ካማላ ሃሪስ፡ የመጀመሪያዋ ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካማላ ሃሪስ የመጀመሪያዋ ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ታሪክ ሰርተዋል።
ይህም ብቻ የመጀመሪያዋ ጥቁር እና እስያ አሜሪካዊ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን በታሪክ መዝገብ ላይ ይሰፍራሉ።
ካማላ ሕንዳዊ ከሆኑት እናታቸው እና ጃማይካዊ ከሆኑት አባታቸው በካሊፎርኒያ ነበር የተወለዱት።
የ55 ዓመቷ የካሊፎርኒያ ሴናተር በዚህ ወሳኝ ወቅት ከተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጋር በመሆን አሜሪካንን ለቀጣይ አራት ዓመታት ይመራሉ።

ካማላ ገና በልጅነታቸው ወላጆቿ መፋታታቸውን ተከትሎ እናታቸው ነበሩ ያሳደገቿው።
የካማላ እናት እውቅ የካንስር ሕመም ተመራማሪ እና የመብት ተሟጋች ነበሩ።
ካማላ አስተዳደጋቸው የህንድ ባህል የተከተለ ነበር። ከወላጅ እናታቸው ጋር በተደጋጋሚ ለጉብኝት ወደ ህንድ ይጓዙ ነበር። ይሁን እንጂ ካማላ ወደ ፖለቲካው ከገቡ በኋላ ወላጅ እናታቸው ያሳደጓቸው የጥቁር አሜሪካውያንን ባህል እና አኗኗርን በተከተለ መልኩ ነበር።
"እናቴ ሁለት ጥቁር አሜሪካውያንን እያሳደገች እንደሆነ ነው የምትረዳው። ያደግነበት ማህብረስብ እኔን እና እህቴን እንደ ጥቁር ሴቶች አድርጎ እንደሚቀበለን ተረድታ ነበር" በማለት ካማላ የሕይወት ታሪካቸውን በያዘው መጽሐፍ ላይ አስፍረዋል።
ካማላ በልጅነት እድሜያቸው በካናዳ ኖረዋል። ወላጅ እናታቸው ካናዳ በሚገኘው ማክጊል ዩኒቨርሲቲ መምህር ነበሩ። በካናዳዋ ሞንትሪያል ለአምስት ዓመታት ኖረዋል።
የኮሌጅ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ደግሞ በአሜሪካዋ ሆዋርድ ዩኒቨርሲቲ ነው። ከአራት ዓመታት የትምህርት ቆይታ በኋላ ካማላ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ለመስራት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያን ተቀላቅለዋል።
ካማላ ዐቃቤ ሕግ በመሆን ረዘም ላለ ዓመታት አገልግለዋል። እአአ 2003 ላይ ካማላ የመጀመሪያዋ የካሊፎርኒያ ጥቁር ሴት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመሆን ተመርጠዋል።
እአአ 2014 ላይ የሕግ ባለሙያ ከሆኑት ዶግ ኤምሆፍ ጋር ትዳር መስረተዋል።












