የትራምፕ መሸነፍ በደስታ ያሰከራቸው አደባባይ ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የጆ ባይደንን ድል ተከትሎ በተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ደስታ ፈንቅሏቸው ወደ አደባባይ ወጥተዋል፡፡
ከፍተኛ ትንቅንቅ በታየበት የባይደንና የትራምፕ የምርጫ ውጤት ቆጠራ እልህ አስጨራሽ ሆኖ ነበር የተጠናቀቀው፡፡
ሁለቱ ተፎካካሪዎች በየግዛቱ አንዱ ሌላውን ያሸነፈበት የድል ህዳግ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ምርጫ ታይቶ የሚታወቅ አይደለም፡፡
በመጨረሻም 20 የውክልና ድምጽ ያላትን ፔኒሲልቬኒያ ግዛትን ማሸነፍ የቻሉት ባይደን ለማሸነፍ ከሚያስፈልገው 270 የውክልና ድምጽ በላይ በማስቆጠራቸው ባለ ድል ሆነዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ነው በበርካታ የአሜሪካና ከአሜሪካ ውጭ ባሉ ከተሞችም ጭምር ድግሱ የተጧጧፈው፡፡እነዚህ ድግሶች ብዙዎቹ ታስቦባቸው የተሰናዱ ሳይሆኑ መገናኛ ብዙኃን የባይደንን አሸናፊነት መናገራቸውን ተከትሎ በግብታዊነት ሕዝብ ደስታ ፈንቅሎት አደባባይ በመውጣት የተከበሩ ናቸው፡፡
ኒውዮርክ ሎስ አንጀለስ በዚህ ረገድ የቀደማቸው የለም፡፡ በአጭር ደቂቃ ውስጥ አደባባዮቻቸው በሕዝብ ተሞልተዋል፡፡
በኒውዮርክ ታይምስ ስኩዌር አደባባይ ሰዎች ለመገናኘትና ድሉን ለማጣጣም አዋጅና መጠራራት አላስፈለጋቸውም፡፡ በደቂቃዎች ውስጥ አደባባዩ በሕዝብ ታጨቀ፡፡
በትራምፕ መኖርያና ቢሮ (ዋይትሐውስ) ደጃፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ዜጎች ድሉን ተከትሎ አደባባይ ወጥተዋል፡፡ ብዙዎቹ የአፍ-አፍንጫ ጭምብል ማጥለቃቸውን በማየት ብቻ የማን ደጋፊ እንደሆኑ መናገር ይቻላል፡፡
ዋይትሐውስ ከድሉ ቀደም ብሎ ረብሻ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ዘለግ ያለ አጥር እንዲታጠር ተደርጎ ነበር፡፡ ሆኖም የድጋፍ ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ አልፏል፡፡
የባይደን ድል የማይተዋወቁ ሰዎችን ጭምር ያስተቃቀፈ ነበር፡፡ በአደባባይ በርካታ የባይደን ደጋፊዎች ትራምፕ ከነጩ ቤተ መንግስት የመሰናበታቸው እውነታ በደስታ አስክሯቸው እርስ በርስ ፎቶ ሲነሱ፣ ሙዚቃ ከፍተው ሲወዛወቁ፣ ሻምፓኝ ሲራጩ ነበር፡፡
ዓለም በዚህ ሁኔታ በደስታ ሲሳከር ተሸናፊው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፐ ቨርጂኒያ በአንድ የጎልፍ ክለብ ውስጥ ነበሩ፡፡












