቀርቦ በሕዝበ-ውሳኔ አብላጫ ድምፅ ሲያገኝ ነው።
ረቡዕ [ኅዳር 10/2012] በተደረገው ሕዝበ-ውሳኔ ለመሳተፍ ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ ነበር ድምፅ ሰጭዎች ወደ ምርጫ ጣብያዎች መጉረፍ የጀመሩት።
ውጤቱ ሐሙስ ቢበዛ አርብ ይታወቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻውን ኦፊሴላዊ ውጤት ትላንት፤ ቅዳሜ [ኅዳር 13/2012] ይፋ አድርጓል።
ምርጫው ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ መጠናቀቁ ቢነገርም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አባል የሆነ አንድ ግለሰብ ምርጫውን ሊያስተጓጉል ሲሞክር ይዤ ለፖሊስ አስረክቤያለሁ ሲል አሳውቆ ነበር።
የምርጫውን ውጤት ተከትሎ ሌሎች ክልሎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሲዳማ ሕዝበ-ውሳኔ ውጤት የተሰማቸውን ደስታ ሲገልፁ ነበር።
ለሲዳማ ክልልነት ድምፃቸውን የሰጡ ሻፌታን፤ ሲዳማ ከደቡብ ክልል ጋር ይቆይ ያሉ ደግሞ ጎጆን በመረጡበት በዚህ ሕዝበ ውሳኔ የምርጫ ጣብያዎች አንሰዋል ተብሎ መጀመሪያ ተመድበው ከነበሩት 1692 የምርጫ ጣብያዎች ተጨማሪ 169 ጣብያዎች ተቋቁመው ነበር።
ምንም እንኳ 99.8 በመቶ ሻፌታን ቢመርጡም 1.48 በመቶ ወይም 33463 ሰዎች ድምፃቸውን ለጎጆ ሰጥተዋል። 18351 የምርጫ ካርዶችን ደግሞ ዋጋ አልባ ሲል የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከጥቅም ውጭ አድርጓቸዋል።
ውጤቱን ተከትሎ በሐዋሳ እና በሌሎች የሲዳማ ዞን ሥፍራዎች ነዋሪዎች ደስታቸውን ሲገልፁ ነበር።













