ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ቀጣዩ ምርጫ ግልጽ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንደሚሆን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, PM Office FB
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ቀጣዩ ምርጫ በማያጠራጥር ሁኔታ ግልጽ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንደሚሆን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በተፈራረሙበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አክለውም "ሕዝቡ ከዚህ በኋላ የሚፈልገውን ሃሳብ ያቀረበለትንና የሚፈልገውን አካል የመምረጥ እድል አለው" ሲሉ የመጨረሻው ውሳኔ የሕዝቡ መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርቲዎቹም ቀጣዩ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ነፃና ግልፅ እንዲሆን በትብብር ለመስራት እንዲሁም ከወራት በኋላ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው ምርጫ በክልሉ ውስጥ መካሄድ ባለበት ሁኔታ ላይም በጋራ ተመካክሮ የሚያስማማ ውሳኔ ላይ ለመድረስም ከስምምነት መድረሳቸው ተነግሯል።
በጋራ ለመስራት ስምምነቱን የፈረሙት የኦዲፒ ሊቀ መንበር እና የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ፣ የኦዲፒ ምክትል ሊቀ መንበርና የመከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ፣ የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ የኦፌኮ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የኦዴግ ሊቀ መንበር አቶ ሌንጮ ለታን ጨምሮ ሌሎች ኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ናቸው።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲዎች ፓለቲካውን ወቅቱን በሚጠይቅ መልኩ በማዘመን ከመጠፋፋትና ከመወጋገዝ በመውጣት "በሀሳቦች ላይ በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ፍላጎታችንን ከግብ ማድረስ እንችላለን" ሲሉ ተናግረዋል።
በፖለቲካ ፉክክር ምክንያት በሕዝቡ ላይ ምንም ዓይነት ስቃይና ጉዳት መድረስ የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ "ሀሳባችንን በሰላማዊ መንገድ እየተወያየን መስራት እንችላለን የሚለው ትልቅ ሀሳብ ነው" ሲሉ እርምጃውን አድንቀዋል።
ጨምረውም አሁን በኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት የተጀመረው የምክክር መድረክ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች መስፋት እንዳለበት አመክልተው አብሮ በመስራት ሀገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚቻል በመወያየትና በመመካከር መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ከአስርት ዓመታት በፊት በሕዝቡ ዘንድ ሲነሱ የነበሩትን ጥያቄዎች በዚህ ዘመን ይዞ መቅረብ ከጊዜው ጋር እንደማይሄድ ጠቅሰው "እንደ ሀገር ትልቅ ኃላፊነት የወሰደውን ለተቀበለ ሕዝብ አዲስ ሀሳብ በማምጣት ሀገሪቱን ማሸጋገር እንደሚያስፈልግና ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጠና ውስጥ ተገቢውን ሚና መጫወት ይጠበቃል" ብለዋል።
ፓርቲዎቹ በደረሱት ስምምነት የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በቅንጅት ለመስራት የሚያስችልና አመራሮችን በአንድ የሚያሰባስብ አካል በመመስረት በመካከላቸው የሚከሰቱ አለመግባባቶች በዚሁ አካል በኩል መፍትሄ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ተገልጿል።
በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆኑ ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ጥሪ ቀርቧል። ፓርቲዎቹም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በማስቆም ሰላምን ለማስፈን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።















