አሜሪካ፡ የስድስት ዓመቱ ታዳጊ በጎ ተግባር የበርካቶችን ልብ ነክቷል

ብሌክ ደግ በመሆን ሌሎችን ማስደሰት እንደሚፈልግ ይናገራል

የስድስት ዓመቱ ልጅ በማክዶናልድ ከጀርባው ለተሰለፈው ግለሰብ ያደረገው በጎ ነገር ለመገበያየት ከጀርባው ተሰልፈው የነበሩትን ሁሉ ልብ የነካ ነገር ሆኗል።

ብሌክ ዱርሃም የተሰኘው ይህ የስድስት ዓመት ልጅ ቁርሱን ለመግዛት ከእናቱ ጋር በማክዶናልድ ተሰልፎ ነበር።

በኋላ ግን ከጀርባው ለተሰለፈው ሰው አንዳች ነገር ማድረግ እንሚፈልግ ለእናቱ ይነግራታል።

ከዚያም ለምትታዘዛቸው ግለሰብ ከጀርባቸው የቆመው መኪና ውስጥ ላለው ግለሰብ ምግብ መግዛት እንደሚፈልግ ይነግራታል።

ቀጥሎም መኪናቸው ውስጥ በመሆን ተራቸውን እየጠበቁ የነበሩ ሌሎች ግለሰቦች በአጠቃላይ አንዳቸው ለሌላኛቸው በመክፈል የዚህን ታዳጊ ልጅ በጎነት ተጋርተዋል።

ብሌክ ስለምግባሩ ለጠየቁት ጋዜጠኞች ሲመልስ እርሱ የመጀመሪያው ፍላጎቱ " ደስተኛ መሆንና ቀሪዎችን ማስደሰት እንደነበር" ግልጿል።

የብሌክ እናት የሆነችው አሚ ዱርሃም የልጇ ዋነኛ ትኩረት "ሌሎች ሰዎችን ማስደሰት ነው። ያንን ማድረግ ነበር የፈለገው" ስትል ተናግራለች።

አክላም " ከጀርባችን የነበረው ግለሰብ ፊቱ ላይ የነበረውን የደስታ ፀዳል አይቼ፣ 'ተመልከት ሰውየውን ምን ያህል እንዳስደሰትከው' አልኩት" ስትል የነበረውን ሁኔታ ታስታውሳለች።

" የአንድ ትንሽ ልጅ ደግ ልብና በጎ ምግባር እንደዘያ አይነት ምላሽ ማምጣቱ የሚደንቅ ነው" ካለች በኋላም " እጅግ በጣም ልብ የሚያሞቅና ደስ የሚል ስሜት ነው" ብላለች።