በሞዛምቢክ ከ50 በላይ ሰዎች በጽንፈኞች 'አንገታቸው ተቀላ'

ሞዛምቢክ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በሞዛምቢክ ጽንፈኛ ኢስላማዊ ታጣቂዎች በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ከ50 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን 'አንገት መቅላታቸውን' የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገበ።

ታጣቂዎቹ በአንዲት መንደር የሚገኝ የእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ ሰዎቹን የገደሉ ሲሆን ሟቾቹ እጅግ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ መገደላቸውን የሚጠቁሙ ሌሎች ሪፖርቶችም እየወጡ ይገኛሉ።

በሌላ መንደር ደግሞ በተመሳሳይ የበርካታ ሰዎች አንገት እንደተቀላ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በሞዛምቢክ ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት በሚገኝባት ካቦ ዴልጋዶ ግዛት ታጣቂዎች ይህን መሰል ጥቃት ሲፈጽሙ የመጀመሪያቸው አይደለም። በአካባቢው እንዲህ አይነት ጥቃቶች መፈጸም የጀመሩት በአውሮፓውያኑ 2017 ላይ ነበር።

አብዛኛዎቹ ነዋሪዎቿ የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑባት በዚች ግዛት እየተካሄደ ባሉ ግችቶች መክንያት እስካሁን እስከ 2 ሺ የሚደርሱ ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን 430ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገድደዋል።

ግድያውን የፈጸመውና ከኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት የታጣቂ ቡድን በደቡባ አፍሪካዊቷ አገር ሞዛምቢክ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር እየሞከረ ይገኛል።

በአገሪቱ የተንሰራፋውን ድህነትና ስራ አጥነት በመጠቀም በርካታ ወጣቶችን እየመለመለ ሲሆን በአካባቢው ኢስላማዊ አስተዳደር ለመመመስረት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በርካታ ነዋሪዎችም ከአካባቢው ከሚወጣው ነዳጅ ሃብት እምብዛም ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።

ናንጃባ በምትባለው መንደር ታጣቂዎቹ ተኩስ በመክፈትና መኖሪያ ቤቶችን በማቃጠል ነዋሪዎቹን ማሸበር እንደጀመሩ ከመንግስት ጋር ግንኙነት ያለው የዜና አውታር አንድ ከጥቃቱ የተረፈ ሰውን ጠቅሶ ዘግቧል።

አክሎም ታጣቂዎቹ የሁለት ሰዎችን አንገት ከቀሉ በኋላ በርካታ ሴቶችን አግተው እንደወሰዱ ዘግቧል። ሌላ ታጣቂ ቡድን ደግሞ ሙቲዴ በምትባል መንደር ከ50 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን እንደቀላ ጠቅሷል።

ታጣቂዎቹ ሲመጡ ለማምለጥ የሞከሩ ነዋሪዎች በአካባቢው በሚገኝ የእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገው አንገታቸው እየተቀላ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን 'ፒናክል' የተባለ የግል የዜና ወኪል ዘግቧል።

የሞዛምቢክ መንግስት ወታደሮቹ ታጣቂዎችን ለመዋጋት ልዩ የሆነ ስልጠና እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን እርዳታ ጠይቋል።