አርሜኒያ "እጅግ በጣም የሚያም" ያለችውን የሰላም ስምምነት ከአዘርባጃን ጋር ለመፈረም ተገደደች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአርሜኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺንያን በሩሲያ አደራዳሪነት የፈረሙትን የሰላም ስምምነት "እጅግ በጣም የሚያም" ብለውታል።
አርሜኒያና አዘርባጃን ላለፉት ስድስት ሳምንታት ናጎርኖ ካራባህ በተሰኘች ግዛት የይገባኛል ጥያቄ የተነሳ የለየለት ጦርነት ውስጥ ነበሩ።
በጦርነቱም በሺዎች ተገድለዋል፣ በመቶ ሺዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።
የናጎርኖ ካራባህ ራስ ገዝ ግዛት በዓለም አቀፍ ሕግ የአዘርባጃን ክልል ቢሆንም ከ1994 ጀምሮ ግን በአርሜኒያ መንግሥት ድጋፍ የሚደረግለት፣ አርሜኒያዊያን ብሔር ተወላጆች የሚኖሩበት ከአዘርባጃን ቁጥጥር ያፈነገጠ ግዛት ሆኖ ቆይቷል።
አዘርባጃን ስትዋጋ የነበረውም ይህንኑ ሕጋዊ ግዛቷን ለማስመለስ ነበር።
የሰላም ስምምነቱ ምን ይዟል?
ይህ ሩሲያ ያሸማገለችው አዲስ የሰላም ስምምነት በአገሬው አቆጣጠር ከማክሰኞ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።
በዚህ ስምምነት መሰረት አዘርባጃን እስካሁን በጦርነት ድል ያደረገቻቸው የናጎርኖ ካራባህ ቦታዎችን ይዛ ትቆያለች።
አርሜኒያ ደግሞ ቀስ በቀስ በሳምንታት ውስጥ ከተቀሩት የግዛቱ አካባቢዎች ለመልቀቅ ተስማምታለች።
ይህ ተፈጻሚ እንዲሆን ደግሞ ቭላድሚር ፑቲን 2ሺ የሚሆኑ ወታደሮቻቸውን ወደ አካባበው በሰላም አስከባሪነት ይልካሉ።
ሩሲያ ብቻም ሳይሆን ቱርክም ወታደሮቿን በሰላም ማስከበር ወደ ግዛቱ ታስገባለች።
ይህ ስምምነት የጦር ምርኮⶉችን መለዋወጥን፣ የተዘጉ ድንበሮችንና የጉዞ እቀባዎች ማንሳትን ይጨምራል።
አዘርባጃን የሰላም ስምምነቱ ትልቅ ድል ነው ስትል በአርሜኒያ በኩል ግን "የተሸለው አማራጭ" ተደርጎ ተወስዷል።
በአርሜኒያ ዋና ከተማ የረቫን መንግሥታቸው በተሸናፊነት መፈረሙ ያስቆጣቸው ዜጎች የመንግስት ንብረቶችን ሲያወድሙና ተቃውሞ ሲያሰሙ ታይተዋል።
አርሜኒያ ወደ ጦርነቱ በታላቅ ጀብዱ ከተቀላቀለች ወዲህ የአዘርባጃንን ጥቃት መከላከል ተስኗት ቆይታለች።
ትናንት የራስ ግዝ ግዛቱን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ሹሻን በአዘርባጃኖች ተነጥቃለች።
ትናንት አዘርባጃን በስህተት የሩሲያ አውሮፕላንን መትታ ጥላለች። ለድርጊቱ ከፍተኛ ይቅርታ ጠይቃለች። በስህተት ነው የመታሁት፣ ካሳም እከፍላለሁ ብላለች።













