የኮሮናቫይረስ ክትባት መገኘት ተስፋ የዓለም ገበያን እያነቃቃው ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኮቪድ-19ን ለመከላከል ይረዳሉ የተባሉ ክትባቶች ወደመጨረሻ ደረጃቸው ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ የዓለም ገበያ እንደ አዲስ እየተነቃቃ መሆኑ ተዘግቧል።
ፋይዘር የተባለው መድሀኒት አምራች ኩባንያ ኮሮናቫይረስን የመከላከል አቅሙ 90 በመቶ ነው ያለውን ክትባት ይፋ ካደረገ በኋላ የድርጅቱ ድርሻ በዓለም ገበያ በ9 መቶ ከፍ ማለቱ ተስተውሏል።
በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊው ጆ ባይደን መሆናቸው ከተነገረ ወዲህ መነቃቃት እያሳየ የነበረው ዓለም ገበያ አሁን ደግሞ ክትባቱን ተከትሎ ሌላ እሽቅድድምን ፈጥሯል።
የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአክስዮን ገበያ ከአውሮፓውያኑ የ2008 የዓለም የገንዘብ ቀውስ ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መቀነሱ የሚታወስ ነው።
በአሜሪካ የሚገኙ ድርጅቶች የአክሲዮን ዋጋቸው ከ1.1 በመቶ እስከ 5.6 በመቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍ ያለ ሲሆን በእሲያና አውሮፓ የሚገኙ ድርጅቶችም ድርሻቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ አሳይቷል።
ክትባቱን ይፋ ያደረጉት ፋይዘርና ባዮኤንቴክ ክትባቱን በሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። በቁጥር የበዙ ክትባቶች የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን ይህ ክትባት ተስፋ ከተጣለባቸው ውስጥ ቀዳሚው ነው።
ከዚህ ቀደም የተደረገው ሙከራ ክትባቱ ሰውነታችን ከበሽታው ጋር እንዲለማመድና አንቲቦዲዎችን እንዲያዳብር መርዳቱ የተስተዋለ ሲሆን ሌላው ደግሞ ቲ-ሴል በመባል የሚታወቀው የመከላከል አቅምን የኮሮናቫይረስን መዋጋት እንዲችል አድርጎታል ተብሏል።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው 'ኤፍቲኤስኢ 100' የወረርሽኙ ዜና ከተሰማበት መጋቢት ወር ጀምሮ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በዓለም አቀፍ ገበያ ድርሻው ላይ የ82 ቢሊየን ፓውንድ ጭማሪ አግኝቷል።
የተለያዩ መድሃኒት አምራች ኩባንያዎች እየሞከሯቸው ባሉት የክትባት ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያገኙ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ መግለጻቸውን ተከትሎ የዓለም አቀፍ ገበያው ከዚህም በበለጠ ሊያድግ እንደሚችል ተጠቁሟል።













