የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝ አዲስ አይነት የአእምሮ ጤና እክል ይዞ መጥቷል ተባለ

አንዛይቲ

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

በኮሮናቫይረስ ከሚያዙ ሰዎች በእያንዳንዱ 17 ሰው አንድ ሰው ከባድ ጭንቀት፣ ድብርት እና እንቅልፍ ማጣት ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚያጋጥመው አንድ አሜሪካ ውስጥ የተሰራ ጥናት ጠቁሟል።

ይህ ቁጥር ታዲያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች የሚያጋጥማቸው እንዲህ አይነት የጤና እክል ከሌሎች በሽታዎች ጋር ሲነጻጸር እጥፍ እንደሆነ ደርሰንበታል ይላሉ ጥናቱን ያካሄዱት ባለሙያዎች።

በጥናቱ መሰረት ባልተጠበቀ ሁኔታ የቀደም የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች በኮሮናቫይረስ የመያዝ እድላቸው ከጤናማ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር 65 በመቶ ከፍ ያለ እንደሆነ ደርሰንበታል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያትነት የተቀመጠው የአእምሮ ጤና ችግር ኣላባቸው ታማሚዎች ሰውነታቸው የሚገኝበት አካላዊ ጥንካሬ፣ የሚወስዷቸው መድሀኒቶችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑትና የጥናቱ መሪው ፖል ሀሪሰን እንደሚሉት ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙ ለከባድ የአእምሮ ጤና እክል የመጋለጣቸው እድል አብሮ ይጨምራል።

''ሌላው ቀርቶ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ ነገር ግን ሆስፒታል ሳይሄዱ በቤታቸው የዳኑት እንኳን ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው'' ይላሉ።

ተመራማሪዎቹ 62 ሺህ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ፈቃደኛ ሰዎችን ለሶስት ወራት ያክል ሲከታተሉ የነበረ ሲሆን ከእነሱ የሚያገኙትን መረጃ እንደ ጉንፋን፣ የኩላሊት ህመም እንዲሁም የአጥንት ስብራት ካጋጠማቸው ሰዎች ጋር አወዳድረውታል፥።

በዚህም መሰረት በኮሮናቫይረስ የተያዙት ሰዎች ከፍተኛ የአእምሮ ጤና መቃወስ ታይቶባቸዋል ተብሏል። በኮሮናቫይረስ የተያዙት ሰዎች በከባድ ጭንቀት፣ ድብርት እና እንቅልፍ ማጣት የመጠቃት ዕድላቸው ከሌሎቹ አንጻር 18 በመቶ ከፍ ብሎ ታይቷል።

እንደዚህ ባሉ ሁኔታዎች መጠራጠርን እና ፍርሃትን መቋቋም አለመቻል የተለመደ የአእምሮ ህመም ባህሪ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

"ብዙ ጊዜ የጭንቀት ህመም ገና ባልተፈጠረና ባልታወቀ ነገር ላይ ይሆናል ብሎ አብዝቶ በመጨነቅ የሚመጣ ነው። ከዚህ አንፃር ኮሮናቫይረስ ከባድ ነገር ነው" ፕሮፌሰር ፖል ሀሪሰን

አዲስ ነገር በሚያጋጥመን ጊዜ አዕምሯችን ለተፈጠረው ነገር በተለያየ መንገዶች ምላሽ ይሰጣል። በአሁኑ ወቅት መላውን ዓለም እያስጨነቀ ያለው ኮሮናቫይረስም በኑሯችን፣ በሥራችናና በአጠቃላይ ህይወታችን ላይ ከዚህ በፊት ያልነበረ ሁኔታን ፈጥሯል።

በዚህም ሳቢያ አዕምሯችን ወረርሽኙን በተመለከተና ተያያዥ ነገሮችን በተለየ ሁኔታ ለመገንዘብ ተገዷል። ይህም ክስተት ነው በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ለተለያዩ የአእምሮ ጤና ችግሮች እያጋለጣቻው የሚገኘው።

ሰዎች አይደለም እንዲህ ነገሮች ከበድ ባሉበት ወቅት አይደለም በደህናው ዘመን እንኳን ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን በአካል ማግኘት አስቸጋሪ ሲሆንና ሃሳብ ጭንቀታቸውን አይን አይናቸውን እያዩ ማካፈል ሳይችሉ ሲቀሩ ቀላል የማይባል ሥነ ልቦናዊ ጫና ይደርስባቸዋል።