የባይደን መመረጥ ለአፍሪካ አዲስ እድል ይዞ ይመጣል ተባለ

የባይደን መመረጥ ለአፍሪካ አዲስ እድል ይዞ ይመጣል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ አዲስ ፕሬዝዳንት መመረጡ የአፍሪካ አገራት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የነበራቸውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንደ አዲስ የሚጀምሩበት እድል እንደሚሰጣቸው ተነገረ።

ይህንን ያሉት መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገውና አሜሪካውያን በአፍሪካ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያበረታታው 'ኮርፖሬት ካውንስል አፍሪካ' የቀድሞ ፕሬዝዳንት ስቴፈን ሃይስ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት ጆ ባይደን ወደ ስራ ሲገቡ ከአፍሪካ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ዙሪያ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ይዘው ይመጣሉ።

''ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለና አዳዲስ አሰራሮችን ያካተተ አካሄድ እንደሚኖር አስባለሁ። ምክንያቱም ከፕሬዝዳንቱ ጋር የሚመጡት ሰዎች ያለምንም ጥርጥር ከትራምፕ አስተዳደር በተሻለ ለአፍሪካ ቅርበት ያላቸው ናቸው'' ብለዋል።

የቀድሞው የካውንስሉ ፕሬዝዳንት ከቻይና ጋር በተያያዘ ስለሚኖረውም ፉክክር ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

''ጆ ባይደን የአሜሪካና ቻይና ፉክክር ላይ የሚያተኩሩ አይመስለኝም። ነገር ግን አሜሪካና አፍሪካ በቢዝነስና ፖለቲካው ረገድ ተባብረው የሚሰሩባቸውን መንገዶች ማጠናከር ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ''

''እንደሚመስለኝ አፍሪካውያን ከአሜሪካ ጋር ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸው ዘርፎች እንደ ጤና፣ ግብርና እንዲሁም በመረጃና ቴክኖሎጂ አካባቢዎች ናቸው''

በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚጠቅሱት አፍሪካ 'ከአጎዋ' ስምምነት በርካታ ጥቅሞችን ያገኘች ሲሆን አህጉሪቱ የተለያዩ ምርቶቿን ወደ አሜሪካ ገበያዎች ለማቅረብ በእጅጉ ረድቷታል።

ስምምነቱ በአውሮፓውያኑ 2025 ላይ የሚያበቃ ሲሆን ቀደም ብለው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደግሞ በአጠቃላይ ከሚደረግ ስምምነት ይልቅ በተናጥል ከአገራት ጋር መደራደርን እንደሚመርጡ ገልጸው ነበር። በዚህ ተጠቃሚ ከሆኑ አገራት መካከል ኬንያ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች።

''አፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና መመስረት ከቻለች ከአሜሪካ ጋር ዘርፈ ብዙ ስምምነቶች ለመድረስ ቀላል ይሆናል'' ይላሉ ባለሙያው።