ኮሮናቫይረስ፡ የኬንያ ፖሊስ የኮቪድ-19 መመሪያን ተላልፈዋል ያላቸውን 1000 ሰዎች በቁጥጥር ስር አዋለ

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ በመጠጥ ቤቶች በፌሽታ ላይ የነበሩ ሰዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተይዘዋል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የኬንያ ፖሊስ የኮቪድ-19 ስርጭት ለመከላከል የተቀመጡ መመሪያና ደንቦችን ተላልፈዋል ያላቸውን 1000 ሰዎች በቁጥጥር ስር አዋለ።

የአገሪቱ ባለስልጣናት አብዛኞቹ ሰዎች በመጠጥ ቤቶች፣ ከመጋቢት ወር ጀምሮ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቀመጠውን የሰዓት እላፊ ተላልፈው መያዛቸውን ተናግረዋል።

ኬንያ 62000 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በምርመራ ሲረጋገጥ ከእነዚህም መካከል 1000 ያህሉ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ፖሊስ በመላ አገሪቱ በሚገኙ መጠጥ ቤቶችና መዝናኛ ስፍራዎች ድንገተኛ አሰሳ በማድረግ እና የተቀመጠውን መመሪያ መተግበሩን በማረጋገጥ የሁለተኛ ዙር የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ሙከራ እያደረገ ነው ተብሏል።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ በመጠጥ ቤቶች በፌሽታ ላይ የነበሩ ሰዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተይዘዋል።

ሰዎቹ ከምሽቱ 3፡00 በኋላ በመጠጥ ቤት ውስጥ የተገኙ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያላደረጉ ናቸው ተብሏል።

ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች በአጠቃላይ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡና 200 የአሜሪካ ዶላር (20000 ሽልንግ ገደማ)እንደሚቀጡ አስተውቋል።

ከሰዓት እላፊ በኋላ ደንበኞቻቸውን ሲያስተናግዱ የነበሩ የመጠጥ ቤት ባለንብረቶች የንግድ ፈቃዳቸው እንደሚሰረዝ እና እንደማይታደስላቸው ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአንዳንድ የአገሪቱ የገጠር ክፍሎች መስፋፋቱን ተከትሎ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ያስችላሉ ያሏቸውን መመሪያዎች በቅርቡ አስተላልፈው ነበር።

ኮሮና