ከቤተሰቧ ጋር የሞተችው የ12 ዓመት ታዳጊ አሳዛኝ ቪድዮ

የፎቶው ባለመብት, Family handout
ባለፈው ወር ከቤተሰቧ ጋር የእንግሊዝ ሰርጥን ለመሻገር ስትሞክር የሞተች ኢራናዊት-ኩርድ ታዳጊን የሚያሳይ ቪድዮ ተሰራጭቶ ነበር።
በቪድዮው የ12 ዓመቷ ታዳጊ እየሳቀችና እያለቀሰች "ስሜ አኒታ ኢራንጃድ ነው። የተወለድኩት ሳራዳሳሀት ነው" ትላለች።
ቪድዮው በትውልድ አገሯ ለሚዘጋጅ የአጭር ፊልም ውድድር የተዘጋጀ ነው። ቪድዮው ላይ አባቷ ከኋላ ሆኖ ሲያበረታታት ይሰማል።
"ተዋናይ መሆን እፈልጋለሁ" ትላለች አኒታ በቪድዮው።
ቪድዮው ቤተሰባዊ መደጋገፍ፣ ተስፋ ይታይበታል።
አባቷ ራሱል ልጁ ህልሟን እንድታሳካ ይመኛል።
ግን ቀዬያቸው የተጨቆነና በግጭት የሚናጥ ነው። በምዕራብ ኢራን ኩርዶች በብዛት የሚኖሩባት ሳራዳሳሀት ነው የተወለዱት።
ታዳጊዋ ቪድዮውን ለውድድር ካስገባች ከዓመት በኋላ አባቷና እናቷ ከሦስት ልጆቻቸው ጋር ወደ አውሮፓ ጉዞ ጀመሩ።
አኒታ፣ የስድስት ወሩ አርሚን እና የ15 ወሩ አርቲን ከቤተሰቦቻቸው ጋር የጀመሩት አደገኛ ጉዞ ነበር።
ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ይጓዝ የነበረው አነስተኛ መርከብ ጥቂት እንደተጓዙ ተገለበጠ። ተሳፋሪዎቹ ነፍስ አድን ጃኬት አላደረጉም ነበር።
የትውልድ መንደራቸው በሕይወት ለመቆየት ከሚደረግ ትግል ባለፈ ህልም የሚሳካበት አይደለም።
ብዙዎች ሥራ አጥ ናቸው። ወደ ኢራቅ ኩርዲስታን ድንበር በሕገ ወጥ መንገድ ቁሳቁስ በማዘዋወር የሚተዳደሩም ብዙ ናቸው። ትርፋማ ግን አይደሉም።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካቶች በኢራን ድንበር ጠባቂዎች ተገድለዋል፤ የቆሰሉም አሉ።
"ሀዘን ልቤን ቢሰብረውም ኩርዲስታንን ትቼ ከመሄድ ውጪ አማራጭ የለኝም"
እአአ ከ1979ኙ የኢራን አብዮት ወዲህ በኢራን የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎቹ ኩርዶች መካከል ግጭት አልቆመም።
ኩርዶች ለመብታችን እየታገልን ነው ሲሉ ኢራን ደግሞ በውጪ ኃይሎች የሚደገፉ ተገንጣዮች ትላቸዋለች።
ከኢራን 10 በመቶው ኩርዶች ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፤ አብላጫውን ቁጥር የያዙት እስረኞች እነሱ ናቸው።
አምና ጸረ መንግሥት ተቃውሞ ከተካሄደ በኋላ ከፍተኛ እርምጃ እየተወሰደ ነው።
የአኒታ አባት ከእስር ለማምለጥ ነበር ጉዞውን የጀመረው።
ንብረታቸውን ሸጠው፣ ገንዘብ ከጓኞቻቸው ተበድረው፤ ወደ አውሮፓ ለሚያሻግሩ ሰዎች ከፍለው ነበር።
ህልማቸው ዩናይትድ ኪንግደም ደርሶ ጥገኝነት መጠየቅ ነበር።
የራሱል ጓደኞች ለቢቢሲ የላኩት ቪድዮ ላይ ራሱል እየሰጠመ ሳለ በኩርድኛ ሲዘፍን ይታያል።
"ሀዘን ልቤን ቢሰብረውም ኩርዲስታንን ትቼ ከመሄድ ውጪ አማራጭ የለኝም" እያለ ሲዘፍን ልጁ አርሚን ይስቅ ነበር። ጨቅላ ልጁ አርቲን ደግሞ ወደአባቱ እየዳኸ ይሄድ ነበር።
"ከተራራዎቹ ውጪ ወዳጅ የለንም"
ኩርዶች "ከተራራዎቹ ውጪ ወዳጅ የለንም" የሚል አባባል አላቸው።
የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት አክትሞ፤ የኦቶማን ግዛት ከወደቀ በኋላ ኩርዶች ነጻ እንደሚወጡ በውጪ ኃይሎች ቃል ሲገባላቸው ነበር።
በግዛቲቱ ግን ተቀባይነት አላገኘም።
እንዲያውም የትውልድ ቀዬያቸው በሦስት የመካከለኛው ምሥራቅ ግዛቶች ተከፋፈለ።

የፎቶው ባለመብት, Hengaw
ከዚያ በኋላ በኢራን፣ በቱርክ፣ በሶርያ እና በኢራቅ የሚኖሩ ኩርዶች የነጻነት ትግል ፍሬ አላፈራም።
ራሱል እና ባለቤቱ ሺቫ ወደ አውሮፓ ለመሻገር 24,000 ዩሮ ከፍለዋል።
ሦስት ልጆቻቸውን ይዘው ከቱርክ ወደ ጣልያን ከዚያም ወደ ሰሜን ፈረንሳይ መሻገር ነበር እቅዳቸው።
ሺቫን በዱንኪክ የእርዳታ መስጫ ያገኘቻት በጎ ፍቃደኛ አድራ "በጣም ቀና ሰው ናት። ትንሽ ኩርድኛ አዋርቻት ስትስቅ ነበር" ስትል ታስታውሳታለች።
ሺቫ እና ባለቤቷ በፈረንሳይ ጉዟቸው ሀብት ንብረታቸውን በአጠቃላይ ተዘረፉ።
ያኔ ለጓደኛዋ በላከችው የጽሁፍ መልዕክት፤ ለቀጣዩ የጉዟቸው ክፍል ለጭነት መኪና የሚሆን ገንዘብ እንደሌላቸው ገልጻ ነበር።
ከራሱል ጋር የነበረ ጓደኛው እንደሚለው፤ አዘዋዋሪዎቹ በቀጣዩ ቀን ጉዞ እንደሚቀጥሉ ነገሯቸው። ያ ቀን ከፍተኛ ንፋስ ስለነበር ጓደኛው ላለመሄድ ወሰነ።
"ራሱልም እንዳይሄድ ለምኜው ነበር" ሲል ያስታውሳል።
አብሯቸው የነበረ ዘጋቢ ፊልም ሰሪ ኢብራሂም ሞሐመድ ኑር እንደሚለው፤ ጀልባው ለስምንት ሰው ብቻ የተዘጋጀ ነበር። ከጭነቱ ጋር ግን 23 ሰዎች ነበሩ።
በጀልባው የነበረው የ16 ዓመቱ ያሲን፤ ከእሱና ሌሎች ሁለት ሰዎች ውጪ ነፍስ አድን ጃኬት ያደረገ ሰው እንዳልነበረ ይናገራል።
22ቱም ተጓዦች የአንድ መንደር ነዋሪዎች ነበሩ።
ሺቫና ልጆቿ በመስታወት የተሸፈነ ቦታ ላይ ነበሩ። ቦታው ሙቀት የሚሰጣቸው ይመስል ነበር። ግን አደጋው ሲከሰት አልታደጋቸውም።
ስምንት ኪሎ ሜትር ከሄዱ በኋላ ጀልባው በውሃ መሞላቱን ኢብራሂም ይናገራል።
"ውሃውን ለማፍሰስ ሞክረን ነበር። አልተሳካም" ይላል።
ተሳፋሪዎቹ ደንግጠው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ጀልባው ተገለበጠ።
የዩኒቨርስቲ ተማሪው ፒሻው ሺቫ እና ልጆቿ የነበሩበት መስታወት ሰብሮ ሊያድናቸው ቢሞክርም አልተሳካም።
ራሱል ውሃው ውስጥ ገብቶ ሊያወጣቸው ሞክሮ ነበር። እርዳታ ለማግኘት እየጮኸም ነበር።
ራሱል አርቲንን ካወጣ በኋላ ሁለቱን ልጆቹና ባለቤቱን ለማውጣት ተመልሶም ነበር።
ኢብራሂም ይህ ሁሉ ሲሆን፤ አኒታ ውሃው ላይ ስትንሳፈፍ እንዳየ ያስታውሳል።
እያለቀሰ "በአንድ እጄ ጀልባውን ይዤ በሌላ እጄ ታቀፍኳት። በሕይወት ያለች መስሎኝ ነበር። ግን ሞታለች። ራሴን ይቅር አልለውም" ይላል።
ራሱል ከውሃው ሲወጣ እያንዳንዱን የቤተሰቡን ስም እየጠራ እያነባ ነበር። ከዚያም በውሃው ተወሰደ።
የፈረንሳይ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሰዎቹን ለመታደግ የመጀመሪያው መርከብ የደረሰው ከአደጋው ከ17 ደቂቃ በኋላ ነበር።
ከአደጋው የተረፉት እንደሚሉት፤ ራሱል፣ ሺቫ፣ አኒታ እና አርሚን ሞተዋል። ጨቅላው አርቲን እየተፈለገ የነበረ ቢሆንም እንደሞተ ይታመናል።
15 ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
የመርከቡ ካፒቴኔን የሆነ ኢራናዊ በነፍስ ማጥፋት እንደሚከሰስ የፈረንሳይ መርማሪዎች ተናግረዋል።
በዚህ መንገድ ወደ አውሮፓ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
2018 ላይ 297 ሰዎች በአነስተኛ ጀልባ ዩናይትድ ኪንግደም ደርሰዋል። 2019 ላይ 1,840 በዚህ ዓመት ደግሞ ወደ 8,000 ገደማ ሰዎች ተጉዘዋል።
አብዛኞቹ ጥገኝነት ጠያቂዎች ኢራናውያን ናቸው።












