አሜሪካ፡ ጆ ባይደንን እንኳን ደስ አለዎት ያላሉት መሪዎች የትኞቹ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጆ ባይደን የአሜሪካ ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ በርካታ የዓለማችን መሪዎች እንኳን ደስ አለዎት ለማለት ፈጥነዋል።
ነገር ግን ሁሉም የዓለም አገር መሪዎች በአንድ ድምጽ የጆባይደን ፕሬዝዳንት ሆኖ መመረጥ ደስታ እንደፈጠረባቸውና አብረው ለመስራትም ዝግጁ መሆናቸውን አልገለፁም።
በተመራጭ ፕሬዝዳንቱ መመረጥ የተሰማቸውን ካልገለፁ የዓለማችን መሪዎች መካከል የሩሲያው ፕሬዝዳንት አንዱ ናቸው። ከአራት ዓመት በፊት ፕሬዝዳንት ፑቲን ዶናልድ ትራምፕ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ቀድመው እንኳን ደስ አለዎት ካሉ መሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ።
አሁን ግን ምንም ዓይነት የትዊት፣ የቴሌግራም ወይንም የስልክ መልዕክት አልላኩም። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔስኮቭ እንኳን ደስ አለዎት ለማለት የዘገዩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የምርጫውን ውጤት በማስመልከት የመሰረቱት ክስ ነው ብለዋል።
''እኛ ትክክለኛው ነገር ብለን የምናስበው የምርጫው ውጤት በይፋ ሲገለጽ ነው'' ብለዋል ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቆይታ። ነገር ግን ሞስኮ የሚገኘው የቢቢሲው ዘጋቢ ስቲቭ ሮዝንበርግ ከሞስኮ በኩል የእንኳን ደስ አለዎት መልእክት አለመላኩ በውጤቱ ደስተኞች አለመሆናቸውን ያስጠረጥራል ይላል።
ጆ ባይደን ቀንደኛ የሩሲያ ተቺ ሲሆኑ በቅርቡም የአሜሪካ ትልቋ ጠላት ሩሲያ ናት ብለው ነበር። ከ2016ቱ ምርጫ ጋር በተያያዘም ሩሲያ ጣልቃ ገብታለች በማለት ይከሳሉ ባይደን።
ሌላኛው ምንም አስተያየት ያልሰጡት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶጋን ናቸው።
በ2016 በተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ ማሸነፋቸው ከተነገረ ከአንድ ቀን በኋላ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ስልክ በመደወል የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን አስተላልፈው ነበር።
በተመሳሳይ 2012 ላይ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሲያሸንፉ እንኳን ደስ አለዎት ብለው ነበር።
ኤርዶጋን ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ጠበቅ ያለ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ባለፉት አራት ዓመታት አሜሪካ ቱርክ ላይ በሩሲያ በኩል ሊጣሉ የሚችሉ ማዕቀቦችን መከላከል ችላለች።
አንዳንድ የአካባቢው ተንታኞች ኤርዶጋን እስካሁን ምንም ያላሉት ወዳጃቸው ዶናልድ ትራምፕን ላለማስከፋት እንደሆነ እየገለጹ ነው። ነገር ግን ከዚህ በኋላ ጆ ባይደንን እና ቱርክ የሚኖራቸው ግንኙነት ወደፊት የምናየው ነው።














