የሲሲሊ ማፊያዎችን የሚገዳደሩት ናይጄሪያውያን ሴቶች

በጣልያን

የፎቶው ባለመብት, Kate Stanworth

አፍሪካውያን ጋዜጠኞች ለቢቢሲ በሚጽፉት ሳምንታዊ ደብዳቤ ላይ ናይጄሪያዊው ጋዜጠና ኢስማኤል ኢናሼ በጣልያኗ ሲሲሊ ከተማ ስለሚገኙ አስገራሚ ሴቶች ተከታዩን ጽፏል።

በጣልያኗ ተራራማ ከተማ ሲሲሊ የሚገኙ ናይጄሪያውያን ሴቶች በአስገዳጅ የወሲብ ንግድ ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉ ሴቶችን የሚፈልግና የሚረዳ ማዕከል በአንዲት ሴት አማካይነት ተቋቁሟል።

ኦሳስ ኢግቦን በሕወጥ አዘዋዋሪዎች ወደ ጣልያኗ ደሴት ለመጡ ሴቶች መቆያ የሚሆነውን ማዕከል የከፈተችው ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ሲሆን ለናይጄሪያውያን በናይጄሪያዊ የተቋቋመ የመጀመሪያው መጠለያ ማዕከል ነው።

በአሁኑ ሰአት ማዕከሉ በሀያዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አራት ሴቶች የሚገኙ ሲሆን አንደኛዋ የልጅ እናት ናት። እስከያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ድረስ ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት ሴቶች እንደሚመጡ እጠብቃለው ትላለች።

በአንዲት ሞቃታማ የመስከረም ከሰአት ላይ እንቅስቃሴ ወደማይታይባትና ማዕከሉ ወደሚገኝበት መንደር ተጓዝኩ። ከደሴቲቱ ዋና ከተማ ፓሌርሞ በብዙ ርቀት ላይ ነው የሚገኘው ማዕከሉ። ሴቶቹን ከሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹና ማፊያ ቡድን አባላት ለመደበቅ።

ማዕከሉ ሰፋ ያለ ወጥ ቤት ያለውና በአረንጓዴው ኮረብታዎች ላይ እይታ ያለው ሰገነት ነው። አሰራሩ የተለመደ የሲሲሊ መንደር የቤት አይነት ነው።

ሴቶቹ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ክፍሎች ያላቸው ሲሆን ወጥ ቤት እና መታጠቢያ ቤት ግን በጋራ ይጠቀማሉ። ይህ ቤት በአንድ በጣሊያናዊ ጓደኛዋ የተሰጣት ነው።

በርካታ ጣሊያናውያን የናይጄሪያ ሴቶችን መርዳት ይፈልጋሉ ትላለች፤ ችግሩ ግን ፀረ-ስደተኞች ስሜት እየጨመረ በሄደበት ወቅት ሌሎች ጣሊያናውያን ይህንን እንዲያደርጉ አይፈልጉም።

አሰቃቂ ግድያዎች

ኦሳስ ኢግቦን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅኳት 2018 ላይ ሲሆን ይህ ደገሞ እሷ እና ሌሎች ሴቶች ናይጄሪያውያንን የሚረዳ ማዕከል በቤኒን ሲቲ ከቋቋሙ ከሶስት ዓመታት በኋላ ነበር።

ማዕከሉ በሲሲሊ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሴቶችን ይረዳል። አብዛኛዎቹ ሴቶች ደግሞ የሚመጡት ኤዶ ከምትባለው የናይጄሪያ ግዛት ሲሆን ዋና ከተማዋ ደግሞ ቤኒን ሲቲ ናት።

አሳስ ኢግቦን ከ18 ዓመት በፊት ነበር በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከቤቷ ተወስዳ በአስገዳጅ የወሲብ ንግድ ውስጥ እንድትገባ የተደረገችው።

ለሲሲሊ አዘዋዋሪዎቿ እዳዋን ከፍላ ከጨረሰች በኋላ በአሁኑ ሰአት ከቤተሰቦቿ ጋር ፓሌርሞ ውስጥ በደስታ እየኖረች ነው።

ነገር ግን ልክ እንደሷ መከራ የሚገጥማቸው ሴቶችን መርዳት ትፈልጋለች።

እሷና ጓደኞቿ በአውሮፓውያኑ 2011 መጨረሻ እና በ 2012 መጀመሪያ ላይ በሁለት ወጣት የናይጄሪያ ሴቶች ላይ ከተፈፀመው ዘግናኝ ግድያ በኋላ እርምጃ ለመውሰድ ተነሳስሱ።

ሟቾቹ የ20 ዓመትና የ22 ዓመት ወጣቶች ነበሩ።

ግድያው በሲሲሊ የሚገኙ ሰዎችን ያስደነገጠ ሲሆን የናይጄሪያ ሴቶች በአስገዳጅ የወሲብ ንግድ ውስጥ እንዲገቡ እየደረጉ መሆኑና በርካታ መከራዎች እንደሚያጋጥማቸው ማሳያ ሆኖ ማለፍ ችሏል።

እንደ የዓለም ስደተኞች ድርጅት መረጃ ከሆነ በአውሮፓውያኑ 2016 ብቻ 11 ሺ ናይጄሪያውያን ሴቶች ሲሲሊ መግባታቸው የተረጋጋጠ ሲሆን ከነዚህ ሴቶች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ተጭነው መጥተው የወሲብ ንግድ ውስጥ እንዲሰማሩ ተደርገዋል።

እነዚህ ሴቶች ሲሲሊ ከደረሱ በኋላ ደግሞ ለአዘዋዋሪዎቹ ክፍያ መፈጸም ግዴታቸው ነው። ሴቶቹም ለአዘዋዋሪዎቹ እስከ 35 ሺ ዶላር ድረስ የሚከፍሉ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ከወሲብ ንግድ የሚያገኙትን ገንዘብ በክፍያ መልክ ይወስዱባቸዋል።

ሴቶቹ ጣልያን ከመድረሳቸው በፊት የሚፈጸሙት ሐይማኖታዊ ቃለ መሀላ መሰል ነገር አለ። ስነስርአቱ ሲካሄድ ቄሶች ጭምር የሚገኙ ሲሆን ከአዘዋዋሪዎቹ ቃል የሚወጡ ከሆነና እዳቸውን የማይከፍሉ ከሆነ ሴቶቹ እንዲሁም የሚወዷቸው ቤተሰቦች ጉዳት እንደሚደርስባቸው ይነገራቸዋል።

አብዛኛዎቹ ከገጠራማ ክፍል የሚመጡት ሴቶች ይህንን ፍራቻ ምንም አይነት እርምጃ አይወስዱም። አብዛኛውን ጊዜም ገንዘባቸውን ለመጠየቅ እንኳን ድፍረት አይኖራቸውም።

ኦሳስ ኢግቦን እንደምትለው ሴቶቹን ከማፊያ ቡድኖቹ ለማላላቀቅ ከፍተኛ ፈተና የሚፈጥረው ይህ የሚገቡት ቃል ነው።

በቤኒን ሲቲ የሚገኘው መጠለያ ማዕከል ሴቶቹ ወደ ጣልያን ከመሄዳቸው በፊት ስለሚጠብቃቸው መከራና ስቃይ ቀድሞው እንዲያውቁ የሚሰራ ሲሆን ወደ አገራቸው ለሚመለሱ ሴቶች ደግሞ የስነልቦና ድጋፍና ምክር ይሰጣል።

''በፓሌርሞ የሚገኘው ማዕከል ደግሞ ከዚህ መሰል መከራ ያመለጡ ሴቶች የትምህርት ዕድል እንዲሁም ጣልያንኛ እንዲማሩና ሌላ ስራ እንዲያገኙ ይመቻችላቸዋል'' ትላለች ኦሳስ ኢግቦን።

ሴቶቹ በማዕከሉ እስከ አንድ ዓመት ድረስ እንዲቆዩ የሚደረገ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ያጋጠማቸውን መጥፎ ትዝታ እንደሚረሱና ለወደፊቱ ሕይወታቸው ለመዘጋጀት እንደሚያስችላቸው ይገመታል።

ምንም እንኳን ማዕከሉ በበጎ ፈቃደⶉች የሚታገዝ ቢሆንም ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ግን በሌሎች በጎ አድራጊዎች ድጋፍ ላይ የተመሰረተ ነው። በፓሌርሞ የሚኖሩ ናይጄሪያውያንም ቢሆኑ የተቻላቸውን እርዳታና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ኦሳስ ትገልጻለች።