ኮሮናቫይረስ፡ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ ማለፉን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ህዳር 2/2013 ዓ.ም አስታወቀ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በፌስቡክ ገፁ ላይ ይፋ እንዳደረገው በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ መከሰቱ ከታወቀበት መጋቢት 4 /2012 ዓ.ም ጀምሮ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 100 ሺህ አልፏል።
የኮቪድ-19 ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በቫይረሱ የተያዘ ሰው የተገኘው መጋቢት 4/ 2012 ዓ.ም ሲሆን እስካሁን ድረስ ለ1,534,470 ምርመራ ተደርጎ 100 ሺህ 327 በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
በኢትዮጵያ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 1ሺህ 537 መሆናቸውን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መግለጫ ያትታል። አክሎም 61 ሺህ 516 ህሙማንም ከበሽታው አገግመዋል ሲል ገልጿል።
የጤና ሚኒስቴሩ አክሎም "ኮሮና የለም" ከሚል የተሳሳተ አመለካከት በመውጣት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በመከላከሉ ላይ ጠንክሮ እንዲሰራ ጥሪ አቅርቧል።
የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትም "ማስክ ካልተደረገ አገልግሎት የለም" የሚለውን መርህ እንዲከተሉ አሳስቧል።
በበርካታ አገራት በኮቪድ-19 የሚያዙ ከፍተኛ ቁጥር መመዝገቡን ተከለትሎ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ከ50 ሚሊዮን አልፏል።
እንደጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ ከ1.25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል።
በብዙ አገራት በቂ ምርመራ ባለመደረጉ እንጂ ይህን አሃዝ ከፍ ያለ ነው ተብሎ ይገመታል።
በመላው አለም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁትር 51,554,166 መድረሱን የዩኒቨርስቲው መረጃ ያሳያል።
በቫይረሱ በከፍተኛ ቁጥር ከተያዙት አገራት መካከል አሜሪካ፣ ሕንድ እና ብራዚል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይገኙበታል።
እንደ አፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር መረጃ ከሆነ እስካሁን ድረስ በአፍሪካ 1,904,820 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ 45,954 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን ከዚሁ ጋር በተያያዘ አጥተዋል።

















